የአዲስ አበባ እሳት አደጋ፡ በከተማዋ ካሉ 20 ሺህ ተቋማት አደጋ የመከላከል መስፈርት ያሟሉት 42 ብቻ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, FDRMC/FB
በአዲስ አበባ ከሚገኙ 20 ሺህ ተቋማት መካከል አደጋዎችን የመከላከል መስፈርት ያሟሉት 42 ብቻ እንደሆኑ የአዲስ አበባ እሳት አደጋ እና ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ይከፈለው ወልደመስቀል ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ አብዛኞቹ ሆቴሎች፣ ፋብሪካዎች፣ ሕንጻዎች፣ የነዳጅ ማደያዎች፣ የገበያ ማዕከላት፣ መጋዘኖችና ሌሎችም ተቋማት የአደጋ ደኅንነት መስፈርትን የሚያሟሉ አይደሉም።
"በየጊዜው በሚደረግላቸው የምክርና የቴክኒክ ድጋፍ መሻሻል ቢኖርም ብዙዎቹ የብቃት ማረጋገጫ መውሰድ የሚያስችል ደረጃ ላይ አይደሉም" ብለዋል።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መስፈርት ለሚያሟሉ ተቋሞች ማረጋገጫ እንደሚሰጥ የጠቀሱት አቶ ይከፈለው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በተከታታይ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ተቋማት ላይ ምርመራ እንደተደረገ አስረድተዋል።
"ባለፉት 5 ዓመታት በጠቅላለው 20 ሺህ ተቋማት ተፈትሸዋል። ከእነዚህ [20 ሺህ የሚጠጉ ተቋማት] መካከል መስፈርት አሟልተው የብቃት ማረጋገጫ የወሰዱት 42 ብቻ ናቸው" ብለዋል።
የግል፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አደጋዎችን የመከላከል ብቃታቸው መፈተሹን ገልጸዋል። እነዚህም ማንኛውም አገልግሎት የሚሰጥባቸውና ብዙ ሕዝብ የሚንቀሳቀስባቸውን ተቋማት እንደሚያካትቱ አክለዋል።
አደጋዎችን የመከላከል መስፈርቶችን አለማሟላት አደጋዎች ሲከሰቱ ምላሽ የመስጠት ክፍተት እንደሚፈጥር የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ተናግረዋል።
"ስለ አደጋ ያለው ግንዛቤ ገና ከጊዜ ወደ ጊዜ ነው እያደገ የመጣው። በቂ የተሟላ ግንዛቤ አለ ብሎ መውሰድ አይቻም። ግንዛቤው እያለም የጥንቃቄ ክፍተቶች አሉ" ሲሉም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
"ለምሳሌ አንድ ሆቴል የእሳት አደጋ ገና እንደተፈጠረ መከላከል የሚያስችል ጅምር እሳት ማጥፊያ መሣሪያ ከሌለው የግድ እሳት አደጋ ሠራተኞች እስኪደርሱ ድረስ ያንን እሳት ሊከላከል የሚችልበት ምንም ዓይነት መንገድ የለውም" ብለዋል አቶ ይከፈለው።
የደኅንነት ባለሙያዎች በተቋማት ውስጥ እንዲኖሩ የሚያስገድድ መመሪያ ማውጣታቸውንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለምሳሌ የእሳት አደጋ መከላከለያ ጅምር መሣሪያዎች በተቋማት ካሉ የደኅንነት ባለሙያዎች ገና እሳቱ እንደተነሳ አደጋውን መቆጣጠር እንደሚችሉ አስረድተዋል።
እነዚህን መስፈርቶች ያላሟላ ሕንጻ ወይም አገልግሎት መስጫ ድርጅት "በጅምር ደረጃ እሳትን ማስቀረትና ተቋሙን ከጥፋት መታደግ አይችልም" ብለዋል።
ሌላው በምሳሌነት የጠቀሱት የአደጋ ጊዜ መውጫ ነው።
"የአደጋ ጊዜ መውጫ የሌለው ሕንጻ ወይም አገልግሎት መስጫ አደጋ በተፈጠረ ጊዜ ሰዎች ሊያመልጡ የሚችሉት ዕድል አይኖራቸውም" ሲሉ ገልጸዋል።
አደጋዎችን የመከላከል መስፈርቶችን አለማሟላት በተቋሙ ውስጥ የሚገለገሉ ማኅበረሰቦችን፣ የተቋሙ ባለቤቶችንና ባለሃብቶችን ለአደጋ እንደሚያጋልጥም ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ እና ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በሚሰጣቸው ድጋፍ መሻሻል ያሳዩ ተቀማት እንዳሉ አቶ ይከፈለው ቢገልጹም፣ ሙሉ በሙሉ መስፈርት እስከሚያሟሉ ድረስ ኮሚሽኑ የብቃት ማረጋገጫ እንደማይሰጣቸው ተናግረዋል።
"20 ሺህ ተቋማት ምንም ዓይነት የአደጋ መከላከለያ መሣሪያ የላቸውም ማለት አይደለም" ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ተቋማቱ የሚፈለገውን ዓለም አቀፍ ልኬት እንዳላሟሉ ገልጸዋል።
"በየሕንጻው ከሆነ በየሕንጻው፣ በሙሉ በገበያ ማዕከሉ ከሆነ በሙሉ በገበያ ማዕከሉ ባሉ ቦታዎች፣ ከጅምር እሳት ማጥፊያ ጀምሮ እስከ አደጋ ጊዜ መውጫና መሰብሰቢያ ድረስ ያሉትን በሙሉ አላሟሉም ማለት ነው እንጂ ምንም አላሟሉም ማለት አይደለም" ብለዋል።
መስፈርት በማያሟሉ ተቋማት ላይ በአደጋ ደኅንነት ደንብ ቁጥር 132/2014 መሠረት የሚወሰደው የመጀመሪያ ቅጣት እንደየተቋሙ ሁኔታ የሚወሰን ከ10ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሆነ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ተቋማት በተደጋጋሚ የተሰጣቸውን ማሳሰቢያ የማይተገብሩ ወይም በገንዘብ ቅጣት የማይታረሙ ከሆነ የንግድ ወይም የሥራ ፈቃዳቸው እንደሚሰረዝና ተቋሙን እስከማሳሸግም እንደሚሄዱም አክለዋል።












