የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት በኢትዮጵያ የሚያቀርበውን እርዳታ ለማቋረጥ ወሰነ

የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ በኢትዮጵያ የሚያቀርበው የምግብ እርዳታ ለተረጂዎች ሳይደረስ ሌላ ጥቅም ውሏል በሚል እንዲቋረጥ መወሰኑን አስታወቀ።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የድርጅቱን ቃል አቀባይ መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ዩኤስኤአይዲ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው “ለኢትዮጵያ ሕዝብ መቅረብ የነበረበት የምግብ እርዳታ በከፍተኛ መጠን እና በተቀናጀ ሁኔታ ከታቀደለት አላማ ውጪ ጥቅም ላይ በመዋሉ” መሆኑን ገልጿል።

ውሳኔው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመቀናጀት የተወሰደ መሆኑን የገለጸው የተራድኦ ድርጅቱ፣ ይህንን የምግብ እርዳታ አቅርቦትን ወደ ሌላ አቅጣጫ በማዞር ተሳታፊ የሆኑ ወገኖችን እንዳልጠቀሰ ሮይተርስ ዘግቧል።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ “የተደረገውን አገር አቀፍ ቅኝት ተከትሎ ዩኤስኤአይዲ፣ በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ ለውጥ እስኪደረግ ድረስ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል፣ አስቸጋሪ ነገር ግን አስፈላጊ ውሳኔ አሳልፈናል” ሲሉ በኢሜይል መግለጻቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።

ባለፉት ሁለት ወራት የተካሄደ ምርመራ በለጋሾች የተገዛ የምግብ እርዳታ ከታለመለት አላማ ውጪ መዋሉን እና ለገበያ መቅረቡን እንዲሁም በአንዳንድ ሁኔታዎችም ወደ ውጪ አገራት መላኩን ብሉምበርግ ተመለከትኩት ያለው ሰነድ አሳይቷል።

ከጥቂት ወራት በፊት ዩኤስኤአይዲ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በተመሳሳይ ሁኔታ ትግራይ ውስጥ ስርቆት ተከስቷል በሚል በክልሉ ያቀርቡ የነበረውን የምግብ እርዳታ ማቋረጣቸው ይታወሳል።

ሮይተርስ ተመለከትኩት ባለው የውጭ አገራት ለጋሽ ድርጅቶች ውስጣዊ ማስታወሻ ላይ፣ ከታለመለት አላማ ውጪ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተደረጉ የምግብ እርዳታዎች “ለኢትዮጵያ ሠራዊት ክፍሎች ቀርቧል ብሎ የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት ያምናል” ብሏል።

“በፌደራል እና በክልል የመንግሥት አካላት አቀናባሪነት በመላው አገሪቱ ያሉ ወታደራዊ ክፍሎች ከሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ ተጠቃሚ ሆነዋል” በማለት ዩኤስኤአይዲ አባል የሆነበት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ቡድኖች ሰነድ አመልክቷል።

ሮይተርስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከመከላከያ ሠራዊቱ ምላሽ ለማግኘት ሞክሮ አልተሳካለትም። የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅትም በተጠቀሰው ሪፖርት ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሊዮኖች ከፍተኛውን ሰብአዊ እርዳታን በማቅረብ ከሌሎች አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል ዋነኛው ነው።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንተኒ ብሊንከን ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በመካሄድ ላይ በሚገኝ ስብሰባ ላይ በተጓዳኝ ካገኟቸው ከኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ መነጋጋራቸውን መሥሪያ ቤቱ ባወጣው አጭር መግለጫ ላይ አመልክቷል።

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች መካከል የእርዳታ ምግብ ከታለመለት አላማ ውጪ መዋሉ አንዱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ቁርጠኛ በመሆኑ ብሊንከን አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

መግለጫው ጨምሮም፣ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት ቃል አቀባይ የእርዳታ አቅርቦቱ ሥርዓት አስተማማኝ መሆኑ ከተረጋገጠ እርዳታውን መልሶ እንደሚጀመር መግለጻቸውን አካቷል።