ኬንያውያን የአርሰናል ደጋፊዎች ከድል በኋላ ለምስጋና በቤተክርስቲያን መሰብሰባቸው አነጋጋሪ ሆነ

ኬንያውያን የአርሰናል ደጋፊዎች ቡድናቸው ድል ከተቀዳጀ በኋላ በቤተክርስቲያን ተሰባስበው ለቡድናቸው ድል ፈጣሪን ማመስገናቸው መነጋገሪያ ሆነ።

ወደ ቤተክርስቲያን አምርተው ልዩ የፀሎት ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል። በዚህም ቡድናቸው በማሸነፉ ለፈጣሪ ምስጋና አድርሰዋል።

ቅዳሜ በተካሄደው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ አርሰናል ከክሪስታል ፓላስ ጋር በነበረው ጨዋታ 5 ለ 0 በሆነ ውጤት ነበር ያሸነፈው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የቡድኑ ደጋፊዎችን የምሥጋና ሥነ ሥርዓት ያደነቁ የመኖራቸውን ያህል፣ በርካታ የሚያሳስቡ እና የሚያነጋግሩ ጉዳዮች እያሉ ለአንድ የእግር ኳስ ቡድን እንዲህ መጨነቃቸውን የተቹ አሉ።

በኬንያ የአርሰናል ደጋፊዎች በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የአርሰናልን መለያ ለብሰው በቤተክርስቲያን የተነሷቸውን ፎቶዎች ለጥፈዋል።

በእሁድ የፀሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ሲዘምሩና ቡድናቸው ላሳየው ድንቅ ብቃት ፈጣሪን ሲያመሰግኑም ነበር።

የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ካነሳ ረጅም ጊዜ የሆነው አርሰናል ይህ የውድድር ወቅት ከጀመረ በኋላ በደረጃ ሠንጠረዡ ላይ በመሪነት ለሳምንታት ለመቆየት ቢችልም በተከታታይ ነጥብ በመጣሉ ቦታውን ለመልቀቅ ተገዶ ነበር።

በቅዳሜው ጨዋታ በበርካታ ግቦች ተቀናቃኙን ለማሸነፍ የቻለው አርሰናል አሁን ሊቨርፑል እና ሲቲን ተከትሎ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ይህም ውጤት ነው ስጋት የገባቸውን የቡድኑን ደጋፊዎች አስደስቶ በቤተክርስቲያን ተሰብስበው ፈጣሪያቸውን እንዲያመሰግኑ ያደረጋቸው።

የአርሰናል ደጋፊዎች ከድላቸው በተጨማሪ ቡድናቸው በቀጣይ ጨዋታዎቹም እንዲያሸንፍ ፀሎት አድርገዋል።

አርሰናል አሁን ላይ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ተመጣጣኝ ነጥብ አለው። ሊቨርፑል በአምስት ነጥብ ይበልጠዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የአርሰናል ደጋፊዎች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመታየታቸው የተለያየ አስተያየት ገጥሞታል። አንዳንዶች ደጋፊዎቹን ተሳልቀውባቸዋል።

አርሰናል ከዚህ በፊት ሦስት ጨዋታ በተከታታይ ተሸንፏል። ኬንያውያን የአርሰናል ደጋፊዎች የተለያዩ ማኅበራት አሏቸው። በጋራ ከመፀለይ በተጨማሪ የበጎ አድራጎት ሥራዎችንም ያከናውናሉ።