ግብፅ ጣልቃ እንድትገባ ከተጠየቀች ከሶማሊያ ጎን እንደምትሰለፍ አል ሲሲ ተናገሩ

ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው ሶማሊያ ጥያቄ ካቀረበች ከጎኗ ለመቆም ጣልቃ እንደምትገባ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ተናገሩ።

ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በባሕር በር አጠቃቀም ዙሪያ የመግባብያ ስምምነት ላይ ከደረሰች በኋላ ሶማሊያ ተቃውሞ ያቀረበች ሲሆን፣ ግብፅም በተደጋጋሚ የሶማሊያን አቋም ደግፋ አስተያየት ስትሰጥ ቆይታለች።

የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ከግብፅ መንግሥት በቀረበላቸው ግብዣ ወደ ካይሮ በመጓዝ ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር ከተወያዩ በኋላ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው ሁለቱ አገራት ከኢትዮጵያ አንጻር በጋራ እንሚቆሙ የተገለጸው።

ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ አገራቸው በሶማሊያም ሆነ በፀጥታዋ ላይ ምንም አይነት የደኅንነት ስጋት እንዲፈጠር እንደማትፈቅድ እና ለዚህም ግብፅ ጣልቃ እንድትገባ ከተጠየቀች ከሶማሊያ ጎን ትሰለፋለች ሲሉ ተናግረዋል።

አል-ሲሲ ይህንን ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረውን አስተያየት ከሰጡ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ስምምነቱ በሶማሊያ ላይ የደኅንነት ስጋት የሚፈጥር አለመሆኑን ገልጸው፤ በቀጠናው ያሉ አንዳንድ ኃይሎች አጀንዳ በአፍሪካ ቀንድ ቀውስ መፍጠር ነው ብለዋል።

ከሦስት ሳምንታት በፊት ይፋ በተደረገው የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ለምታገኘው የባሕር ጠረፍ፤ በምላሹ ሶማሊያ እንደ አንድ ግዛቷ ለምትመለከታት ሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን ትሰጣለች ተብሏል።

ይህ ታዲያ ሶማሊያን በእጅጉ ያስቆጣ ሲሆን፣ በሉዓላዊነቷ ላይ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑን በመግለጽ ስምምነቱን አጥብቃ ተቃውማለች።

ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በቀጣናው ከሚገኙ መሪዎች ጋር ተከታታይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ወደ አሥመራ እና ካይሮ ጉዞዎችን አድርገዋል።

“ግብፅን አትሞክሯት . . .”

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከአል-ሲሲ በቀረበላቸው ግብዣ ወደ ካይሮ ካቀኑ በኋላ ከፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች እና በቀጠናዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት አስታውቋል።

መሪዎቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ “ግብፅ የትኛውም አገር ሶማሊያንም ሆነ ደኅንነቷን ስጋት ውስጥ እንዲጥል አትፈቅድም” ካሉ በኋላ “ግብፅን አትሞክሯት፤ በተለይ ደግሞ ወንድም አገር [ሶማሊያ] ከጎኑ እንቅድንቆም ከጠየቀን” በማለት አገራቸው ከሶማሊያ ጋር እንደምትቆም አሳውቀዋል።

ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገባችው ሶማሊያ ጎን እንደምትቆም ስትገልጽ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም፣ በካይሮ በኩል ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ ግልፅ ዛቻ አዘል ጠንካራ አስተያየት ሲሰማ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከአዲስ አበባ ጋር የሻከረ ግንኙነት ያላት ካይሮ፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የመግባቢያ ሠነዱ መፈረሙን ተከትሎ “ከሶማሊያ ጎን ለመቆም ያላትን ጠንካራ አቋም” ገልጻ ነበር።

ፕሬዝዳንት አል ሲሲ እሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት “ግዛትን በኃይል የመቆጣጠር ሙከራ” ብለው ከገለጹ በኋላ፤ “ለኢትዮጵያ ያለኝ መልዕክት . . . መሬትን ለመቆጣጠር መሞከር ማንም የማይስማማበት ጉዳይ ነው” ብለዋል።

አል-ሲሲ ሶማሊያ የአረብ ሊግ አባል አገር መሆኗን አስታውሰው በሊጉ ቻርተር መሠረት ሶማሊያ ሊገጥማት ከሚችለው የደኅንነት ስጋት የመጠበቅ መብት አላት ሲሉም ተናግረዋል።

“የትኛውም አገር በሶማሊያን ደኅንነት ላይ ስጋት እንዲደቅን ወይም ግዛቷን እንዲጥስ አንፈቅድም። በግልጽ የምናገረው ነገር፣ የግብፅ ወንድም አገርን ማንም መዳፈር የለበትም፤ በተለይ ደግሞ ወንድሞቻችን ከጎናቻው እንድንሰለፍ ሲጠይቁን” ብለዋል ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ።

የአል-ሲሲ አስተያየትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደኅንንት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ላይ የደኅንነት ስጋት የምትደቅን አገር ሳትሆን ለሶማሊያ ጥበቃ ለማድረግ ወታደሮቿን ማሰማራቷን አስታውሰዋል።

ሁለቱ አገራት ከጉርብትናቸው በላይ አንድ ቋንቋ እና ባሕል የሚጋሩ ሕዝቦች እንዷላቸው አስታውሰው፤ “እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በችግሯ ጊዜ ለሶማሊያ ድጋፍ ሳያደርጉ የቆዩ አንዳንድ ኃይሎች እራሳቸውን እውነተኛ ወዳጅ አድርገው ለማሳየት እየሞከሩ ነው” ብለዋል።

በግልጽ ስም ባልጠሩበት ሁኔታም “የሚያነሳሳቸው ከሶማሊያ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ያላቸው ጥላቻ እንደሆነ ግልጽ ነው” ብለዋል አምባሳደር ሬድዋን በኤክስ ገጻቸው።

አምባሳደር ሬደዋን በቀጠናው ያሉ አንዳንድ ኃይሎች አጀንዳ በአፍሪካ ቀንድ ቀውስ መፍጠር ነው ካሉ በኋላ ኢትዮጵያ ውጥረት ከሚያባብሱ መግለጫዎች እና ንግግሮች ይልቅ ቀጣይነት ያለው ንግግር ጠቃሚ ነው ብላ ታምናለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት በተመለከተ ባለፈው ሳምንት የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት የልማት ድርጅት (ኢጋድ) እና የአረብ ሊግ በተናጠል ስብሰባ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ያልተሳታፈችበት የኢጋድ ስብሰባ አገራቱ ውጥረቱን በማርገብ ንግግር እንዲያደርጉ ጥሪ ሲያቀርብ፣ የአረብ ሊግ ደግሞ ኢትዮጵያን በማውገዝ ለሶማሊያ ድጋፉን ገልጿል።