ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታጣቂዎች የጋምቤላ ከተማን በከፊል ተቆጣጥረው እንደነበረ ክልሉ ገለጸ
ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ ላይ ዛሬ ማክሰኞ ማለዳ ላይ ጥቃት ከፍተው የከተማዋን የተወሰነ ክፍል ተቆጣጥረው እንደነበረ የክልሉ መንግሥት ገለጸ።
የክልሉ መስተዳደር ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በጋምቤላ ከተማ “የሸኔ እና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር” በጋራ ጥቃት ከፍተው እንደነበረና ከረፋድ አራት ሰዓት በኋላ መጠነኛ መረጋጋት እንዳለ አመልክቷል።
በታጣቂዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ዛሬ ማክሰኞ ከማለዳ ጀምሮ በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ በክልሉ የፀጥታ አባላት እና በታጣቂዎቹ ላይ ጉዳት መድረሱንም የቢቢሲ ምንጮች ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ መስተዳደር ስለተከሰተው ሁኔታ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በሰጡት መግለጫ እናዳሉት፣ በጋምቤላ ከተማ ያጋጠመው የፀጥታ ችግር የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።
ከተማዋም በአሁኑ ጊዜ በክልሉ የፀጥታ ኃይል ቀጥጥር ስር ሙሉ ለሙሉ መግባቷን አቶ ኡሞድ ገልጸው፣ ታጣቂዎቹ የከፈቱትን ጥቃት ተከትሎ የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ “በታጣቂዎቹ ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ መድረሱን” አመልክተው በፀጥታ ኃይሉ ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።
በጋምቤላ ከተማ ማክሰኞ ሰኔ 07/2014 ዓ.ም. ከንጋት 11 ሰዓት ተኩል ገደማ ጀምሮ ለሰዓታት የቆየ ከባድ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ እንደነበርና ከፊል የከተማዋ ክፍልም በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር መግባቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
አንድ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣን ክስተቱ በጋምቤላ ከተማ ውስጥ ማጋጠሙን አረጋግጠው፣ በዚህም የሰው ህይወት መጥፋቱንና የተጎዱ መኖራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የክልሉ ባለሥልጣን ከዕኩለ ቀን በፊት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቢያንስ ሁለት የፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም ከታጣቂዎቹ የሦስቱ ህይወት ማለፉን ከሆስፒታል ምንጮቻቸው መረዳታቸውን ተናግረዋል።
ክልሉ ማክሰኞ ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ በጥቃቱ መካከል የደረሰው ጉዳት በውል እንደማይታወቅ አመልክቶ በታጣቂዎችና በፀጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጾ ነበር።
ዛሬ ማለዳ ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የተኩስ ልውውጥ “ያለማቋረጥ እስከ ረፋዱ 4 ሰዓት ከ20 ድረስ ሲካሄድ ቆይቶ” አሁን በከተማዋ ውስጥ መረጋጋት እንደሚታይና “የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ባካሄደው ብርቱ ትግል ከተማውን በከፊል ነፃ ማውጣት እንደተቻለ” ክልሉ ገልጿል።
ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት በዚሁ ክስተት ሳቢያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የንግድ ሥራዎች ብሎም ሌሎች መደበኛ እንቅስቃሴዎች የተስተጓጎሉ ሲሆን ነዋሪዎችም በቤታቸው ዘግተው መቀመጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ክስተቱን በሚመለከት ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ ላይ የከተማው ነዋሪ ኅብረተሰብ ከቤት ባለመውጣት የፀጥታ ኃይሉ እያደረገ ላለው የሕግ ማስከበር ተግባር የበኩሉን እንዲወጣ ተጠይቋል።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ አካባቢም ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ላለፉት አስከ ረፋድ አራት ሰዓት ድረስ ሲሰማ እንደነበረ አንድ በአቅራቢያው የነበሩ ነዋሪ ጠዋት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በከተማዋ ስለተከሰተው የተኩስ ልውውጥና አሁን ስላለው ሁኔታ “ምንም የምንሰጠው መረጃ የለም’’ ሲሉ ረፋድ ላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ተጨማሪ መረጃ ከርዕሰ መስተዳደሩ ለማግኘት ቢጠይቅም ለጊዜው ከዚህ ያለፈ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
በዚህም የከተማዋን የተወሰነ ክፍል ታጣቂዎቹ መቆጣጠራቸውን ብሎም የጥቃቱ ኢላማ የርዕሰ መስተዳደሩን ጽህፈት ቤት ለመቆጣጠር ያለመ ሳይሆን እንደማይቀር የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በተኩስ ልውውጡ በርካቶች መቁሰላቸውን ብሎም ታጣቂዎቹ ከርዕሰ መስተዳደሩ ጽህፈት ቤት በተጨማሪ በተለምዶ ቤተ መንግሥት የሚባለውን የርዕሰ መስተዳደሩን መኖሪያ ቤት እንዲሁም የነዳጅ መከማቻ ዴፖ ለመቆጣጠር ጥቃት ከፍተው እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የክልሉ ባለሥልጣንም ጥቃቱን በሚመለከት “ለፌደራል መንግሥት አሳውቀናል። ከአቅራቢያ ወደ ከተማው ኃይል ለማሰማራት እየሞከሩ እንደሆነ ነግረውናል። እዚህ ያለው ኃይላቸው ግን ትንሽ ነው’’ ሲሉ ማክሰኞ ጠዋት ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት አንድ የከተማው ነዋሪ ከባሮ ወንዝ ተሻግሮ ያለው የከተማው ክፍል በታጣቂዎች ቁጥጥር ስለሆነ ጠዋት ከባሮ ማዶ ተሻግረው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
“ከአራት ቀን በፊትም ተመሳሳይ ሙከራ ተደርጎ ነበር። ከዚህ በፊት በዚህ መጠን የታጣቂዎች እንቅስቃሴ አይተን አናውቅም ነበር’’ ሲሉም ነዋሪው አክለዋል።
መንግሥት በሽብርተኝነት የሰየመውና ኦነግ-ሸኔ የሚለው፣ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሲል የሚጠራው ታጣቂ ቡድን የሕዝብ ግንኙነት ኦዳ ተርቢ የተሰኘው ግለሰብ በትዊተር ገጹ ሠራዊቱ ከጋምቤላ ነጻነት ግንባር ጋር በመሆን በጋምቤላ ከተማ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደ ነው ብሏል።
ይኸው ገጽ አክሎም ከጋምቤላ በተጨማሪም በምዕራብ ኦሮሚያ በደምቢ ዶሎ ተመሳሳይ ወታደራዊ ዘመቻ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
የጋምቤላ ክልል በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የሚዋሰን ሲሆን፣ ታጣቂዎች ይንቀሳቀሱባቸዋል ከሚባሉት ከምዕራብ ኦሮሚያ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ጋር ይዋሰናል።
በተለያዩ ጊዜያት ከጎረቤት አገር ሱዳን ዘልቀው የሚገቡ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙ እንደነበረም አይዘነጋም።