በጋዛ የሆስፒታል ፍንዳታ ስፍራ የተፈጠረው ድንጋጤ እና ግራ መጋባት

የፍልስጤም የጤና ኃላፊዎች ማክሰኞ ምሽት በጋዛ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል በደረሰ ፍንዳታ በትንሹ 471 ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል።

ለፍንዳታው የእስራኤል የአየር ጥቃትን ተጠያቂ አድርገዋል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ ፍንዳታው የተከሰተው ታጣቂው የፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ የተኮሰው ሮኬት ተበላሽቶ ከታለመለት ዒላማ ውጭ በመውደቁ ነው ብሏል።

የቢቢሲው ጋዜጠኛ ራሽዲ አቡ አሎፍ ቦታውን ጎብኝቷል። አሁን ድረስ የተጎጂዎች ሰውነት ክፍሎች እየተሰበሰቡ መሆናቸውን አረጋግጧል።

ፍንዳታውን ተከትሎ በተፈጠረው ትርምስ እና በደረሰው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ምክንያት አልባሳትና የግል ንብረቶች በየቦታው ተበታትነዋል። በደም የራሱ ትራሶች በአል አህሊ አረብ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ እዚህም እዚያም ይታያሉ።

በመኪና ማቆሚያ ስፍራ እሳት የበላቸው በደርዘን የሚቆጠሩ መኪናዎች ይገኛሉ።

በሆስፒታሉ ዙሪያ ያሉ ህንጻዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ይህ ነው የሚባል ትልቅ ጉድጓድ ግን አይታይም።

በዓለም አቀፍ ሕግ ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባው ቦታ ነበር። ብዙዎች የተፈጠረውን ነገር ለመረዳት ተቸግረዋል፣ በፍርሃት ድባብ ተውጠዋል።

ከፍንዳታው የተረፈች አንዲት ሴት "ወደዚህ የመጣነው ቤታችንን ትተን ነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። "ምንም አይሆንም ብለን ነበር ያሰብነው፣ ግን በቦምብ ተደበደበ" ብላለች።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሆስፒታሉን መጠለያ አድርገውታል።

አብዛኛዎቹ ተጎጂዎችም ቤታቸውን ጥለው በሆስፒታሉ የተጠለሉ ሰዎች መሆናቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል ።

የእስራኤል ጦር በታጣቂው ሐማስ ላይ የአየር ድብደባውን ከማጠናከር ባለፈ ነዋሪዎች የጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል ለቀው እንዲወጡ በማስጠንቀቁ የሸሹ ናቸው።

አብዛኛዎቹ በቤታቸው የቀሩት አረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ናቸው። ወደ ደቡብ እንዳይሰደዱ ትራንስፖርት ማግኘት አልቻሉም።

አካባቢው በከባድ ፍንዳታ ሲናጥ መሬት ላይ ተቀምጠው እንደነበር አንድ የዓይን እማኝ ተናግሯል።

ተጎጂዎችን ለመርዳት በጋዛ ሰርጥ ዙሪያ ያሉ ሰዎች በቦታው ለመድረስ ጊዜ አንዳልፈጀባቸውም ተናግሯል። በፍጥነትም አስክሬን ማሰባሰብና የተጎዱ ሰዎችን ማውጣት ጀመሩ።

ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው በሞተር ሳይክል ተነስተዋል። ቀለል ያለ ጉዳት ያስተናገዱት ደግሞ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ሺፋ ሆስፒታል በእግር ለመጓዝ ተገደዋል።

ሌላ ግለሰብ ደግሞ ከፍንዳታው በፊት አንድ ነገር መስማቱን አስታውቆ፤ ምን እንደሆነ ግን አላውቅም ብሏል።

አማራጭ ስላልነበረውም በድጋሚ ወደ ሆስፒታል መመለሱን አስረድቷል። "ወዴት መሄድ እንችላለን? ልክ እንደ 1948 ልንሄድ?" ሲል ጠይቋል።

እአአ 1948 በመቶ ሺህ ዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ቤታቸውን ጥለው የተሰደዱበት የመጀመሪያው የአረብ-እስራኤል ጦርነት ነው።

ምንም እንኳን ጥበቃ የሚደረግላቸው ቢሆንም አል አህሊ አረብን ጨምሮ በሰሜን ጋዛ የሚገኙ 20 ሆስፒታሎች ታካሚዎቻቸው እና ሠራተኞቻቸው ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ እንደደረሳቸው የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

አሁን ካለው የፀጥታ ችግር፣ ከታማሚዎች አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆን፣ የአምቡላንስ እጥረት እና የአልጋ እጥረት አንፃር ትዕዛዙን ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል መሆኑን ገልጿል።

ትዕዛዙ “አሁን ያለውን የሰብአዊ እና የማኅበረሰብ ጤና አደጋ የበለጠ እንደሚያወሳስበው” አስጠንቅቋል።