ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከሥራ ለቀቁ መባሉን አስተባበለ
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ኃላፊዎች ድርጅቱ የሚያካሂደው ምርመራ ከመጠናቀቁ በፊት በፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀዋል የተባለው ሐሰት ነው ሲል ድርጅቱ አስተባበለ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቢሮ ዛሬ ግንቦት 29/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር እንዲሁም ምክትላቸው ጄኔፈር ቢቶንድ ከሥራ ገበታቸው አልተሰናበቱም ብሏል።
ድርጅቱ ይህን መግለጫ ያወጣው በትግራይ ክልል ለእርዳታ ተብሎ የተላከ ምግብ ለገበያ መቅረቡን ተከትሎ የእርዳታ አቅርቦቱን በማቆም ምርመራ ተካሂዶ ውጤቱ ይፋ ከመደረጉ በፊት የድርጅቱ የኢትዮጵያ ኃላፊዎች የሥራ መልቀቂያ እስገብተዋል የሚል ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ ነው።
ነገር ግን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር እረፍት ላይ እንጂ አሁንም የድርጅቱ ሥራተኛ ናቸው ያለ ሲሆን፣ ምክትላቸው ጄነፈር ቢቶንዴ በሥራ ገበታቸው ላይ ያሉ መሆናቸውን በማመልከት ከድርጅቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ሥራ የለቀቀ ከፍተኛ ኃላፊ አለመኖሩን ጨምሮ ገልጿል።
ከፍተኛ መጠን ያለው ለተረጂዎች የተላከ የእርዳታ ምግብ ለገበያ ቀርቦ መገኘቱን ተከትሎ በትግራይ ያደርግ የነበረውን የምግብ እርዳታ አቅርቦት ሥራውን ከአንድ ወር በፊት ማቋረጡን ድርጅቱ መግለጹ ይታወሳል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሚያቀርበው ድጋፍ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ብቻ መድረሱን ማረጋገጥ የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።
ሚያዚያ 2015 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ ማቋረጡ አሳውቋል።
ድርጅቱ የእርዳታ ስርጭት ሥራውን ያቋረጠው ለተረጂዎች በሚቀርብ የምግብ እርዳታ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ስርቆት ለማጣራት ውሳጣዊ ምርመራ ለማካሄድ እንደሆነ አራት የእርዳታ ሠራተኞች ለአሶሺየትድ ፕሬስ ተናግረው ነበር።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የእርዳታ ስርጭት ሥራውን ስለማቋረጡ ከመገለጹ በፊት በትግራይ ክልል በሚያካሂደው የሕይወት አድን የእርዳታ ሥራ ላይ የተፈጸመ የምግብ አቅርቦት ስርቆትን እየመረመረ እንደሚገኝ ተገልጾ እንደነበርም ይታወሳል።
የዚህ ምርመራ ውጤት እስካሁን ይፋ ባይደረግም ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ የድርጅቱ ሠራተኞች በክልሉ እንደሚገኙ ገልጾ፤ የእርዳታ አቅርቦት ሥራውን ግልጽነት በተሞላበት መልኩ በአስቸኳይ ለመጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት መሥራቱን ይቀጥላል ብሏል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ትናንት ሰኞ በትዊተር ገጻቸው ላይ የምግብ እርዳታ ላልተፈለገለት ዓላማ የዋለበትን ሁኔታ በተመለከተ አስተዳደራቸው ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ይህን ያሉት ከአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን ጋር በመቀለ ውይይት ማድረጋቸውን በገለጹበት ጽሑፋቸው ነው።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ የምርመራውን ውጤት ይፋ እንደሚያደርጉ እና ለእርዳታ እህሉ መጥፋት ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙትን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ጨምረው ገልጸዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ከማድረሱ በተጨማሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን እርዳታ ጠባቂ አድርጓል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጨምሮ ሌሎች ሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ተጎጂዎችን ለመርዳት የምግብ እርዳታ ሲያደርሱ ቆይተዋል።
ከዓለም ምግብ ፕሮግራም በተጨማሪ የአሜሪካ መንግሥት የዓለም የልማት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤአይዲም በእርዳታ አቅርቦት ላይ ከሚፈጸም ስርቆት ጋር በተያያዘ በትግራይ የሚያካሂደውን የእርዳታ አቅርቦቱን ማቋረጡ ይታወሳል።
በዚህ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች የምግብ እርዳታ በመዝረፍ እና ለተዋጊዎቻቸው በማቅረብ ሲከሰሱ እንደነበር ይታወሳል።