የራፋህ የድንበር ማቋረጫ ምንድን ነው? እንዴትስ የጋዛ ነዋሪዎች ተስፋ ለመሆን በቃ?

ከሚጠበቀው የእስራኤል የእግረኛ ጦር ዘመቻ በፊት ፍልስጥኤማውያን ከአካባቢው ለመልቀቅ በማሰብ ከደቡባዊ የጋዛ ሰርጥ ወደ ግብፅ በሚያሻግረው የራፋህ የድንበር ማቋረጫ ላይ እየተሰባሰቡ ነው።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በዚህ ጊዜ ባይሉም የድንበር ማቋረጫው ጥምር ዜግነት ያላቸውን ለማስወጣት እና ሰብዓዊ እርዳታ ለማስገባት እንደሚከፍት ዘግበዋል።

ሆኖም ድንበር ማቋረጫው እስካሁን ድረስ እንደተዘጋ ነው።

የራፋህ የድንበር ማቋረጫ ምንድን ነው?

ከጋዛ ደቡባዊው ጫፍ የሚገኝ እና ከግብፅ የሲናይ በረሃ ጋር የሚዋሰን የድንበር ማቋረጫ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ከጋዛ ሰርጥ የሚመወጡ ሁለት የድንበር ማቋረጫዎች ብቻ አሉ ። ኢሬዝ የሚባለው ከእስራኤል ጋር የሚዋሰን ሲሆን፣ በሰሜናዊ ጋዛ ላሉ ሰዎች መሻገሪያ ሆኖ ያገለግላል።

ኬሬም ሻሎም ደግሞ በደቡብ ጋዛ ከእስራኤል ጋር የሚያገናኝ ብቸኛ የንግድ ዕቃዎች መተላለፊያ ነው። ሁለቱም የድንበር ማቋረጫዎች አሁን ተዘግተዋል።

የድንበር ማቋረጫው አሁን ለምን አስፈላጊ ሆነ?

ጋዛን የሚያስተዳድረው የፍልስጥኤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ከቀናት በፊት በኤሬዝ የድንበር ማቋረጫ በኩል በደቡብ እስራኤል ጥቃት ፈጸመ። በዚህ ታይቶ የማይታወቅ ነው በተባለው ጥቃት ከ1,300 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

ከቀናት በኋላ እስራኤል ኢሬዝ እና ኬሬም ሻሎም መተላለፊያዎች ተጨማሪ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ እንደተዘጉ እንደሚቆዩ አስታወቀች። ይህም የራፋህ የድንበር ማቋረጫን ብቸኛው ለሰዎች መግቢያ እና መውጫ የሚያገለግለው መንገድ እንዲሆን አድርጎታል።

አሁን ራፋህ ለሰብአዊ እርዳታ ብቸኛ መሻገሪያ ሆኗል።

ባለፈው ሳምንት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ የእርዳታ በረራዎችን በሰሜን ሲናይ ወደሚገኘው ኤል-አሪሽ የአውሮፕላን ማረፊያ እያመሩ መሆኑን ገልጾ ነበር።

በደርዘን የሚቆጠሩ ነዳጅ እና ሰብዓዊ ድጋፎችን የጫኑ መኪናዎች በግብፅ አቅጣጫ በሚገኘው በራፋህ የድንበር ማቋረጫ ላይ ደርሰዋል።

በድንበር ማቋረጫው ላይ ምን እየተከናወነ ነው?

በራፋህ ስላለው ሁኔታ እርስ በርስ የሚጋጩ ዘገባዎች እየወጡ ነው። ማን ማለፍ ይችላል የሚለውን ሐማስ እና ግብፅ ይቆጣጠራሉ። እስራኤል ለሐማስ ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት በጋዛ የአየር ድብደባ ማድረጓን ተከትሎ የድንበር ማቋረጫው ሥራውን አቁሟል።

የእስራኤልን ሦስት ጥቃቶች ተከትሎ የድንበር ማቋረጫው መዘጋቱን የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። በጥቃቱ በግብፅ እና በፍልስጥኤም ድንበር በኩል ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል።

ለጋዛ ነዋሪዎች “የእርዳታ መስጫ መስመር” ሆኖ እንዲያገለግል እስራኤል በራፋህ ድንበር ማቋረጫ አቅራቢያ የምታደርገውን ጥቃት እንድታቆም ግብፅ ጠይቃለች። በድንበሩ ላይ ለሚሠሩ ዜጎቿ ደኅንነት ዋስትና እስካላገኘች ድረስ መተላለፊያውን እንደማይከፍትም አስታውቃለች።

በጋዛ የሚገኙ የውጭ ዜጎች በራፋህ በኩል እንዲወጡ እና ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ በማለት ምዕራባውያን አገራትም ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊ እና የአሜሪካው አቻቸው አንቶኒ ብሊንከን ከእስራኤል፣ ከግብፅ እና ከሌሎች የቀጣናው አገራት ጋር በመሆን ማቋረጫው እንዲከፈት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቁት የአሜሪካ ዜጎች ከጋዛ ለመውጣት ወደ ራፋህ እንዲሄዱ ተነግሯቸዋል። ምክንያቱም “መሻገሪያው የሚከፈተው በአጭር ማስታወቂያ ሊሆን ስለሚችል እና ሲከፈትም ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ሊሆን ስለሚችል ነው” ብለዋል።

ለአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ከተደረገ ማቋረጫው በጊዜያዊነት ይከፈታል መባሉን ተከትሎ ሰኞ ዕለት በርካታ ሕዝብ በራፋ ተሰብስቦ ነበር።

እስራኤል እና ሐማስ ግን የተኩስ አቁም ይደረጋል መባሉን በፍጥነት አስተባብለዋል።

የድንበር ማቀወረጫዎቹ ለምን ተዘጉ?

ሐማስ ጋዝን እአአ በ2007 መቆጣጠሩን ተከትሎ እስራኤል እና ግብፅ ወደ አካባቢው የሚገባ ቁሳቁስ እና ሰው እንዲገደብ አድርገው ቆይተዋል። ሁለቱም ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በደኅንነት ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል።

የሐማስ ጥቃትን ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ጋዛ “ሙሉ በሙሉ በከበባ” ስር እንድትሆን አዟል። “ኤሌክትሪክ፣ ምግብ እና ነዳጅ አይኖርም። ሁሉም ነገር ተዘግቷል።”

የውጭ አገራት ፓስፖርት ለያዙ እና ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ በሚል ግብፅ የራፋህ ድንበር ማቋረጫን እንደገና ለመክፈት የተዘጋጀች ቢመስልም፤ ከጦርነቱ የሚሸሹ ፍልስጥኤማውያን ስደተኞች በብዛት ወደ ድንበሯ እንዳይሻገሩ ስጋት ገብቷታል።

የግብፁ ፕሬዝዳንት በርካታ ሕዝብ ከጋዛ ነመውጣት ወደ አገራቸው የሚገባ ከሆነ የፍልስጥኤም ጉዳይን “በማዳከም” አደጋ ላይ እንደሚጥል በማስጠንቀቅ፤ ፍልስጥኤማውያን “በመሬታቸው ላይ ጸንተው እንዲቆዩ” ጠይቀዋል።

በሲናይ በኩል ለአስር ዓመታት ያህል የጂሃዲስቶች ሽምቅ ጥቃትን የተጋፈጠችው ግብፅ፤ አጋጣሚውን ተጠቅመው እስላማዊ ታጣቂዎች ወደ አገሪቱ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ተጨማሪ ስጋት አለባት።

የራፋህ ማቋረጫ እንዴት ያገለግል ነበር?

ቀደም ብሎም ቢሆን ፍልስጥኤማውያን በራፋህ በኩል ከጋዛ ለመውጣት ቀላል አይሆንላቸውም።

ማቋረጫውን ለመጠቀም የሚፈልጉ ፍልስጥኤማውያን ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት ቀደም ብለው በፍልስጥኤም ባለሥልጣናት መመዝገብ ይጠበቅባቸው ነበር።

በፍልስጥኤምም ሆነ በግብፅ ባለሥልጣናት በቀላል ምክንያት ወይም ማብራሪያ ጥያቄያቸው ውድቅ ሊደረግ ይችላል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እአአ በ2023 እንደገለጸው የግብፅ ባለሥልጣናት 19,608 ሰዎች ከጋዛ እንዲወጡ ሲፈቅዱ 314 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ እንዳይገቡ ከልክለዋል።