ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ያለ እውነተኛ የተኩስ አቁም ንግግሮች ፍሬ አልባ ናቸው- ጄነራል አል ቡርሃን
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሳዑዲ አረቢያዋ ከተማ ጅዳ እያደረጉት ያለው ንግግር ሶስተኛ ቀኑን ቢያስቆጥርም ስለተደረሰበት ሁኔታ ዝርዝር መረጃዎች እየወጡ አይደለም።
በሁለቱ ኃያላን ጦሮች መካከል እየተደረገ ያለውንም የሽምግልና ሂደት ሳዑዲ አረቢያና አሜሪካ በጋራ እየመሩት ይገኛሉ።
በዚህም መካከል የሱዳኑ ጦር መሪ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ለግብጹ አልቃሂራ ኒውስ ሰኞ እለት እንደተናገሩት “ያለ እውነተኛ የተኩስ አቁም ስምምነት በሳዑዲ አረቢያ በድርድር ጠረጴዛ ላይ መቀመጥ ምንም ጥቅም የለውም” ብለዋል።
ጄነራል አል ቡርሃን ደም መፋሰስን ለማስቆም የሚደረጉ የትኞቹንም ጅምሮች በሙሉ በደስታ እንደሚቀበሉ ገልጸው ነገር ግን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሳሪያዎቹን ማስረከብ አለበት ብለዋል።
ሚያዝያ 28/ 2015 ዓ.ም በጅዳ የተጀመረው የቅድመ ድርድር የሰላም ንግግር ምንም አይነት እድገት እንዳላሳየ አንድ የሳዑዲ ዲፕሎማት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የአሜሪካ እና የሳዑዲ አረቢያ መንግሥታት “ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ለአገሪቷ እና ለሱዳን ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ግጭቱን ለማስቆም በሚደረገው ውይይት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ፤ ይህም ሁኔታ ለተቸገረው ሕዝብ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ የሚያረጋግጥና የሱዳንን ሕዝብ ስቃይና መከራ የሚታደግ መሆኑን” አሳስበዋል።
የሱዳን ግጭት ሚያዝያ 7/ 2015 ዓ.ም ከተቀሰቀሰበት ጀምሮ በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደረስም ሁለቱም ኃይሎች ተፈጻሚ ሊያደርጉት አልቻሉም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የተለያዩ የረድዔት ድርጅቶች በሱዳን ጦርነት ያስከተለው ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ እልባት እንዲያገኝ ጥሪ እያደረጉ ይገኛሉ።
ለሦስት ሳምንታት ያህል በቀጠለው ከባድ ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን ወደ 450 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎችም ቀያቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል።
ከነዚህም ውስጥ ከ115 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት ሃገራት እንደተሰደዱም ከተመድ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የሚሊዮኖች ሕይወት ስጋት ውስጥ በገባበት በዚህ ግጭት መሃል ሁለት ጄኔራሎች በባላንጣነት በጽንፍ ስፍራ ተቀምጠዋል።
የሱዳን ጦር ኃይል አዛዥና አገሪቷን እያስተዳደሩ ያሉት አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ከፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ ጋር በመረረ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ገብተዋል።