ፕሬዝደንታዊ ዕጩዎቹ ከልጅነት እስከ ዕውቀት - ከዚህ ቀደም ያልታዩ የሃሪስ እና የትራምፕ ፎቶዎች

ሃሪስ እና ትራምፕ በሦስት ዓመታቸው የተነሱት ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, ሃሪስ እና ትራምፕ በሦስት ዓመታቸው የተነሱት ፎቶ

የአሜሪካ ምርጫ ሲቃረብ መራጮች በዕጩዎች ፎቶ ይጨናነቃሉ። ዕጩዎች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ፤ ደጋፊዎቻቸውን ሲጨብጡ፤ አውሮፕላን ሲሳፈሩ እና ሲወርዱ።

ነገር ግን የብዙዎቹ ዕጩዎች የቀድሞ ፎቶዎች ብዙም ብቅ ሲሉ አይታዩም።

ከላይ የሚታዩት ዶናልድ ትራምፕ እና ካማላ ሃሪስ ዋይት ሐውስ ምን እንደሆነ እንኳ ሳያውቁ በፊት በሦስት ዓመታቸው የተነሷቸው ፎቶዎች ናቸው።

እነሆ በርካታ አስርት ዓመታት አልፈው ዲሞክራቷ ዕጩ ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ ተፋጠዋል።

ካማላ ልጅነታቸውን ያሳለፉት በካሊፎርኒያ ግዛት ኦክላንድ ከተማ ነው፤ ትራምፕ ደግሞ በኒው ዮርክ ግዛት ኩዊንስ ነው ያደጉት።

ሃሪስ እና እህታቸው ማያ የካንሰር ጥናት ባለሙያ እና የማኅበረሰብ አንቂ በሆኑት ሕንዳዊት እናታቸው ሺያማላ ጎፓላን ሃሪስ እንክብካቤ ነው ያደጉት።

የትራምፕ አባት ፍሬድ ትራምፕ ደግሞ የጀመርን ስደተኞች ልጅ ሲሆኑ፣ እናታቸው ማሪ አን ትራምፕ ደግሞ ስኮትላንድ ነው የተወለዱት።

ትራምፕ በ13 ዓመታቸው የኒው ዮርክ ወደ ሚገኘው ወታደራዊ አካዳሚ ገብተዋል።

ሃሪስ ከእታቸው እና ከእናታቸው ጋር፤ ትራምፕ እና ወላጆቻቸው

የፎቶው ባለመብት, Kamala Harris / @realDonaldTrump

የምስሉ መግለጫ, ሃሪስ (በስተግራ ቢጫ ልብስ ያደረጉት) ከእታቸው እና ከእናታቸው ጋር፤ ትራምፕ እና ወላጆቻቸው (በስተቀኝ)

ሃሪስ በካናዳ ሞንትሪያል ግዛት ለ5 ዓመታት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል። እናታቸው ማክጊል ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር ሲሉ ነው ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ካናዳ ያቀኑት።

የኮሌጅ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአብዛኛው የጥቁሮች ነው በሚባለው ዋሺንግተን በሚገኘው ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ነው።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ሲናገሩ እንደተደመጡት ከአውሮፓውያኑ 1959 ጀምሮ በወታደራዊ አካዳሚው ያሳለፏቸው እምስት ዓመታት ወታደዊ እና የአመራር ክህሎት እንዲያዳብሩ አድርጓቸዋል።

ትራምፕ ወደ ቪየትናም ጦርነት ሳይዘምቱ የቀሩት አጥንታቸው ላይ በነበረ ችግር ምክንያት መሆኑ ይነገራል።

ካማላ ሀሪስ በ22 ዓመታቸው በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ፤ ትራምፕ በ18 ዓመታቸው በኒው ዮርክ ወታደራዊ አካዳሚ

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, ካማላ ሃሪስ በ22 ዓመታቸው በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ፤ ትራምፕ በ18 ዓመታቸው በኒው ዮርክ ወታደራዊ አካዳሚ

ሃሪስ ገና ከልጅነታቸው ነው የሲቪል መብቶችን እንቅስቃሴን ከእናታቸው ጎን ሆነው ሲከታተሉ ያደጉት። በየዓመቱ የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር የነፃነት ቀን ሲከበር ቀርተው አያውቁም።

ከፔንሲልቬኒያ ዋርተን ስኩል ድግሪያቸውን ያገኙት ትራምፕ አባታቸውን ተክተው የቤተሰቡን ግዙፍ ሀብት እንደሚያስተዳድሩ ተስፋ የተጣለባቸው ከታላቅ ወንድማቸው ሞት በኋላ ነው።

ሃሪስ በማርቲን ሉተር ኪንግ መታሰቢያ ሰልፍ ላይ በ2004፤ ትራምፕ ደግሞ በ1987 ቢሯቸው ውስጥ የተነሱት ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሃሪስ በማርቲን ሉተር ኪንግ መታሰቢያ ሰልፍ ላይ በ2004፤ ትራምፕ ደግሞ በ1987 ቢሯቸው ውስጥ የተነሱት ፎቶ

ሃሪስ ወደ ካሊፎርኒያ ተመልሰው በግዛቷ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ እያደጉ መጡ። የካሊፎርኒያ ዐቃቤ ሕግ ሳሉ ነው በአውሮፓውያኑ 2016 በተደረገው ምርጫ የሴኔት ተወካይ ለመሆን ተወዳድረው ያሸነፉት።

እሳቸው ኮንግረስ ሲገቡ ትራምፕ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝደንት ለመሆን እየተፎካከሩ ነበር። ያሸንፋሉ የሚል ትልቅ ግምት ያልተሰጣቸው ትራምፕ ሂላሪ ክሊንተንን በመርታት ነበር ወደ ዋይት ሐውስ አቀኑ።

ከሦስት ዓመታት በኋላ ሃሪስ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው እንዲወዳደሩ በወቅቱ ፕሬዝደንት በጆ ባይደን ተመረጡ። ሁለቱ ተጣምረው ትራምፕ እና ማይክ ፔንስን በመርታት ዋይት ሐውስን ተረከቡ።

ካማላ ሃሪስ በ2021 ምክትል ፕሬዝደንት፣ ትራምፕ በ2017 ፕሬዝደንት ሆነው ቃለ-መሐላ ሲፈፅሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካማላ ሃሪስ በ2021 ምክትል ፕሬዝደንት፣ ትራምፕ በ2017 ፕሬዝደንት ሆነው ቃለ-መሐላ ሲፈፅሙ

የትራምፕ የምርጫ ዘመን ማብቂያ እና የባይደን እና ሃሪስ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በኮቪድ ወረርሽኝ እና በተለያዩ አመፆች የታጀቡ ነበሩ።

በተለይ በሚኒያፖሊስ ፖሊስ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ መግደሉን ተከትሎ በመላው አሜሪካ ከባድ አመፅ ተቀስቅሶ ነበር።

ካማላ ሃሪስ እና ዶናልት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካማላ ሃሪስ እና ዶናልት ትራምፕ

ሃሪስ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ተፅዕኖ ለመፍጠር ተቸግረው ነበር። ነገር ግን ጎልተው መውጣት የቻሉት በ2022 የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕገ-መንግሥታዊው ፅንስ የማቋረጥ መብትን ሲከለክል ነው።

ፕሬዝደንት ባይደን ፅንስ የማቋረጥ መብትን በተመለከተ የዋይት ሐውስን ዘመቻ እንዲመሩ ምክትላቸው ሃሪስን ወደፊት ማምጣት ጀመሩ።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በአብዛኛው ወግ አጥባቂ እንዲሆኑ መንገድ የጠረጉት ትራምፕ ናቸው። ይህ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ፅንስ ማቋረጥን በተለመከተ ጠበቅ ያለ አቋም እንዲይዝ አድርጎታል።

ትራምፕ በፕሬዝደንታዊ ጽህፈት ቤት (ኦቫል ኦፊስ) ቆይታቸው ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ራሳቸው ያገለሉ ሲሆን የስደተኞች ቁጥር እንዲቀንስም ሲጥሩ ቆይተዋል።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ፊርማ ሲያኖሩ ካማላ ሀሪስ ከኋላቸው ቆመው፤ ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ዋይት ሐውስ ሆነው ስልክ ሲደውሉ

የፎቶው ባለመብት, White House / Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ፊርማ ሲያኖሩ ካማላ ሀሪስ ከኋላቸው ቆመው፤ ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ዋይት ሐውስ ሆነው ስልክ ሲደውሉ

ሃሪስ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጓዙት ወደ ጓቲማላ ነው። ወደዚያ ያቀኑት ሜክሲኮን ተጠቅመው ከላቲን አሜሪካ በደቡባዊ የአሜሪካ ድንበር በኩል የሚመጡ ስደተኞችን ጉዳይ አንድ ለማለት ነው።

እሳቸው ምክትል ፕሬዝደንት ሳሉ በዩክሬን እና ጋዛ ውስጥ ጦርነት ተቀስቅሷል። የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን ነቅለው የወጡትም በባይደን ዘመነ መንግሥት ነው።

ትራምፕ ሥልጣና ከያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት በሳዑዲ አረቢያ ነው።

ትራምፕ የሚከተሉት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አሜሪካ በሌሎች ሀገራት ጦርነት ውስጥ እጇን ከማስገባት እንድትቆጠብ የሚሰብክ ነው።

ሃሪስ ሥልጣን ከየዙ በኋላ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በጓቲማላ ሲያደርጉ፤ ትራምፕ ደግሞ በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝታቸው አድርገዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images / Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሃሪስ ሥልጣን ከየዙ በኋላ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በጓቲማላ ሲያደርጉ፤ ትራምፕ ደግሞ በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝታቸው አድርገዋል

የሃሪስ ባል ዳግ ኤምሆፍ ይባላል። ዳግ ሚስታቸውን ወክለው በተለያዩ አካባቢዎች የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ናቸው።

ኤምሆፍ ከጀመሪያ ትዳራቸው ሁለት ልጆች ያፈሩ ሲሆን፣ አሁን ከሃሪስ ጋር ይኖራሉ። ልጆቻቸው ኮል እና ኤላ ይባላሉ።

የዶናልድ ትራምፕ ቤተሰብ አባላት በፖለቲካ ሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው። የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ግን በ2024 የምርጫ ቅስቀሳቸው ብዙም ሲሳተፉ አልተስተዋሉም።

ትራምፕ ከመጀመሪያ ሚስታቸው ኢቫና ሦስት ልጆች አሏቸው። ዶናልድ ጁኒዬር፣ ኢቫንካ እና ኤሪክ። ከሁለተኛ ሚስታቸው ደግሞ ቲፋኒን አፍርተዋል። ትራምፕ ከአሁኗ ሚስታቸው ሜላኒያ አንድ ወንድ ልጅ አላቸው።

ካማላ ሃሪስ ከባለቤታቸው እና ልጆቻቸው ጋር፤ ዶናልት ትራምፕ ከወቅቱ ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Alamy / AP

የምስሉ መግለጫ, ካማላ ሃሪስ ከባለቤታቸው እና ልጆቻቸው ጋር፤ ዶናልት ትራምፕ ከወቅቱ ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው ጋር

ሃሪስ የ2024 የአሜሪካ ምርጫን የተቀላቀሉት አርፍደው ነው። ፕሬዝደንት ባይደን ራሳቸውን ከምርጫው በማግለላቸው ነው ዲሞክራቲክ ፓርቲ እሳቸውን ያጨው።

በዚህም የመጀመሪያዋ ጥቁር እና እስያዊት-አሜሪካዊት ሴት ዕጩ ፕሬዝደንት በመሆን በታሪክ ተመዝግበዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ ከፓርቲያቸው ዕጩነት በማግኘት ነው እየተወዳደሩ ያሉት። ይህ ብዙም አልተለመደም።

ትራምፕ ዕጩነታቸውን የተቀበሉት የግድያ ሙከራ በተደረገባቸው ሰሞን ስለነበር ጆሯቸውን በፋሻ ጠቅልለው ነበር በሪፐብሊካኖች ጉባኤ ላይ የቀረቡት።

ካማላ ሀሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ ከፓርቲዎቻቸው ዕጩነት ሲቀበሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters / EPA-EFE

የምስሉ መግለጫ, ካማላ ሀሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ ከፓርቲዎቻቸው ዕጩነት ሲቀበሉ