ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መውጫ መግቢያው ለተዘጋባቸው የጋዛ ነዋሪዎች ለመድረስ መከፈቱ የሚጠበቀው በር
ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ እርዳታ ጋዛን ከግብፅ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ ቆሞ ባለበት ሁኔታ ምግብ፣ ነዳጅ እና የመጠጥ ውሃ ጋዛ ውስጥ እየተሟጠጠ ስለመሆኑ የመንግሥታቱ ድርጅት አስጠንቅቋል።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደው ግጭት በተባባሰበት በአሁኑ ወቅት የዓለም መሪዎች እና የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች እጅግ አስፈላጊ የሆኑ አቅርቦቶችን ወደ ጋዛ ለማስገባት እየጠየቁ ነው።
ምግብ፣ ውሃ እና መድኃኒት የጫኑ 20 የሚሆኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከአርብ ጀምሮ በሚኖሩት ቀናት ወደ ጋዛ እንዲገቡ ይፈቅድላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የእርዳታ አግልግሎት ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ እንዳሉት 2.1 ሚሊዮን የሚሆኑ የጋዛ ነዋሪዎችን ለመደገፍ በየቀኑ 100 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መግባት አለባቸው።
ለጋዛ የሚያስፈልገው እርዳታ ለምን ዘገየ?
ሐማስ ጋዛን ከተቆጣጠረበት 2007 (እአአ) ጀምሮ አስራኤል እና ግብፅ ለደኅንነት ቁጥጥር በማለት ከግዛቲቱ እና ወደ ግዛቲቱ የሚደረጉ የሰዎች እና የሸቀጦች እንቅስቃን ገድበዋል።
ጋዛ የትኛውንም አይነት እንቅስቃሴ በሚያግዱ አጥሮች የተከበበች ሲሆን፣ ሦስት በጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው የመተላለፊያ በሮች ቢኖሩም ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ ከ1,400 በላይ ሰዎችን ከገደለ በኋላ ተዘግተዋል።
ለዚህም ምላሽ ከጥቃቱ እለት አንስቶ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት “ኤሌክትሪክ፣ ምግብ፣ ነዳጅ አይኖርም፤ ሁሉም ነገር ዝግ ነው” በማለት በጋዛ ላይ ሙሉ ከበባ መደረጉን ይፋ አድርገዋል።
በተጨማሪም እስራኤል በጋዛ ላይ እያደረገችው ባለው የአየር ድብደባ ቢያንስ 3,785 ሲገደሉ፣ ከ12,500 በላይ ነዋሪዎች መቁሰላቸውን የጋዛ ጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ከእስራአል ጋር የሚገኛኙት በሰሜናዊ ጋዛ ያለው የኤሬዝ እና በደቡብ የሚገኘው ኬሬም የድንበር መተላለፊያዎች ከእስከ ወዲያኛው መዘጋታቸው ተገልጿል።
ሦስተኛው እና ከግብፅ ጋር ጋዛን የሚያገናኛው የራፍህ መተላለፊያ አሁን እርዳታ ወደ ጋዛ ለማስገባት ዋነኛ መንገድ ነው። በመተላለፊያው መስመር ላይ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት ጉዳት በመድረሱ የጥገና ሥራ እየተከናወነ ነው።
ለጋዛ ስለሚቀርበው እርዳታ እስራኤል ምን አለች?
በሐማስ የታገቱት ዜጎቿ አስኪለቀቁ ድረስ አስራኤል በግዛቷ በኩል ወደ ጋዛ ማንኛውም አይነት እርዳታ እንዲያልፍ እንደማትፈቅድ አሳውቃለች።
መስከረም ወር መጨረሻ ላይ በሐማስ በተፈጸመው ጥቃት 16 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 203 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸውን የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል።
ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋር ውይይት ከተደገ በኋላ እስራኤል የተወሰነ እርዳታ ከግብፅ በራፋህ የድንበር መተላለፊያ በኩል ወደ ጋዛ እንዲገባ ፈቅዳለች።
ቢሆንም ግን፣ የሚቀርበው እርዳታን ሐማስ በየትኛውም መንገድ ሊጠቀምበት መሞከሩን የሚያሳዩ ምልክቶች ከታዩ እስራኤል እርምጃ እንደምትወስድ ባለሥልጣናቷ አስጠንቅቀዋል።
የራፍህ የድንበር መተላለፊያ የት ነው?
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደው ግጭት መባባሱን ተከትሎ የራፋህ የድንበር መተላለፊያ ወደ ጋዛ እርዳታ ለማስገባት ዋነኛው መስመር በመሆን ትኩረትን አግኝቷል።
ራፋህ በጋዛ ደቡባዊ ጫፍ ላይ የሚገኝ የመውጫ በር ሲሆን፣ ከጋዛ ለመውጣት በቀጥታ ከእስራኤል ጋር የማይገናኝ ብቸኛው መስመር ነው። በራፋህ በኩል ድንበሩ የሚዋሰነው ከግብፁ የሲናይ ባሕረ ገብ መሬት ጋር ነው።
ግብፅ በአሁኑ ጊዜ ከጋዛ ጋር ያላትን የራፋህ የድንበር መተላለፊያን በመክፈት የውጭ አገራት ፖስፖርት ያለውን ሰዎች ለማሳለፍ የሚያስፈልጋትን ዝግጅት እያደረገች ነው።
የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “በእኛ በኩል ያለው የራፍህ መተላለፊያ በይፋ ክፍት ነው” በማለት በመተላለፊያው ላይ የተፈጸመው የአየር ጥቃት መንገዱ ላይ ውድመት በማድረሱ ለእርዳታ አቅራቢ ተሽከርካሪዎች አስቸጋሪ ሁኔታን እንደፈጠረ ተናግረዋል።
የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ “አሁን ጋዛ ውስጥ እየሆነ ያለው ሲቪል ነዋሪዎች በግድ ወደ ግብፅ እንዲሰደዱ ማድረግ ነው፤ ይህ መፈቀድ የለበትም” በማለት ፍልስጥኤማውያን የተነሱለት ዓላማ እንዳይጠፋ ከግዛታቸው እንዳይወጡ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ግብፅ ለአስር ዓመታት ያህል በሲናይ በኩል ከገጠማት የጂሃዲስቶች ጥቃት አንጻር የመተላላፊያው ክፍት መሆን እስላማዊ ታጣቂዎች ወደ ግዛቷ የሚገቡበትን ዕድል ሊፈጠር ይችላል ብላ ትሰጋለች።
ወደ ጋዛ እርዳታ ማን ይልካል?
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስካሁን 3,000 ቶን የሚሆን እርዳታ ወደ ራፋህ መተላለፊያ አድርሷል። ከጋዛ ድንበር በአንድ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ምግብ፣ ነዳጅ እና መድኃኒቶችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ለማለፍ እየተጠባበቁ ነው።
የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣን የሆኑት ፊሊፔ ላዛሪኒ “አጋጥሞ የማያውቅ ሰብአዊ መቅሰፍት እየተከሰተ ነው” በማለት፣ ደኅንነቱ የተረጋገጠ የእርዳታ ማቅረቢያ መንገድ ካልተመቻቸ ጋዛ ውስጥ ያሉት መሠረታዊ አቅርቦቶች እያለቁ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የዓለም ጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ፤ መቀመጫውን ዱባይ ባደረገው ኢንተርናሽናል ሂዩማኒቴሪያን ሲቲ ጋር በተመተባበር በሰሜናዊ ግብፅ በሚገኘው ኤል-አሪሽ አየር ማረፊያ ውስጥ የእርዳታ አቅርቦት ማስተባበሪያ ማዕከል ከፍተዋል።
በዚህም በአየር ማረፊያው የተዘጋጁ ምግቦች እና ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች በብዛት እየደረሱ ነው። ከመካከላቸውም በከባድ ተሽከርካሪዎች ተጭነው 45 ኪሎ ሜትር ወደ ሚርቀው ወደ ራፋህ መተላለፊያ በመሄድ ወደ ጋዛ ለመግባት እየተጠባበቁ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እና የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ሌሎችም ወደ እስራኤል ተጉዘው እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ግፊት አድርገዋል። በቀጣይ ቀናትም የእርዳታ አቅርቦት የጫኑ 20 ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ የሚፈቅድ ስምምነት ተደርሷል።
ነዳጅ እና ውሃስ?
ነዳጅ ወደ ጋዛ በመደበኛው ሁኔታ ይገባ የነበረው ኬሬም ሻሎም በተባለው የድንበር መተላለፊያ በኩል በቧንቧ ሲሆን፣ ወጪውም በኳታር የሚሸፍን ነው። የነዳጅ አቅርቦቱም የሚውለው በቀን 600,000 ሊትር ለሚጠቀመው የጋዛ ብቸኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ነበር።
ነገር ግን ይህ ነዳጅ በአሁኑ ጊዜ የተቋረጠ ሲሆን፣ የጋዛ ፔትሮሊየም ባለሥልጣን ኃላፊው ኻሊድ ሞሐራብ የአቅርቦቱ መቋረጥ “የጋዛን ነዋሪ ሙሉ ለሙሉ ከማጥፋት እና በከተማዋ ያለውን ሕይወት ሽባ ከማድረግ ጋር የሚመሳሰል ነው” ይላሉ።
ከግጭቱ በፊት በጋዛ ኤሌክትሪክ በተደጋጋሚ የሚቋረጥ በመሆኑ ብዙ ሰዎች ለሚጠቀሙት ጄኔሬተር ነዳጅ ይፈልጋሉ። በተመሳሳይም አብዛኞቹ ሆስፒታሎች የመጠባበቂያ ጄኔሬተር ስለሚጠቀሙ ነዳጅ እያለቀባቸው ነው።
የኤሌክትሪክ ማመንጫው “የጋዛ እስትንፋስ ነው” የሚለው ሞሐራብ፣ የጋዛ ሆስፒታሎች እና የውሃ ማጣሪያዎች እንዲሁም ሌሎች ቁልፍ ተቋማት ኃይል የሚያገኙበት ነበር።
በጋዛ ውስጥ ወትሮም የውሃ ችግር የነበረ ቢሆንም፣ ከግጭቱ በኋላ ግን የውሃ ማጣሪያ ማዕከላት ሥራ በመስተጓጎሉ ችግሩ የበለጠ ተባብሷል። በቧንቧ የሚቀርበው ውሃ ቀደም ሲልም ጤንነቱ አስተማማኝ ያልነበረ ሲሆን፣ ከግጭቱ መጀመር በኋላ እስራኤል የንጹህ ውሃ አቅርቦቶችን አቋርጣለች።
በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሎች ውስጥ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የውሃ አቅርቦት እየሟጠጠ ነው። ለሕክምና መሳሪያዎች ሥራ እና ለንጽህና የሚውል ውሃ እጥረት በማጋጠሙ ከሱቆች አቼቶ በመግዛት የሕክምና መሳሪያዎችን ማጽዳት ግድ እንደሆነ አንድ ዶክትር በኤክስ (ትዊተር) ገጽ ላይ አስፍሯል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ወደ ጋዛ ምግብ፣ ውሃ እና የመድኃኒት አቅርቦት እንዲገባ በማድረግ በኩል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረትን አድንቀዋል። “በርካታ ሰዎች በእርዳታ ላይ ጥገኛ ናቸው” ሲሉም ዶ/ር ቴድሮስ ኤክስ ላይ የእርዳታ መንገድ እንዲከፈት ጠይቀዋል።