መከላከያ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚወጡ ዘገባዎች ዙሪያ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን እቅስቃሴ በተመለከተ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ዘገባ የሚሰሩትን አስጠነቀቀ።

ሠራዊቱ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሠራዊቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ “የመዘገብ ወይም የማራገብ አሉታዊ ሙከራዎች በአስቸኳይ ይቁሙ” ሲል አሳስቧል።

መከላከያ በመግለጫው አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘገባዎች እና መረጃዎች አፍራሽ ውንጀላን ባልተገባ መልኩ እየተቀባበሉት መሆኑን አስተውለናል ብሏል።

የሕዝብ ድጋፍ እና ተሳትፎ መከላከያ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ወሳኝ መሆኑን በፅናት ያምናል ያለው መግለጫው፤ ያለበቂ መረጃ የጠላትን እንቅስቃሴ መዘገብ ግን የሕዝብን የዕለት ተዕለት ኑሮ ያውካል ብሏል።

“ጠላት በዚህ ገባ፣ በዚህ ወጣ፤ የወገን ሠራዊት በዚህ ገባ፣ በዚህ ወጣ የሚለው ወሬ በፍፁም ዜና እና የዜና ትንታኔ ሊሆን አይችልም” ብሏል አገር መከላከያ በመግለጫው።

ጦርነቱን እንዲዘግቡ ፍቃድ ከተሰጣቸው ውጪ በአገር ህልውና ላይ የተቃጣን ጦርነት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ገቢ ማስገኛነት ተቆጥሮ የልተረጋገጠ መረጃ ሳይኖር ወሬ ማናፈስ የሕዝብን መረጋጋት እንደሚነሳ እና የፀጥታ ኃይሎችን ተግባር እንደሚያውክ በመግለጫው ተመልክቷል።

የሠራዊታችን እንቅስቃሴ በተመለከተ ለሕዝብ ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እናሳውቃለን ያለው መከላከያ፤ “... በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የሠራዊታችንን እንቅስቃሴ በማሰራጨት ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት እንዳሉ አይተናል። ይህ ድርጊት በሠራዊታችን የግዳጅ አፈፃፀም ላይ ምንም አዎንታዊ ተፅኖ ሊኖረው አይችልም” ብሏል።

አገር መከላከያ የተዛባ፣ ተገቢና የማይመለከታቸውን ዘገባ የሚዘግቡ የማኅበራዊ ሚዲያ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ ያሳሰበ ሲሆን ከደርጊታቸው በማይታረሙት ላይ ግን ሕጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል።

“ይህንን ተግባር በግዴለሽነት ወይም በማን አለብኝነት የሚቀጥሉና የማይታረሙ ካሉ መከላከያ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ ከመሆኑም በላይ የሠራዊቱን ምስጢር በመንዛት፣ የጠላትን አጀንዳ በማራገብ የአገር ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉትን እንደ አስፈላጊነቱ የወንጀል ክስ በመመስረት ተጠያቂ ለማድረግ እንደምንገደድ በጥብቅ እናሳውቃለን” ብሏል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ እየተካሄደ ካለው ወታደራዊ ፍጥጫ ጋር በተያያዘ በመንግሥትና በህወሓት ስላሉ እንቅስቃሴዎች የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ የሚገኙ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚወጡትን መረጃዎች ማጣራት አዳገች ነው።

በሁለቱም ወገኖች መረጃዎችን ለማጣራት ከመገናኛ ብዙኃን በኩል ለሚቀርቡ ማብራሪያዎች እና ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል።