ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሰሜናዊ የአማራ ዞኖች በድርቅ ቢያንስ የ18 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ባለሥልጣናት ተናገሩ
በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ጎንደር ዞኖች በተከሰተ ድርቅ ቢያንስ የ18 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና በርካቶችም የሞት አደጋ እንደተጋረጠባቸው የአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት ተናገሩ።
ባለሥልጣናቱ ለቢቢሲ እንደገለጹት ቀድሞ ከነበረው ችግር ጋር ተደማምሮ ሲጠበቅ የነበረው የክረምት ዝናብ ባለመዝነቡ በተከሰተው ድርቅ በሁለቱም ዞኖች ከ10 ሺህ በላይ የዳልጋ እና የጋማ ከብቶች ሞተዋል።
በሰሜን ጎንደር ውስጥ የሚገኘው ጃናሞራ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት ሸጋው ተሰማ በወረዳው በተከሰተው ድርቅ የ16 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከሟቾቹ መካከልም አብዛኞቹ ሴቶች እና አረጋውያን መሆናቸውንም ገልጸዋል።
“አርሶ አደሮቹ ተስፋ ቆርጠዋል። እስካሁን ድረስ ወደ 4 ሺህ የሚደርሱ አርሶ አደሮች የሄዱበት አልታወቀም። ስንንቀሳቀስ ቤታቸው ተዘግቶ ነው የምናገኘው። በአካባቢው ያሉት ነዋሪዎችም መንግሥት በአፋጣኝ እንዲደርስላቸው ተማጽነዋል” ብለዋል።
አተትን ጨምሮ በአካባቢው ወረርሽኞች በስፋት መከሰታቸውን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በድርቁ ሳቢያ ከ7500 በላይ የዳልጋ እና የጋማ ከብቶች መሞታቸውን፣ የተረፉትም የደከሙ እና ለገበያ እንኳን መቅረብ የሚችሉ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
“ለሚመለከታቸው አካላት ብናሳውቅም ምላሽ አላገኘንም። ለበሽታ ለተጋለጡት ሰዎችም መድኃኒት ማቅረብ አልተቻለም” ብለዋል።
በወረዳው ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተደጋጋሚ ድርቅ አጋጥሞ እንደነበር የሚያስታውሱት አስተዳዳሪው፣ ባለፈው ክረምት በወረዳው ውስጥ ከሚገኙት 38 ቀበሌዎች ውስጥ በ13ቱ ጭራሽኑ ዝናብ እንዳልነበረ ተናግረዋል።
በእነዚህ ቀበሌዎች ወደ 57 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል።
በአጠቃላይ በወረዳው ከ230 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚኖር ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ከ128 ሺህ በላይ የሚሆኑት ቀድሞውንም የምግብ ዋስትና ችግር የነበረባቸው ናቸው።
አስተዳዳሪው ጨምረውም በዞኑ የሚገኘው የጠለምት ወረዳም በድርቅ መጠቃቱን እንደሚያውቁም ተናግረዋል።
አጎራባች በሆነው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች ውስጥም ባለፈው ዓመት ዝናብ ባለመዝነቡ ከፍተኛ የሆነ የሰዎች እና የእንስሳት ሞት መከሰቱ ተነግሯል።
በዞኑ አስከፊ ድርቅ የተከሰተበት የስሃላ ሰየምት ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት ሲሳይ ብሩ እንደተናገሩት እስካሁን በረሃብ ምክንያት ቢያንስ የሁለት ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ የሞት አደጋ የተጋረጠባቸው በርካቶች ናቸው።
በአካባቢዎቹ ከመንግሥትም ሆነ ከእርዳታ ድርጅቶች የሚቀርብ ምንም ዓይነት እርዳታ አለመኖሩንም ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
እርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ እርዳታው በትግራይ ክልል ከታለመለት ዓላማ ውጭ ውሏል በሚል በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ድጋፍ ማቋረጣቸውን ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እርዳታው በትግራይ በረሃብ ለተጎዱ ሰዎች ሳይሆን፣ ለሽያጭ መቅረቡን፣ እንዲሁም ስርቆት ተፈጽሟል በሚል ነበር የሚያደርጉትን ድጋፍ ያቋረጡት።
ዩኤስኤአይዲ የእርዳታ አቅርቦቱን ማቋረጡን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ‘ፖለቲካዊ’ ነው ሲል ተቃውሞታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን የምግብ እርዳታ ሊያስቀጥል እንደሚችል ሰኔ ወር ላይ ተጠቁሞ የነበረ ቢሆንም እስካሁን አልጀመረም።
በዚህም ምክንያት ጥቃት እና ግጭትን ሸሽተው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች እና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች የሚኖሩ እና ቀድሞውኑም እርዳታ ጠባቂ የሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል።
የስሃላ ሰለምት ወረዳ አስተዳዳሪ እንዳሉት በወረዳው ዝናብ ባለመዝነቡ 60 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብልም ወድሟል።
“ማኅበረሰቡ የሚላስ የሚቀመስ የለውም” ያሉት አስተዳዳሪው፣ ከዚህ በፊትም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ይገፉ የነበሩት ነዋሪዎቹ ለረሃብ ተጋልጠዋል ብለዋል።
“ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ የቤት እንስሳትም ሞተዋል። ከዚህ በፊት ድርቅ አጋጥሞ ቢያውቅም ቢያንስ ለእንስሳት የሚሆን መኖ ይገኝ ነበር። አሁን ግን ለሰውም፣ ለእንስሳትም አስጊ የሆነ ድርቅ ነው የተከሰተው” ብለዋል።
እንደ አቶ ሲሳይ ከሆነ በወረዳው ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ይኖራሉ።
ከእነዚህ መካከል 46 ሺህ የሚሆኑት ዘላቂ ድጋፍ የሚሹ ሲሆን፣ ከ20 ሺህ በላይ ሚሆኑት አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።
“እናቶች፣ አረጋውያን እና ሕጻናት ለከፋ ረሃብ ተጋልጠዋል፤ በተለያዩ ወረርሽኞችም እየተሰቃዩ ነው” ብለዋል።
አሁን ላይ በአካባቢው የፀጥታ ችግር እንደሌለ የገለጹት አስተዳዳሪው፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ይቀርብ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ከተቋረጠ በኋላ ምንም የሚቀርብ እርዳታ እንደሌለ ተናግረዋል።
ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ብናደርግም ያገኘነው ምላሽ የለም ብለዋል።
በዚህም ምክንያት በርካቶች በረሃብ ይሞታሉ ብለው ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ በዞኑ ውስጥ በሚገኙት ሳሃላ ሰየምት፣ ዝቋላ እና አበርገሌ በሚባሉት ሦስት ወረዳዎች ውስጥ ድርቅ መከሰቱን ለቢቢሲ አረጋግጠው፣ በስሃላ ሰየምት ወረዳ የተከተሰው ግን የከፋ ነው ብለዋል።
ቢቢሲ ባነጋገራቸው ወቅት በወረዳው የወደመውን ሰብል እየጎበኙ እና ነዋሪዎችን እያነጋገሩ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው “አካባቢው መስከረም ሳይሆን መጋቢት ወር ላይ ያለ ነው የሚመስለው። አቧራ ነው የሚታየው። ድርቁን ለመግለጽ ከባድ ነው” ብለዋል።
በዚህ ሳምንት የመንግሥት ድጋፍ ካልደረሰ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 6.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች እንዳሉ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ እያሱ መስፍን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ለተከታታይ አምስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ በመጥፋቱ በአርባ ዓመታት ውስጥ ያልታየ ድርቅ ተከስቶ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉ አይዘነጋም።
በአገሪቷ ውስጥ የሚፈፀሙ ጥቃቶች፣ ግጭቶች እና ጦርነቶች ተደማምረው ችግሩን አስከፊ አድርገውታል።
ዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት 11.8 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በድርቅ ምክንያት አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ጥር ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት ጠቁሟል። ቁጥሩ ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ59 በመቶ ከፍ ማለቱን መግለጹም ይታወሳል።