ተመድ በድርቅ ምክንያት በአፍሪካ ቀንድ በርካታ ሕጻናት ሊሞቱ ይችላሉ አለ

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በድርቅ ምክንያት በአፍሪካ ቀንድ እና በሳህል ቀጠና ሕጻናት “በከፍተኛ ቁጥር ሊሞቱ ይችላሉ” አለ።

ድርጅቱ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የሕጻናቱን ሕይወት ለመታደግ አስቸኳይ የሆነ ድጋፍ ያስፈልጋል ሲል አሳስቧል።

ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በሶማሊያ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የማያጋኙ ሰዎች ቁጥር ከ9.5 ሚሊዮን ወደ 16.2 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ገልጿል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረቱ በሳህል ቀጠና መኖሩን የገለጸው የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ፤ በቀጠናዎቹ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት እንዲኖር እና የውሃ ወለድ በሽታ ተጋላጭነትን ጨምሯል ብሏል።

“ውሃ ሳይኖር ሲቀር ወይም ንፅህናው የተጠበቀ ካልሆነ በሕጻናት ላይ ያለው አደጋ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል” ሲሉ የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ሩሴል ተናግረዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት አካል የሆነው ዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር በአፍሪካ ቀንድ እና በሳህል አካባቢ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት ለከፋ አደጋ ለመጋለጥ በአንድ በሽታ ብቻ መጠቃት ይበቃቸዋል ብለዋል።

በቡርኪና ፋሶ፣ በቻድ፣ በማሊ፣ በኒጀር እና በናይጄሪያ ድርቅ፣ ግጭት እና የደኅንነት እጦት ለውሃ አቅርቦት ችግር ምክንያት መሆናቸው ተመልክቷል።

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት አሃዝ ከሆነ 40 ሚሊዮን ሕጻናት ከከፍተኛ እስከ እጅግ ከፍተኛ ለሆነ የውሃ አቅርቦት እጥረት ተጋላጭ ናቸው።

በሳህል ቀጠና ያሉ ሕጻናት ደግሞ ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል በከፋ ሁኔታ ንፅህናው ባልተጠበቀ ውሃ እና በንፅህና አጠባበቅ ጉድለት ምክንያት ሕይወታቸው ያልፋል።

ኢትዮጵያ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅ የሕጻናት መርጃ ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በአፍሪካ ቀንድ ባሉ አገራት ውስጥ አብዛኛው ሰው የውሃ አቅርቦት የሚደርሰው በቦቴ መኪኖች ወይም በአህያ ጋሪዎች አማካይነት ነው።

ይሁን እንጂ በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ የውሃ ምንጮችን በማድረቁ የውሃ ዋጋ ዝቅተኛ ገቢ ላለው አብዛኛው ማኅብረሰብ የሚቀመስ አልሆነም ይላል።

ዩኒሴፍ ጥቅምት 2013 ዓ.ም. ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ ሰኔ ወር ላይ በኦሮሚያ ክልል የውሃ ዋጋ በእጥፍ ጨምሮ እንደነበረ፤ በሶማሌ ክልል ደግሞ የውሃ ዋጋ ጭማሪ 50 በመቶ መሆኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

የሕይወት አድን ሥራ

ዩኒሴፍ ይህን ቀውስ ለመቀልበስ በአፍሪካ ቀንድ እና በሳህል ቀጠና ተጋላጭ ለሆኑ ሕጻናት እና ቤተሰቦች ሕይወት አድን የሰብዓዊ እርዳታዎችን እና አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።

የአየር ጸባይ ለውጥን መቋቋም የሚችል የውሃ አቅርቦት፣ የግል ንፅህና አጠባበቅ አገልግሎት፣ የከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮ፣ ከፀሐይ ብርሃን የአሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕጻናትን መለየት እና ማከም ዩኒሴፍ ትኩረት ያደረገባቸው ተግባራት ናቸው።

ይሁን እንጂ ተቋሙ እነዚህን ተግባራት ለመፈጸም ከሚያስልገው ገንዘብ 3 በመቶውን ብቻ ማግኘቱን ገልጿል።

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ሩሴል መንግሥታት፣ ለጋሾች እና ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ይህን ቀውስ መግታት የሚቻለው ዘላቂ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ነው ብለዋል።