የአሜሪካ ምርጫ መጻኢ ዕጣ ፈንታቸውን ጥያቄ ውስጥ የከተተው አፍሪካውያን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በመጪው ሳምንት ጥቅምት 26/ 2017 ዓ.ም የሚደረገው የአሜሪካ ምርጫ የአፍሪካውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መጻዒ ዕጣ ፈንታን የሚወስን ይሆናል።
በአሜሪካ ጥገኝነት ጠያቂ ከሆኑት አንዱ የሆነው የኮንጎ ዜግነት ያለው የ38 ዓመቱ ዶክተር ያቭአስ ካዱሊ “ደኅንነት እንሻለን” ይላል።
ዶክተሩ ለሦስት አስርት ዓመታት በጦርነት ከምትናጠው አገሩ ሕይወቱን ለማዳን ሸሽቶ ነው አሜሪካ የደረሰው።
ካሎንጌ በምትባል ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት እየሰጠ በነበረበት ወቅት ታግቶ ስቃይ እና እንግልት ደርሶበታል።
የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ የሆነው ዶክተር ካዱሊ ታጣቂ ቡድኖች የሚያደርሷቸውን ግድያዎች እና መድፈሮችን በመቃወም የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ከሆኑት ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጌ እና ሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ሰልፎችን አድርገዋል።
በወቅቱ አገሪቱን ያስተዳድር የነበረው የጆሴፍ ካቢላ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ አልቻለም በሚልም ተችተዋል።
በዚህም ምክንያት ባልታወቁ ታጣቂዎች ዒላማ ሆኗል።
የህክምና ባለሙያው እና የሥራ ባልደረቦቹ አገልግሎት ከሚሰጡበት ሆስፒታል ታግተው ተወስደው ድብደባ፣ እንግልት እና የሞት ማስፈራሪያዎች ደርሶባቸዋል። ከአጋቾቹ በሁለተኛው ቀን ማምለጥ ቢችልም ሕይወቱን ለማትረፍ መሰደድ እንዳለበት ወሰነ።
እናቱን እና ትንሹን ልጁን ትቶ የስደት መንገዱን ጀመረ። አሜሪካ እስኪደርስ ድረስ አምስት ዓመት ወስዶበታል። በጎረቤት ሩዋንዳ አልፎ ወደ ኩባ፣ ኢኳዶር እና ኒካራጓ በመብረር በመጨረሻም በአውሮፓውያኑ 2019 አሜሪካ ለመግባት ሜክሲኮ ድንበር ደረሰ።
ቢያንስ ለአንድ ወር ያህል በድንበር ላይ በአነስተኛ ድንኳኖች ውስጥ የቆየ ሲሆን፣ ሁኔታውንም “ኢሰብዓዊ” ሲል ይጠራዋል።
ዶክተር ካዱሊ ተሳክቶለት ወደ አሜሪካ የገባ ቢሆንም ለአስራ አምስት ወራት ያህል በእስር ላይ መቆየቱን ይናገራል። አሁን በቨርጂኒያ ግዛት በህክምና ቴክኒሻንነት እያገለገለ ሲሆን የጥገኝነት ጥያቄውን መልስ እየተጠባበቀ ይገኛል።
ዶክተር ካዱሊ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በሜክሲኮ ድንበር በኩል ወደ አሜሪካ በየዓመቱ ከተጓዙ በሺዎች ከሚቆጠሩ ስደተኞች አንዱ ነው። በድንበር በኩል የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።

በአሜሪካ ምርጫ የቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት ስደት ዋነኛ ጉዳይ ነው። ሁለቱም ዕጩ ፕሬዚዳንቶች የዲሞክራቷ ካማላ ሃሪስም ሆኑ የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ በድንበር በኩል የሚገቡ ስደተኞችን ማስቆም ዋና ተግባራቸው እንደሚሆን ቃል ገብተዋል። በዚህም ምክንያት አፍሪካውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ሕዝቡ ፊቱን ሊያዞርብን ይችላል የሚል ስጋት ገብቷቸዋል።
“ፖለቲከኞቻችን ያለንበትን ሁኔታ ወንጀል ሲያደርጉት እና ማኅበረሰባችንንም ከሰውነት ሲያወርዱት እየሰማን ነው። መጪው ዕጣ ፈንታችንን የሚወስኑት እነዚህ ፖለቲከኞች ናቸው” በማለት ዶክተር ካዱሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ወደ 13 ሺህ የሚጠጉ አፍሪካውያን ስደተኞች በሜክሲኮ ድንበር በኩል ገብተው መመዝገባቸውን የአሜሪካ የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ መረጃ ያሳያል።
ይህ አሃዝ ባለፈው ዓመት በአራት እጥፍ አድጎ ወደ 58 ሺህ ደርሷል። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በበኩሉ በድንበር በኩል ከሴኔጋል፣ ከሞሪታንያ እና ከጊኒ የሚመጡ የምዕራብ አገራት ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ ማሳየቱን ነው።
ከሁለት ዓመታት በፊት ከሴኔጋል የመጡ ስደተኞች ቁጥር 773 የነበረ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት 13 ሺህ 224 ማሻቀቡ ሪፖርት ተደርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሴኔጋል - ኒካራጓን ተሻግሮ በሜክሲኮ በኩል የሚደረገው የስደት ጉዞ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ቲክቶክን ጨምሮ በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ብዙ ይባልለታል።
ባለፈው ዓመት 140 የሴኔጋል ስደተኞች የሜክሲኮን ድንበር ተሻግረው አሜሪካ ከገቡ በኋላ ተባረው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል።
በአገራቸው ያሉ መሳደዶችን ሸሸተው፣ ፈታኝ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ እና በሌሎች ሁኔታዎች ምክንያት ወደ አሜሪካ እንደሚመጡ ‘ማይግሬሽን ፖሊሲ’ የተሰኘ ተቋም ሠራተኛ የሆኑት ካትሊን ቡሽ ጆሴፍ ይናገራሉ።
ሆኖም በአሜሪካ ውስጥ ጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘት በተለይም ለአፍሪካውያን ስደተኞች ፈታኝ ነው።
ስደተኞች ቋንቋን አቀላጥፎ አለመናገር፣ የሚቀበላቸው እና የሚደግፋቸው ማኅበረሰብ ማጣት እንዲሁም ስለ አፍሪካ ጦርነቶች ግንዛቤ ማነስ ለአፍሪካውያን ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸውን የበለጠ ከባድ እንደሚያደርገው ካትሊን ያስረዳሉ።
የጥገኝነት ጥያቄያዎችን የሚያዩ “ዳኞች እና ጠበቆች አብዛኛውን ጊዜ ሸሽተው የሚመጡባቸውን የአፍሪካ አገራት ያለውን ሁኔታ በቅጡ አያውቁትም” ይላሉ።
ከአሜሪካ ተባረው ወደ አገራቸው ለሚመለሱ ስደተኞች ሁኔታው የከፋ ነው።
ከአሜሪካ ድንበር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉ ካሜሮናውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች መታሰር፣ መሰቃየት እና መደፈር የመሰሉ አሰቃቂ ጥቃቶች እንደደረሰባቸው ‘ሂውማን ራይትስ ዋች’ ከሁለት ዓመት በፊት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።
አፍሪካውያን ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በአሜሪካ የሚደግፈው ‘አፍሪካን ኮሙዩኒቲስ ቱጌዘር’ የተሰኘ ተቋም የፌደራል ፖሊሲ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ኒልስ ኪኑአኒ በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት በስደተኞች ዙሪያ የሚነገሩ ትርክቶች በማኅበረሰቡ ላይ “ከባድ ፍርሃት” ፈጥሯል ይላሉ።
“በርካቶች በፍርሃት ላይ ናቸው። የስደተኞች ፕሮግራሞች ጥቃቶች ሊደርስባቸው ይችላል የሚል ስጋት ነግሷል።”
የእሳቸው ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ተሟጋቾች ወደ አገራቸው እንዳይባረሩ የሰጉ አፍሪካውያን ስደተኞችን ለመርዳት ሕጋዊ ከለላዎችን እየጠየቁ ይገኛሉ።
አንዱ አማራጭ ሰብዓዊ ምህረት (ሂውማኒታሪያን ፓሮል) የሚባለው ሲሆን፣ በዚህም በአገራቸው ጦርነቶችን እና የተፈጥሮ ቀውሶችን ጨምሮ ሌሎች መከራዎችን ሸሽተው ለመጡ የውጭ ዜጎች ሕጋዊ ጥበቃ የሚሰጥ ነው።
ለአደጋ የተጋለጡ የውጭ አገራት ዜጎች በአሜሪካ በጊዜያዊነት እንዲኖሩ እንዲሠሩ የሚፈቅድ ሲሆን፣ እስካሁን የዩክሬን፣ የኩባ፣ የኒካራጓ፣ የሄይቲ፣ የቬንዙዌላ እና የአፍጋኒስታን ዜጎችን ያካትታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ እና በየትኛውም የአፍሪካ አገራት መካከል ምንም ዓይነት የሰብዓዊነት የምህረት ጥበቃ ፕሮግራም የለም። በዩክሬን ጦርነቱ በተከሰተ በጥቂት ሳምንታት ግጭቱን ሸሽተው ወደ አሜሪካ የመጡ ስደተኞች በዚህ ፕሮግራም ጥበቃ ማግኘታቸው ቅሬታ እንዳስነሳ ኪኑአኒ ይናገራሉ።
የዩክሬን ስደተኞች በእንደዚህ ዓይነት ፕሮግራም ለመታቀፍ መሟገት ያላስፈለጋቸው ሲሆን “እንደ ሱዳን ካሉ በጦርነት ከሚናወጡ አገራት ለመጡ ስደተኞች ከፍተኛ ሙግት ገብተናል” ይላሉ ኪኑአኒ።
የሱዳን ጦርነት ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን ሕዝብ አፈናቅሏል። የዲሞክራትም ሆነ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩዎች ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞችን መቆጣጠር እና የድንበሩን ሁኔታ በዘላቂነት መፍታት በምረጡኝ የቅስቀሳ ዘመቻዎች ቃል የገቡባቸው ጉዳዮች ናቸው።
ዶናልድ ትራምፕ ከተመረጡ “በአሜሪካ ታሪክ ታላቅ የተባለውን ስደተኞችን ወደ አገራቸው የመመለስ ተግባርን” ያከናውናሉ።
በተጨማሪም የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸውን የሚያስታውሱ የድንበር ፖሊሲዎችን ወደ ነበሩበት እንደሚመልሱ የሪፐብሊካን ብሔራዊ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ አትቷል።
የዲሞክራትዋ ዕጩ እና ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት በአሜሪካ ምክር ቤት ተቀባይነት ያላገኘውን የሁለቱ ፓርቲዎች የድንበር ደኅንነት ረቂቅ እንደሚያመጡት ቃል ገብተዋል።
ረቂቁ “ፈጣን እና ፍትሃዊ” የጥገኝነት ጠያቂዎችን ሂደት ያረጋግጣል ሲል ዋይት ሐውስ ቢገልጽም ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትችት ገጥሞታል።
የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በድንበር ላይ ያሉ ስደተኞችን በመመለስ እና በቁጥጥር ስር በማዋል ይታወቃል።
ባለፈው ዓመት በተላለፈ ትዕዛዝ መሠረት በሕገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸው ሳይታይ ባለሥልጣናቱ በፍጥነት የሚያስወግዱበትን መንገዶች አስቀምጧል።
ዶክተር ካዱሊ የጥገኝነት ጥያቄያው እስኪያገኝ ከ4 እስከ 10 ዓመት መጠበቅ ይኖርበታል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት አባቱ ቢያርፍም አገሩ ሄዶ መቅበርም እና እርሙን ማውጣት ባለመቻሉ ሐዘኑ ጥልቅ ነው። ቢሆንም አንድ ቀን ልጁ እና እናቱ ወደ አሜሪካ ይመጣሉ የሚል ተስፋው አለ።












