ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋዛው አል-አህሊ ሆስፒታል ላይ ስለደረሰው ፍንዳታ ማስረጃዎች ምን ይጠቁማሉ?
በጋዛ አል-አህሊ ሆስፒታል ላይ የደረሰው ከባድ ፍንዳታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደገደለ ተዘግቧል።
በሐማስ ሥር ያሉ በጋዛ አመራሮች ለፍንዳተው እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል። ሆነ ተብሎ የተፈጸመ የአየር ጥቃት ነው ሲሉም አውግዘዋል። እስራኤል ግን እጄ የለበትም ብላለች።
በሁሉም ወገኖች ክስ በበዛበት በዚህ ወቅት እውነታውን ማወቅ ፈታኝ ነው። ቢቢሲ እውነታውን ለማግኘት ተንቀሳቃሽ ምሥሎች፣ ምሥሎች፣ የዐይን እማኞች ምስክርነት እና ሌሎችም ማስረጃዎችን መርምሯል።
እምብዛም መረጃ ማግኘት ባይቻልም የቢቢሲ ጋዜጠኛም በቦታው ተገኝቷል።
በየጊዜው አዳዲስ መረጃ ይወጣል። ቢቢሲም አዳዲሶቹን መረጃዎች እና የባለሙያዎች አስተያየት ተመርኩዞ እዚህ ዘገባ ላይ ለውጥ ሊያደርግ ይችላል።
ውጊያው አካላዊ ብቻ ሳይሆን የመረጃ ጦርነት እየተደረገ እንደሆነም መገንዘብ ያሻል።
ፍንዳታ ከተከሰተ በኋላ የእስራኤል እና የጋዛ አመራሮች የተለያየ ምላሽ ሲሰጡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። የተለያዩ መግለጫዎች እና አስተያየቶችን በዘገባው እናካትታለን።
የተከሰተው ፍንዳታ
ባሳለፍነው ማክሰኞ ምሽት 1 ሰዓት አካባቢ ነው ፍንዳታው በጋዛ የተከሰተው። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የ20 ሰከንድ ቆይታ ያለወ ተንቀሳቃሽ ምሥል ተለቋል። ይህም ስለ ክስተቱ የመጀመሪያ የሚታይ ማስረጃም ነው። ሚሳኤል በስፍራው ላይ ሲያርፍ እና ተከትሎም ፍንዳታ ሲሰማ አንዲሁም እሳት ሲነሳ ይታያል።
በአል-ጃዚራ የተላለፈ ቀጥታ ተንቀሳቃሽ ምሥል 12 ሰዓት ከ59 ደቂቃ ላይ ደማቅ ብርሃን በጋዛ ሰማይ ላይ ያሳያል። ሁለት ጊዜ በልጨ ብሎ አቅጣጫ ይለውጥ እና ይፈነዳል።
ከዚያም ራቅ ባለ ስፍራ ፍንዳታ ይታያል። ከፍተኛ ፍንዳታ በካሜራ ባለሙያው አቅራቢያም ይታያል።
ቢቢሲ ይህ የሆነበትን ስፍራ የት እንደሆነ መርምሯል።
አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ፍንዳታው የተከሰተው ከሮኬት እንደሆነ አና ሮኬቱ እንደተበታተነ ገልጸዋል።
ሃያ የጦር መሣሪያ ባለሙያ፣ ድርጅቶች እና የምርምር ቡድኖችን አስተያየታቸው ጠይቀናል። እስካሁን ዘጠኙ ምላሽ አልሰጡም።
አምስቱ አስተያየት ለመስጠት አልፈቀዱም። የተቀሩት ስድስቱ ግን መልሰዋል።
የፍንዳታውን መጠን፣ ከፍንዳታው በፊት የተሰማውን ድምጽ እና ሌሎችም ማስረጃዎችን በማስደገፍ ነው አስተያየታቸውን የጠየቅነው።
በሆስፒታሉ ስለደረሰው ፍንዳታ መንስኤ ጠይቀን እስካሁን ግኝቶቹ እርግጠኛ ድምዳሜ ላይ የደረሱ አይደሉም።
ሦስት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ይህ ፍንዳታ እስራኤል በሌላ ጊዜ የአየር ጥቃት ስትፈጽም ከሚታየው ሰፋ ያለ ፍንዳታ ጋር ተመሳሳይ አይደለም።
በአሜሪካ፣ ቫንደርቢልት ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄ አንደርስ ጋኖን፣ ፍንዳታዎቹ መሬት ላይ ሲታዩ ትንሽ ይመስላሉ ይላሉ። ይህ ማለትም የፈጠረው ግለት መነሻው ከዚያ በፊት ከነበረ ሮኬት የተፈጠረ እንጂ የዚያ ፍንዳታ አይደለም።
በዩናይትድ ኪንግደም፣ የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስስ ኢንስቲትዩት አጥኚ ጀስቲን ብሮንክም በዚህ ይስማማሉ።
ብዙ መረጃ ባልወጣበት በአሁኑ ወቅት እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ማስረጃዎቹ የሚጠቁሙት ያልተሳካ የሮኬት አካል የመኪና ማቆሚያውን ከመታ በኋላ የተከሰተ የነዳጅ ፍንዳታ ነው ይላሉ።
ጄ አንድሬስ ጋኖን እንደሚሉት፣ ከታየው ተንቀሳቃሽ ምሥል በመነሳት ሚሳኤሉ ዒላማውን መምታቱ ወይም መሳቱ ለማወቅ አይቻልም።
በሰማይ ላይ የታዩ ብልጭታዎች የሚጠቁሙት ሮኬቱ ሞተሩ የጋለ ወይም መሥራት ያቆመ እንደሆነ ነው ይላሉ።
ሲቢላይን በሚባል ተቋም የመካከለኛው ምሥራቅ ተንታኝ የሆኑት ቫሌርያ ስኩቶ እንደሚሉት፣ እስራኤል ሌላ ዓይነት የአየር ጥቃቶችን በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) መፈጸም የሚያስችላት አቅም አላት። ሄልፋየር ሚሳኤል ሊጠቀሙም ይችላሉ።
እነዚህ ሚሳኤሎች ሙቀት መፍጠር የሚችሉ ሲሆን፣ ሰፋ ያለ ቅሪት ግን መተው አይችሉም።
ባለሙያዋ እንደሚሉት፣ ያልተረጋገጠ ተንቀሳቃሽ ምሥል እንደሚያሳየው፣ ከፍንዳታው ጋር የማይስተካከል የእሳት አካሄድ ተከስቷል።
ከፍንዳታው ስፍራ የተገኙ ማስረጃዎች
ቢቢሲ የአል-አህሊ ሆስፒታልን አቀማመጥ እና አቅራቢያው ያሉ ሕንጻዎች አቀማጥን ከሳተላየት ምሥል ጋር አመሳክሯል። ይህም ሆስፒታሉ ዒላማ ሆኖ ከሆነ ለማወቅ ነው።
ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ፍንዳታው የተከሰተው የሆስፒታሉ አካል የሆነ የግቢው ክፍል ውስጥ ነው።
ፍንዳታው ከተከሰተ በኋላ የታዩ የአካባቢው ምሥሎች ፍንዳታው በሆስፒታሉ አካባቢ ያሉ ሕንጻዎች ላይ የከፋ ጉዳት አለመድረሱን ያሳያሉ። ምሥሎቹ የተቃጠሉ መኪናዎችን ቅሪት ግን ያሳያሉ።
ሆስፒታሉ የአንገሊካን ቤተ ክርስቲያን ነው።
በእየሩሳሌም የሴንት ጆርጅ ኮሌጅ ዲን የሆኑት ካኖን ሪቻርድ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በሆስፒታሉ ፍንዳታው ሲከሰት 1,000 ገደማ ተፈናቃዮች በጊቢው ውስጥ ተጠልለው ነበር።
በሕንጻው ውስጥ ወደ 600 ታካሚዎች እና ሠራተኞች ነበሩ።
ተጎጂዎቹ
የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሩሽዲ አብዱላውፍ ሆስፒታሉን ጎብኝቷል። የደረሰውን አስከፊ ውድመት ይናገራል። ገና አስክሬኖች እየተነሱ እንደሆነም ይገልጻል።
ፍንዳታው ሲከሰት ሴቶች፣ ሕጻናትና አረጋውያን ሆስፒታሉ ውስጥ እንደነበሩ አንድ ሰው ነግረውታል።
የተጎጂዎቹን ምሥሎች በማጣራት ላይ ስንሆን በፍንዳታው የደረሰን ጉዳት ከዚያ ቀደም ከደረሰ የአካል ጉዳት ለይቶ ለማወቅ እየተሞከረ ነው።
ቢቢሲ እጅግ አሰቃቂ የሆኑ የተጎጂዎችን እና ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ምሥል ተመልክቷል።
የሰው አካል ጥናት ባለሙያው (ፓቶሎጂስት) ዴሪክ ፖውንደር በዩናይትድ ኪንግደም ፊዚሺያንስ ፎር ሂውማን ራይትስ የተባለ ተቋም መሥራች ናቸው።
ከደረሰው ጉዳት የተወሰኑትን ተመልክተዋል።
“የተበታተኑት ጠባሳዎች ከፍንዳታ የሚጠበቁ ናቸው” ይላሉ።
የተረጋገጡ ምሥሎች ውስን ስለሆኑ ሁሉንም ጉዳቶች በአጠቃላይ ለመረዳት እንደሚያስቸገር ይገልጻሉ።
የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር በፍንዳታው 471 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቁጥሩ የተጋነነ ነው ብሏል። ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ግን አልገለጸም።
ገለልተኛ ወገኖች ወደ አካባቢው መግባት ስለማይችሉ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር በእርግጥ ለማወቅ ይቸግራል።
እስካሁን የምናውቀው
በፍንዳታው የደረሰው ጠባሳ አንድ ሁነኛ ማስረጃ ነው።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ሰፊ ቅሪት አለመገኘቱ አና በአካባቢው ባሉ ሕንጻዎች የደረሰው ጉዳት በእሱ መሣሪያዎች የደረሰ ፍንዳታ ላለመሆኑ ማስረጃ ናቸው።
ተጨማሪ ምሥሎችን ቢቢሲ እየመረመረ ሲሆን፣ አንድ ትንሽ ቅሪት የተወ የፍንዳታ ቦታ ተመልክቷል።
ከመሣሪያው የወዳደቁ ክፍሎች አለመገኘት ሌላው ትልቅ ጉዳይ ነው።
መሣሪያዎችን ለመለየት የወዳደቁ ክፍሎቹን መመልከት ይረዳል።
ይህንን ማስረጃ ግን አላየንም።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል አንድ የተቀዳ ድምጽ ለቋል።
ድምጹ ሁለት የሐማስ ታጣቂዎች ሲነጋገሩ ነው የተባለ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹ የሚያወሩት ሆስፒታሉ በፍልስጤም ኢስላሚከ ጂሀድ ቡድን መመታቱን ሲያረጋግጡ ነው ተብሏል።
ይህ ቡድን በጋዛ ሁለተኛው ትልቁ ታጣቂ ቡድን ነው። ሐማስ በእራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃትም ደግፏል።
ይህንን የድምጽ ቅጂ በገለልተኛ ወገን ለማጣራት አይቻልም። የፍልስጤም ኢስላሚክ ጂሀድ ግን በዚህ ውስጥ እጁ እንደሌለ ገልጾ ለፍንዳታው እስራኤልን ወንጅሏል።