የተባበሩት መንግሥታት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የምግብ እርዳታ አቋረጠ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ እርዳታ ላልተገባ ዓላማ በመዋሉ ለአገሪቱ የሚያደርገውን የምግብ ዕርዳታ አርብ ሰኔ 2/2015 ዓ.ም ማቋረጡን አስታወቀ።

በረሃብ ለተጎዱ ሰዎች የተላከን ዕርዳታ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ በመፈጸም ሽያጭ ላይ ውሏል በሚል የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ ተመሳሳይ ዕርምጃ ከአንድ ቀን በፊት መውሰዱም ተዘግቧል።

“ዕርዳታው ላልተገባ ዓላማ መዋሉ ፍጹም ተቀባይነት የለውም” ሲሉም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲንዲ ማኬይን በትናንትናው ዕለት ባወጡት መግለጫ ተናግረዋል።

“የመጀመሪያው ኃላፊነታችን በእኛ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ለሆኑ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ረሃብተኞች ነው። ከሁሉም አጋሮቻችን ጋር ሆነን ለማስጀመር በትጋት የምንሠራ ሲሆን ዕርዳታ ለተጎጂዎች መድረሱን ማረጋገጥ ስንችልም የምናስቀጥል ይሆናል” ሲሉም ኃላፊዋ መናገራቸው በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።

በአፍሪካ ቀንድ ለአራት አስርት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ድርቅና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በእነዚህ ቀውሶች ለተጎዱ 7 ሚሊዮን ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እርዳታን የሚያቀርብ ሲሆን የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ እስካሁን በአውሮፓውያኑ ባለፈው ዓመት 1.8 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ በመለገስ ቀዳሚዋ እንደሆነችም መረጃዎች ያሳያሉ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራምም ሆነ የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ እርዳታቸውን ለማቋረጥ ምክንያት ስለሆነው ዕርዳታ ላልተገባ ጥቅም መዋል ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ነገር ግን ሮይተርስ ተመልክቼዋለሁ ባለው የውጭ አገራት ለጋሽ ድርጅቶች ውስጣዊ ማስታወሻ፣ የምግብ እርዳታዎች ለኢትዮጵያ ሠራዊት መቅረቡን የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት ያምናል ብሏል።

“በፌደራል እና በክልል የመንግሥት አካላት አቀናባሪነት በመላው አገሪቱ ያሉ ወታደራዊ ክፍሎች ከሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ ተጠቃሚ ሆነዋል” በማለት ዩኤስኤአይዲ አባል የሆነበት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ቡድኖች ሰነድ አመልክቷል።

ለተረጂዎች መድረስ የነበረበት የምግብ እርዳታ ላይ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ መፈጸሙ በምርመራ መረጋገጡንና የአሜሪካ መንግሥትም በዚህ ምክንያት እርዳታውን ማቋረጡን ዋሽንግተን ፖስት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል።

ለለጋሾች የተሰጡ እና ዋሸንግተን ፖስት የተመለከታቸው ሾልከው የወጡ ሰነዶች እንደሚያመለከቱት የእርዳታ ዝርፊያው በፌደራል እና የክልል መንግሥታት አካላት የተቀነባበረ ነው ብሏል። በዚህም መሠረት ለተራቡ ተጎጂዎች የተላከውን ዕርዳታ ባለሥልጣናቱ ለጦር ሠራዊቱና ለቀድሞ ተዋጊዎች ሲመግቡ ነበር ብሏል።

በተጨማሪም እርዳታው በገበያ ላይ የተሸጠ ሲሆን ነጋዴዎችም ፈጭተው ወደ ውጭ አገራት ማከፋፈላቸውንም የዩኤስኤይዲ ምርመራ ማመላከቱንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሥልጣን ለዋሽንግተን ፖስት መግለጻቸው ተዘግቧል።

የአሜሪካ መንግሥት እርዳታ ማቋረጡንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ዩኤስኤአይዲ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለውን የምግብ እርዳታ ላልተገባ ዓላማ መዋልን እልባት ለማግኘት ቁርጠኞች መሆናቸውን ሰኔ 1/2015 ዓ.ም በጋራ ባወጡት መግለጫ አመልክተዋል።

“ሁለቱ መንግሥታት እርዳታዎችን ላልተገባ ዓላማ ያዋሉ ወንጀለኞች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ምርመራ እያደረጉ ነው። ሁለቱ መንግሥታት በኢትዮጵያ ውስጥ እርዳታ በተቀላጠፈ መንገድ የሚዳረስበትና እንዲሁም እርዳታ ላልተገባ ዓላማ ከመዋል በሚታደግ መልኩ የሚሰራጭበትን ሥርዓት ለማስፈን በትብብር ለመሥራት ቃል ገብተዋል” ብሏል የጋራ መግለጫቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታው ላልተገባ ዓላማ መዋሉን ምርመራ ለማድረግና ተጠያቂነት ለማስፈን መግለጹንም በበጎ እንደሚመለከቱት የገለጹት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ተቋማቸው በኢትዮጵያ የሚያደርገውን አንዳንድ እርዳታውን እንደሚቀጥልም መናገራቸው በመግለጫቸው ሰፍሯል።

“በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታን ለጊዜው ብናቆምም ለሕጻናት፣ ለነፍሰ ጡሮች እና ለአራሶች የምናደርገው የምግብ እርዳታ እንዲሁም የትምህርት ቤት ምገባ ይቀጥላል። በተጨማሪም አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ለማቋቋም እየሠራናቸው ያለው የአቅም ግንባታ ተግባራት አይቋረጡም” ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ በጦርነቱ በከፋ ለተጎዳችው ትግራይ የሚያቀርቡትን እርዳታ ባለፈው ወር አቋርጠዋል።

የረድዔት ድርጅቶቹ እርዳታው በትግራይ በረሃብ ለተጎዱ ሰዎች ሳይሆን ከታለመለት ዓላማ ውጭ ገበያ ላይ ሽያጭ መቅረቡን እንዲሁም ስርቆት ተፈጽሟል በሚል በተመሳሳይ ሁኔታ ማቋረጣቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ በትግራይ ክልል በምግብ እጥረት ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩንና ሁኔታዎች መክፋታቸው ተዘግቧል።

በክልሉ ባለፉት አምስት ወራት በምግብ እጥረት 13 ሕጻናት መሞታቸውን የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ለቢቢሲ ተናግሯል።

በመቀለ በሚገኘው የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ገብተው ሕክምና ሲደረግላቸው ከነበሩት መካከል በግንቦት ወር ብቻ ሰባት ሕጻናት ሕይወታቸው ማለፉንም የሕክምና ባለሙያዎች ገልጸዋል።