በአሜሪካ በኢስላሚክ ስቴት ተነሳስቶ 15 ሰዎችን ገጭቶ ገድሏል ስለተባለው ግለሰብ ምን እናውቃለን?

ሻምሱድ-ዲን ጃባር

የፎቶው ባለመብት, FBI

በኢስላሚክ ስቴት ቡድን ተነሳስቷል የተባለ ግለሰብ በአሜሪካዋ ኒው ኦርሊየንስ ከተማ ባደረሰው ጥቃት 15 ሰዎች ሲገደሉ 35 የሚሆኑ ቆስለዋል።

ግለሰቡ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ በሉዊዚያና ግዛት ሰዎች በተሰበሰቡበት ነው ጥቃቱን ያደረሰው ሲሉ ባለሥልጣናት ገልፀዋል።

ለመሆኑ ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ ማነው?

ጥቃቱ እንዴት ደረሰ?

በአካቢቢው ሰዓት አቆጣጠር ከለሊቱ 9፡15 ገደማ ነው አንድ ክፍት መኪና እየፈጠነ መጥቶ በርበን መንገድ አካባቢ ተሰባስበው የነበሩ ሰዎች ላይ የወጣው።

የሲሲቲቪ ምስሎች እንደሚያሳዩት ጥቃት አድራሹ ሲነዳው የነበረው ነጭ ፎርድ ኤፍ-150 ላይትኒንግ የተባለ ከኋላው ክፍት የሆነ መኪና ነው።

ፖሊስ ድርጊቱን "ሆነ ተብሎ የተፈፀመ" ብሎ ሻምሱድ-ዲን ጃባር የተባለው ጥቃት አድራሽ "ድርጊቱን የፈፀመው እንዲህ አይደነት ጉዳት ለማድረስ አቅዶ ነው" ሲል ገልፆታል።

የኒው ኦርሊየንስ ፖሊስ ኃላፊ አና ከርክፓትሪክ "ግለሰቡ በመኪናው የተቻለውን ያክል ሰው እየገጨ መሄድ ነበር የፈለገው" ብለዋል።

ጃባር የጦር መሣሪያ የታጠቀ እንደነበር ተነግሯል። ግለሰቡ ፖሊስ ላይ ተኩሶ ሁለት መኮንኖችን አቁስሏል። ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት እዚያው አደጋው የደረሰበት ስፍራ መገደሉም ተነግሯል።

በሉዊዚያና አካባቢ ከጓደኞቹ ጋር ሲዝናና የነበረው ዊት ዴቪስ ከጥቃቱ በኋላ አንድ መጠጥ ቤት እንዳለ ፖሊስ ከቦ እንዲረጋጉ እንዳደረጋቸው ለቢቢሲ ይናገራል።

ፖሊሶቹ ወደ አደጋው ስፍራ ሲሄዱ "በሞቱ እና በተጎዱ ሰዎች መካከል እየተራመዱ ነበር" ሲል አክሏል።

ሻምሱድ-ዲን ጃባር ማነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኤፍቢአይ ጥቃቱን ያደረሰው የ42 ዓመቱ የቴክሳስ ነዋሪ የሆነ አሜሪካዊ ዜጋ እና የቀድሞ ወታደር ሻምሱድ-ዲን ጃባር ነው ብሏል።

ጥቃት ባደረሰበት መኪና ላይ የኢስላሚክ ስቴት ባንዲራ ተሰቅሎ እንደነበር የተነገረ ሲሆን ኤፍቢአይ ጃባር ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር ምን ግንኙነት ነበረው የሚለውን እየመረመረ እንደሆነ አስታውቋል።

አደጋው በደረሰበት አካባቢ ቤት ውስጥ የተሰሩ ፈንጂዎችም ተገኝተዋል። ማፈኚያ የተገጠመለት ረዥም የጦር መሣሪያም በቁጥጥር ሥር ውሏል።

አሁን የተወገደ የግለሰቡ ነው የተባለ የሊንክድኢን ገፅ እንደሚያሳየው ጃባር ከሠራዊቱ ከመሰናበቱ በፊት በአሜሪካ ጦር የሰው ኃይልና የአይቲ ባለሙያ ሆኖ አገልግሏል።

በፈረንጆቹ የተካቲት 2009 እና ጥር 2010 ወደ አፍጋኒስታን ለግዳጅ ተልኮም እንደነበር ተጠቁሟል።

በ2020 ዩቲዩብ ላይ በተለጠፈ ቪድዮ ከጦር ሠራዊቱ ጋር የነበረው ጊዜ "የማገልገልን ትርጉም ያወቅኩበት፤ ነገሮችን ከልብ መውሰድ እና ምላሽ መስጠት ምን እንደሆነ የተማርኩበት" ነበር ሲል ይገልፃል።

ከ2015-2017 ባለው ጊዜ ጆርጅ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተምሮ በኮምፒውተር ኢንፎርሜሽን ሲስተም ድግሪ ተመርቋል።

በሪል ስቴት ዘርፉም እንደሰራ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። የትራፊክ ሕግ በመጣስ እና ከስርቆት ወንጀል ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም ስሙ የሕግ መዝገብ ላይ ሰፍሯል።

ጥቃቱን ያደረሰበት መኪና በኤሌክትሪክ የሚሠራ እና ቴክሳስ ውስጥ የተከራየው ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል።

ጆ ባይደን ከጥቃቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ስለአደጋው ዝርዝር መረጃ ከኤፍቢአይ እንደተቀበሉ ገልፀዋል። ተጠርጣሪው "ከጥቃቱ ጥቂት ሰዓታት በፊት" ቪድዮዎችን ማኅበራዊ ሚድያ ላይ መልቀቁን እና በኢስላሚክ ስቴት ተነሳስቶ "የመግደል ፍላጎት" እንደነበር ባይደን ተናግረዋል።

በኒው ኦርሊየንስ የደረሰው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሌሎች ተጠርጣሪዎች አሉ?

ኤፍቢአይ እንዳለው ተጠርጣሪው ጥቃቱን ያደረሰው በሰዎች ታግዞ ነው። በተለይ ደግሞ ፈንጂዎችን በመቅበር የተባበሩት ሰዎች አሉ።

ነገር ግን እኒህን ተባባሪዎች በተመለከተ ባለሥልጣናት እስካሁን የለቀቁት ማስረጃ የለም።

ሲቢኤስ እንደዘገበው ፖሊስ በአካባቢው የነበሩ የፀጥታ ካሜራዎችን እያጠኑ ቢሆንም ካሜራዎቹ የሚያሳዩት በስፍራው የነበሩ ሰላማዊ ዜጎችን ብቻ ነው።

ጥቃቱ የደረሰባቸው ሰዎች ስም ዝርዝር እስካሁን ይፋ አልተደረገም።

የጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት አንድ ተማሪያቸው ክፉኛ መጎዳቱን ተናግረዋል። እስራኤል ደግሞ ሁለት ዜጎቿ እንደተጎዱባት ገልፃለች።

ፖሊስ እንዳለው አብዛኛዎቹ ጉዳት የደረሰባቸው የኒው ኦርሊየንስ ነዋሪዎች ቢሆኑም አዲስ ዓመትን ለማክበር የመጡ ጎብኚዎች ሊኖሩ ይችላሉ።