ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢዜማ የፓርቲው ሊቀመንበር የታሰሩት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ መሆኑን አስታወቀ
ከሳምንት በፊት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ፓርቲያቸው አስታወቀ።
በአማራ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት የፓርቲው ሊቀመንበር በኮማንድ ፖስቱ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው መረጃዎች እንዳገኘ ፓርቲው ሰኞ መስከረም 21/ 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ሊቀመንበሩ በቁጥጥር ስር የዋሉት “በፓርቲያችን ባላቸው ኃላፊነት” አለመሆኑም የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ጉዳዩን እንዲከታተል ያቋቋመው ኮሚቴ ባደረገው ማጣራት ማወቁን ፓርቲው በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
መግለጫው ሊቀመንበሩ በኮማንድ ፖስቱ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው ውጪ በምን እንደተጠረጠሩም ሆነ ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችን አላስቀመጠም።
ከሊቀመንበሩ መያዝ በኋላ ቢቢሲ በእራሱ ማረጋገጥ ያልቻላቸው የዶክተር ጫኔ ከበደ ናቸው የተባሉ የስልክ ውይይት የድምጽ ቅጂዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ሲዘዋወር ነበር።
የስልክ ውይይቱ በትክክል የማን እንደሆነ እና እንዴት እንደተገኘ እና ለምን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሊወጣ እንደቻለ በትክክል የታወቀ ነገር የለም።
ዶክተር ጫኔ የእስር ማዘጃ በሌለበት ሁኔታ እሁድ መስከረም 13/2016 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች የሰሌዳ ቁጥር በሌለው መኪና መወሰዳቸውን ፓርቲያቸው አስታውቆ ነበር።
ፓርቲው በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ሊቀመንበሩ በቁጥጥር ስር የዋሉበት መንገድ ሕግ እና ሥርዓትን ያልተከተለ ነው ሲል ወቅሶ ነበር።
ሊቀመንበሩ በቁጥጥር ስር የዋሉበት ምክንያት ከታወቀ በኋላም የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴው መስከረም 19/2016 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ አድርጓል።
አገሪቱ ያለችበትን የፖለቲካ ውጥረት እንደገመገመ ያሳወቀው ኢዜማ በመርኅም ሆነ በተግባር በዜግነት የፖለቲካ አስተሳሳብ እና በጸና የሰላማዊ ትግል እንደሚያምን አጽንኦት ሰጥቷል።
በዚህም መሠረት በማንኛውም ሁኔታ “በዘውግ ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴም ሆነ በኃይል መንግሥታዊ ሥልጣን ለመያዝ በሚደረግ ትግል” ፈጽሞ እንደማይሳተፍ እና ከቆመበት አላማም ተቃራኒ መሆኑንም አሳውቋል።
ሥራ አስፈጻሚው በዚህ ውይይቱ ማንኛውም የኢዜማ አባላት እንዲሁም የድርጅቱ አመራሮች በእነዚህ ተግባራት ከተሳተፉ ድርጅቱን ለማፍረስ እንደሚሠሩ ተደርጎ ይቆጠራል ብሏል።
“ኢዜማ ውስጥ የማይነካም ሆነ የማይተካ አባልም ሆነ አመራር የለም” ያለው መግለጫው፣ ከድርጅቱ ዓላማ እና የትግል መስመር ባፈነገጡ አባላትም ላይ የጸና አቋም እንደሚይዝም አስታውቋል።
የኢዜማ አባላት እና ደጋፊዎች ፓርቲው ካስቀመጠው የሰላማዊ ትግል አቅጣጫ በተቃራኒ መቆምም የፓርቲውን ሕገ ደንብ በግልጽ መጣስ የአገሪቱን የፓለቲካ ችግሮች የሚያባብስ መሆኑን ሊገነዘቡ እንደሚገባም አስታውቋል።
“ከሰላማዊ ትግል እና ከዜግነት ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውጪ ያለን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መደገፍ፣ የሀሳብም ሆነ የተግባር ተሳትፎም ሆነ ትብብር ማድረግ” ከፓርቲው መርኅ ያፈነገጠ ነው ብሏል።
የፓርቲው ሊቀ መንበርም ጉዳይ በዚህ መርኅ አንጻር የሚታይ እንደሆነም መግለጫው አስፍሯል። ሆኖም የፓርቲው ሊቀመንበር ፓርቲው መርኅ ሲል ካስቀመጣቸው “የሰላማዊ ትግል አቅጣጫ እና የዜግነት ፖለቲካ” ውጪ ስለመሳተፋቸው ያለው ነገር የለም።
ከዚህ ቀደም የኢዜማ ምክትል ሊቀ መንበር እና አሁን የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶክተር ጫኔ፣ በመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) እና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ውስጥ በተለያዩ የአመራርነት ቦታዎች አገልግለዋል።