ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ወደ ቺካጎ ወታደሮችን ለመላክ ማቀዳቸው ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ነው በሚል ተተቸ
የኢሊኖይ ግዛት ገዥ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ቺካጎ ወታደሮችን የመላክ ውጥን ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ነው ሲሉ ተቹ።
ጄቢ ፕሪዝከር የአገሪቱ ብሔራዊ ዘብ እንዲሰማራ የሚያደርግ ምንም አደጋ የለም ያሉ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ "ቀውስ ለመፍጠር እየሞከሩ ነው" ሲሉ ባወጡት መግለጫ ከስሰዋል።
ትራምፕ በዲሞክራቶች በምትመራው በዋሽንግተን ዲሲ እስካሁን ሁለት ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን ያሰማሩ ሲሆን፣ በአሜሪካ ከተሞች ወንጀልን ለመቀነስ ቃል ገብተዋል።
ባለፈው አርብ ትራምፕ ፖሊሲያቸውን በዲሞክራቶች እጅ ሥር በሆኑት ቺካጎ እና ኒው ዮርክ ከተሞች እንደሚተገብሩ አስታውቀዋል።
የቺካጎ ከተማ ከንቲባ ብራንደን ጆንሰን ለፕሬዚዳንቱ ዕቅድ ምላሽ ሲሰጡ የብሔራዊ ዘብ ወደ ቺካጎ እንደሚሰማራ መረጃ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል።
የከተማዋ አስተዳደር በወታደሮች መሰማራት ላይ "ከባድ ስጋት" እንዳለው ገልፀው፤ የፕሬዝዳንቱን እንቅስቃሴ "ያልተቀናጀ፣ጥያቄ ያልቀረበበት እና የማይመስል" ሲሉ በይነውታል።
ከንቲባውም አክለውም "ሕገ ወጥ ማሰማራት" በነዋሪዎች እና በሕግ አስከባሪዎች መካከል ውጥረት ሊፈጥር ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀው፤ ከተማዋ ወንጀልን ለመቀነስ የተጓዘችበትን ሂደትም ወደ ኋላ ይመልሳል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትራምፕ አስተዳደር በዋሺንግተን ዲሲ "ከቁጥጥር ውጭ" ሲል የገለፀውን ወንጀል ለመከላከል የተሰማሩት የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች መሣሪያ እንዲታጠቁ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግዝ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ባለፈው ሳምንት የመከላከያ መስሪያ ቤቱ ፔንታጎን እና የአገሪቱ ጦር በዲሲ የተሰማሩት እና ሁለት ሺህ የደረሱት ወታደሮች መሣሪያ እንደማይዙ ተናግረው ነበር።
የትራምፕ አስተዳደር ተልዕኮውን ቢያሞካሽም፤በዲሞክራቶች በምትመራው ዋሺንግተን በሕዝብ እንዳልተወደደ የሚያሳዩ የዳሰሳ ጥናቶች እየወጡ ነው።
ፔንታጎን ባወጣው መግለጫ የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች ተልዕኳቸውን ለማስፈፀም በቅርቡ ለአገልግሎታቸው የተፈቀዱ የጦር መሣሪያዎችን ይዘው ይንቀሳቀሳሉ ብሏል።
የወታደሮቹ መሣሪያ ታጥቆ የመንቀሳቀስ ውሳኔ ብሔራዊ ዘቡ በዋሽንግተን ከተማ የተሰጠው ተልዕኮ መቀየሩን የሚያሳይ ለመሆኑ ግልፅ አይደለም።
እስካሁን ድረስ ወታደሮቹ በሕግ ማስከበር ዘመቻዎች አካል ሆነው ያልተሳተፉ ሲሆን፤ ለዋሽንግተን ዲሲ ምልክት በሆኑ በዋናነት የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ተመድበዋል።
የዋሽንግተን ዲሲ ከንቲባ ሙሬል ባውሰር እስካሁን በውሳኔው ዙሪያ አስተያየት አልሰጡም።
በዋይት ሐውስ ኦቫል ኦፊስ ንግግር ያደረጉት ትራምፕ፤ተልዕኮው በዋሽንግተን "ሙሉ ለሙሉ ደኅንነት" አምጥቷል ያሉ ሲሆን ይህ እርምጃ ወደ ቺካጎ ይስፋፋል ብለዋል።
ትራምፕ የተመደቡ ወታደሮችን ከጎበኙ በኋላ "ዲሲ ገሀነም ነበረች" ያሉ ሲሆን፤ "አሁን ግን ደኅንነት አለ" ብለዋል።
በሚቀጥሉት ሳምንታት 1,700 የሚሆኑ የብሔራዊ ዘብ ጠባዊዎች በ19 ግዛቶች እንደሚሰማሩ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች የኢምግሬሽን እና ጉምሩክ አስፈፃሚዎችን እንደሚያግዙ እና ወንጀልን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ ተነግሯል።