ኢላን መስክ ለመራጮች በነብስ ወከፍ 1 ሚሊዮን ዶላር መስጠቱ ለጊዜው ሕጋዊ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢሊየነሩ ኢላን መስክ ለተመዘገቡ መራጮች በነብስ ወከፍ 1 ሚሊዮን ዶላር መክፈሉ ለጊዜው ሕጋዊ ነው ሲሉ አንድ የፔንሲልቬኒያ ዳኛ ወሰኑ።
የዕጩው ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ የሆነው መስክ አሜሪካ ፓክ በተሰኘው ፖለቲካዊ ድርጅቱ አማካይነት ለተመዘገቡ መራጮች የገንዘብ ሽልማት እየሰጠ ይገኛል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህ ድርጊት የምርጫ ሕጉን ይፃረራል ሲሉ ቢከራከሩም መስክ ይህን ያስተባብላል።
የፊላደልፊያ አቃቤ ሕግ ሎረንስ ክራስነር በያዝነው ሳምንት ኢላን መስክን የከሰሱ ሲሆን ግለሰቡ “ከምርጫው በፊት ከድርጊቱ ሊገታ ይገባል” ብለው ነበር።
ሐሙስ በዋለው ችሎት ዳኛ አንጀሎ ፎግሊየታ የፌዴራል ፍርድ ቤት ጉዳዩን እስኪመለከተው ድረስ ማስቆም እንደማይችሉ አሳውቀዋል። የፌዴራል ፍርድ ቤት በጉዳዩ ብይን መስጠት ካልፈለገ ግን ክሱ ወደ ግዛቲቱ ይመለሳል።
ሐሙስ ዕለት ከዋለው ችሎት በኋላ በኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ገፁ መልዕክት ያስተላለፈው ኢላን “የአሜሪካ ፍትሕ ለአሸናፊነት” የሚል መፈክር አሰምቷል።
ይህ ክስ በቀጣይ ማክሰኞ ከሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ በፊት ይቋጫል ተብሎ አይታሰብም።
መስክ ፊላደልፊያ በሚገኘው ፍርድ ቤት የነበረውን ችሎት በአካል ተገኝቶ አልተከታተለም።
ቢሊየነሩ በያዝነው የአውሮፓውያኑ ወር መባቻ ነው ወሳኝ በሚባሉ ግዛቶች እስከ ምርጫው ቀን ድረስ በየቀኑ ዕጣ ለሚደርሳቸው የተመዘገቡ መራጮች 1 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ሲል ቃል የገባው።
ሰባቱ በሚመጣው ምርጫ ወሳኝ የተባሉት ግዛቶች ፔንሲልቬኒያ፣ ጆርጂያ፣ ኔቫዳ፣ አሪዞና፣ ዊስኮንሲን፣ ሚሺጋን እና ኖርዝ ካሮላይና ናቸው።
በእነዚህ ወላዋይ በሚባሉ ግዛቶች ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ እና ተቀናቃኛቸው ዲሞክራቷ ካማላ ሀሪስ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ችሎቱ በዋለበት ሐሙስ ዕለት የኖርዝ ካሮላይና ነዋሪ የሆኑ ዴሲ የተባሉ ግለሰብ 1 ሚሊዮን ዶላር ማሸነፋቸውን የኢላን መስክ አሜሪካ ፓክ ይፋ አድርጓል።
የ1 ሚሊዮን ዶላር ዕድለኛ ለመሆን ፈቃደኞች የግል መረጃቸውን ለምሳሌ አድራሻቸውን እና ስልክ ቁጥራቸውን ይፋ ማድረግ እና የአሜሪካ ሕገ-መንግሥትን እደግፋለሁ የሚል የፊርማ ማሰባሰቢያ ወረቀት ላይ መፈረም አለባቸው።
ኢላን መስክ ሕጋዊ ያልሆነ “ሎተሪ” ማውጣት ጀምሯል ተብሎ ነው የተከሰሰው። “ኢላን መስክ እና አሜሪካ ፓክ የፊላደልፊያ ዜጎች የግል መረጃቸውን ሰጥተው ፖለቲካዊ አቋማቸውን እንዲያሳውቁ እና በምትኩ 1 ሚሊዮን ዶላር እንዲያገኙ ቃል እየገቡ ነው” ይላል ክሱ።
“ይህ ሎተሪ ነው። በእርግጠኝነት የማያጠራጥር ሕጋዊ ያልሆነ የሎተሪ አወጣጥ ነው።”
የኢላን መስክ ጠበቃዎች ከሳሹ ያቀረቡት ክስ ውሀ የሚያነሳ አይደለም ብለው መከራከራቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
መስክ ከሳሻቸው ክራስነርን በኤክስ ገፃቸው መዝለፋቸውን ተከትሎ ሰውዬው ብዙ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል። ችሎቱም በርከት ባሉ ፖሊሶች ሲጠበቅ ነበር።
የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር የኢላን መስክ ድርጊት የፌዴራል የምርጫ ሕግጋትን ሊጥስ ይችላል ሲል ለቢሊየነሩ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መላኩ ይታወሳል።
ፍርድ ቤት ኢላን መስክን ጥፋተኛ ሆኖ ካገኘው 10 ሺህ ዶላር እና እስከ 5 ዓመት በእስር ሊቀጣው እንደሚችል ይጠበቃል።
ለዕጩው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ድጋፉን እየገለጠ ያለው መስክ ሽልማቱን ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች የግድ ሪፐብሊካን መሆን የለባቸውም የመምረጥም ግዴት አልተጫነባቸውም ብሏል።












