የኢራኑ ፕሬዝዳንት ጎረቤቶቻቸውን ይቅርታ የጠየቁት ለምንድን ነው?

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ቅዳሜ ጠዋት የአገሪቱ ጊዜያዊ አመራር አካል ሆነው ባደረጉት ንግግር በጎረቤት አገራት ላይ ከኢራን በኩል ለተፈጸሙ ጥቃቶች ይቅርታ በመጠየቅ ብዙ ታዛቢዎችን አስገርመዋል።

በአገራት መካከል ይቅርታ መጠያየቅ የተለመደ አይደለም። በተለይ ፈግሞ በግጭት ውስጥ እያሉ ጠንከር እና መረር ያሉ የቃላት አጠቃቀሞች የተለመዱ ናቸው። መሪዎች አንዳንድ ጊዜ "ጸጸትን" ይገልጻሉ ወይም ራሳቸውን ከኃላፊነት ያርቃሉ።

ፔዜሽኪያን በምትኩ ጎረቤት አገራት በቀጥታ ዒላማ መሆናቸውን ገልጸው የኢራን ጦር በአገሪቱ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ከግዛታቸው ካልመጣ በስተቀር ጥቃቱን እንዲያቆም ታዝዟብለዋል።

"ጥቃት ለደረሰባቸው ጎረቤት አገራት ይቅርታ መጠየቅ አስፈላጊ ይመስለኛል" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፤ "ጎረቤት አገራትን የመውረር ሃሳብ የለንም።"

ይህ ብቻ የመጀመሪያውን ጥያቄ ያስነሳል። በእርግጥ እውነተኛ ይቅርታ ነበር፣ እና ለምን አሁን?

አንዱ መልስ ጊዜያዊ አመራሩ እየሰፋ የመጣውን የቀጣናውን ችግር ለመቆጣጠር እየሞከረ መሆኑ ነው።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል በጋራ በጀመሩት ጥቃት ምክንያት በቀጣና ውስጥ ያሉ አንዳንድ አገራት ሳያስቡበት በግጭቱ ውስጥ ተገኝተዋል።

ፔዜሽኪያን እነዚህ ጥቃቶች የተፈጸሙት የመጀመሪያው ጥቃት ከፍተኛ የኢራን አዛዦችን ከገደለ እና የማዕከላዊ ዕዝ መዋቅሮችን ካወከ በኋላ "ይሆናል ወደምትሉት ተኩሱ" በሚል መመሪያ መሠረት የተፈጸሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይቅርታ በመጠየቅ፣ ቴህራን ጦርነቱን ወደ ሰፊ ቀጣናዊ ግጭት ማዛመት እንደማትፈልግ ለማሳየት እየሞከሩ ሊሆንም ይችላል።

መልዕክቱ በተዘዋዋሪ የፖለቲካ እውነታን ያረጋግጣል። አንዳንድ የጎረቤት አገራት የአሜሪካ ኃይሎች በግዛታቸው ላይ ካሉ የጦር ሰፈሮች እንዲንቀሳቀሱ ቢፈቅዱም፣ ኢራን በግልጽ ዒላማ ካደረገቻቸው ራሷን የበለጠ ታገላለች።

ነገር ግን ይቅርታው ወደ ፖሊሲ ይተረጎማል ወይ የሚለው ብዙም ግልጽ አይደለም።

ከቀጣናው የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከኢራን ወይም ከጦር ኃይሏ ጋር የሚያያዙ ጥቃቶች እስካሁን አላቆሙም። ኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ዒላማ ያደረጓቸውን ሚሳኤሎች ማምከናቸውን ተናግረዋል።

እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች ከቀጠሉ፣ በኢራን የተፍረከረከ የአመራር መዋቅር ውስጥ ስላለው ቁጥጥር ጥያቄ ያስነሳል።

የአገሪቱ የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ጨምሮ ቁልፍ አመራሮች ከገደሉበት የመጀመሪያው የጥቃት ማዕበል ጀምሮ፣ የውሳኔ አሰጣጡ ወደ ጊዜያዊ የመሪዎች ምክር ቤት ተሸጋግሯል።

በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ይህ መዋቅር እንደ ፔዜሽኪያን ያሉ ባለሥልጣናት በአንድ የበላይ አመራር በሚመራ ሥርዓት ውስጥ ከነበራቸው የበለጠ ተጽእኖ ይሰጣቸዋል።

በተግባር ግን፣ እንደ አብዮታዊው ዘብ ያሉ ጠንካራ ወታደራዊ እና የደኅንነት ተቋማትን የመቆጣጠር አቅማቸው ላይ አሁንም እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

ከፕሬዝዳንቱ መግለጫ በኋላም ኢራን በጎረቤት አገራት ላይ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች ከቀጠሉ፣ የግጭቱን መጠን ለመቀነስ ፈቃደኛ ካልሆኑ ወገኖች ጋር የመረጃ ፍሰት ችግር ወይም ተቃውሞ መኖሩን ይጠቁማል።

በደኅንነት ተቋሙ ውስጥ ያሉ አክራሪ አካላት ለረዥም ጊዜ አገራቸው የአሜሪካን እና የእስራኤልን ወታደራዊ ኃይል ለመቃወም ቀጠናው ላይ የምትፈጥረው ጫና ወሳኝ እንደሆነ ሲከራከሩ ቆይተዋል።

በአገር ውስጥ ያሉ ምላሾችም ያንን ውጥረት ያንፀባርቃሉ። አንዳንድ አክራሪ ብሔርተኞች የፔዜሽኪያንን አስተያየት ደካማ ሲሉ ተችተዋል።

በኢራን ውስጥ ያለው አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታ ያልተለመደ ነው፤ በሥርዓቱ አናት ላይ የነበሩት ጠንካራ የመወሰን አቅም ከነበራቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ተገድለዋል። ዝቅ ባለ የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙት ባለሥልጣናት እና አዛዦች ደግሞ ማንኛውንም ወደ መሃል የሚያመጣ አስተያየት በእጅጉ ይጠራጠራሉ።

ለእነሱ የሌላ አገር መንግሥታትን ይቅርታ መጠየቅ በብሔራዊ ቀውስ ወቅት እንደ እጅ መስጠት የመታየት አደጋ አለው።

ከኢራን ውጪ የፕሬዝነንቱ ምላሽ በተለያየ ሁኔታ ተተርጉሟል። ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ኢራን ጎረቤቶቿን "ይቅርታ ጠይቃ እጅ ሰጥታለች" በማለት የጻፉት ወዲያውኑ ነበር።

የፕሬዝዳንቱ ይቅርታ የአሜሪካ እና የእስራኤል ወታደራዊ ጫና እየሠራ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ሲሉም አክለዋል።

ይህ አስተያየት ዋሽንግተን የቴህራንን መልዕክቶች እንዴት ልትተረጉም እንደምትችል ያሳያል። ትራምፕ በተደጋጋሚ ተቀባይነት ያለው ብቸኛው ውጤት የኢራን "ሙሉ በሙሉ እጅ መስጠት" እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህ ፍላጎት ደግሞ የዲፕሎማሲያዊ ግራ መጋባት ይፈጥራል።

በታሪክ የቦምብ ድብደባው ምን ያህል ከባድ ቢሆን፣ አገራት በአየር ድብደባዎች ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እጅ መስጠትን አይቀበሉም። ያለ እግረኛ ጦር እንዲህ ዓይነቱን ውጤት ማምጣት እጅግ በጣም ከባድ ነው።

ስለዚህ የፔዜሽኪያንን ይቅርታ እንደ እጅ መስጠት መተርጎም ለዋሽንግተን የፖለቲካ ድልድይ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፤ ይህም የእጅ ስጡ ጥያቄን በይፋ ሳይተዉ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ለመናገር ጥሩ መንገድ ነው።

ለፔዜሽኪያን እና ለጊዜያዊ የአመራር ምክር ቤቱ ደግሞ ስሌቱ የተለየ ሊሆን ይችላል።

አሁን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ አዲስ ቋሚ መሪ ከመምጣቱ በፊት ሁኔታውን ሊያረጋጋ ይችላል።

የኢራንን የፖለቲካ ሥርዓት የሚቆጣጠረው ቀጣዩ ሰው ጠንካራ የሃይማኖት መሪ ከሆነ የዲፕሎማሲ ተስፋው የበለጠ ጠባብ ሊሆን ይችላል።

ይህ አጋጣሚ ሌላ ቁልፍ ጥያቄ ያስነሳል። ፔዜሽኪያን እንደ ተደራዳሪ፣ የምዕራባውያን መንግሥታት ሊቀበሏቸው የሚችሉ ለዘብተኛ መሪ አድርገው ራሳቸውን እያቀረቡ ነው?

በንግግራቸው ለጎረቤት አገራት ከጥቃት መታቀብን ቢያሳዩም፣ በእምቢተኝነት እና በግልጽነትን መካከል ሚዛናዊ ለመሆን ሞክረዋል።

በተመሳሳይ የኢራን የወደፊት አመራር በሚመለከት የሚደረገው ትግል ቅርፅ መያዝ ጀምሯል።

የተለያዩ የፖለቲካ እና የሃይማኖት መሪዎች፣ እንዲሁም በአብዮታዊ ዘብ እና በፀጥታ ኃይሎች ውስጥ ያሉ አዛዦች፣ ይህንን የጦርነት አቋማቸውን ለማጠናከር ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን አድርገው ሊመለከቱት ይችላሉ።

አንዳንዶች የባለሙያዎች ጉባኤ የሚቀጥለውን መሪ በፍጥነት እንዲመርጥ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

ፔዜሽኪያን መረጋጋትን ማስፈን ወይም በጦር ኃይሎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ካልቻሉ፣ ተቀናቃኞቻቸው የበለጠ ጠንካራ አካሄድ እንደሚያስፈልግ ሊያቀርቡ ይችላሉ።

ለጊዜው የአገሪቱ አሁናዊ ፈተና ያለው ከኢራን ድንበር ውጪ ነው።

እስካሁን ድረስ ብዙ ጎረቤት አገራት ይቅርታውን መሬት ላይ እውነተኛ ለውጦችን ያመጣ እንደሆነ ለማየት በጥንቃቄ ምላሽ ሰጥተዋል ወይም ዝም ብለዋል።

ይህንን ጦርነት ለረዥም ጊዜ ስጋት አድርጋ ታየው የነበረውን አገዛዝ ለማዳከም እንደ ጥሩ አጋጣሚ ለምትመለከተው እስራኤል፣ መልዕክቱን ፍጥጫ ለማርገብ የመፈለግ አድርጋ የመተርጎም ዕድሏ አነስተኛ ሊሆን ይችላል።

አሻሚነቱ ሆን ተብሎ ሊሆን ይችላል።

የፔዜሽኪያን ይቅርታ ለብዙ ትርጓሜዎች የተጋለጠ ነው።

ይህም የቀጣናውን ውጥረት ለማረጋጋት የሚደረግ እውነተኛ ሙከራ፣ ለኢራን ጊዜያዊ አመራር ጊዜ ለመግዛት የሚደረግ ስልታዊ እርምጃ ወይም በቴህራን ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ የመክፈቻ ምልክት ሊሆን ይችላል።

በውስጥ የኃይል ሽኩቻ እና ከውጪ በተከፈተባት ጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ኢራን ሦስቱም ምክንያቶች ይሰራሉ።