ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በዓለም የውሃ እና የኤሌክትሪክ አቅርቦት ላይ ስጋት ደቅኗል? እንዴት?
የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ የዕለት ተዕለት ሕይወት አካል እየሆነ መጥቷል።
የማኅበራዊ ሚዲያ የምንመለከታቸውን ልጥፎች ግላዊ ለማድረግ፣ በስማርት ስልኮች ፎቶዎች ላይ ወዳጅ ዘመዶቻችንን ለመለየት እንዲሁም ለሕክምና ግኝቶች መንገዱን ለመክፈት ሥራ ላይ ይውላል።
ነገር ግን እንደ ኦፕን ኤአይ፣ ቻትጂፒቲ እና ሜታ ኤአይ ያሉ የቻትቦቶች መበራከት ቴክኖሎጂው ከሚኖረው የአካባቢ ተጽእኖ፣ የሥነ ምግባር አንድምታ እና የመረጃ አጠቃቀም ስጋት ጋር አብሮ መጥቷል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ መስኮች አዲስ ጥቅምን እየሰጠ ሲሆን፣ ወደፊትም የሚያስገኘው ትሩፋትም የበለጠ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ነገር ግን ጥያቄዎችም እየተነሱበት ነው።
ኤኤይ ምንድን ነው? ለምን ጥቅም ላይ ይውላል?
ኤአይ ኮምፒውተሮች ልክ የሰው ልጅ በሚያደርገው መንገዶች እንዲማሩ እና ችግሮችን እንዲፈቱ ያስችላቸዋል።
ኮምፒውተሮች ማሰብ፣ መረዳዳት ወይም ማመዛዘን አይችሉም።
ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶች ሰዎች እውቀትን እንዴት እንደሚያገኙ እና እንደሚጠቀሙ ለመድገም በመሞከር ብዙውን ጊዜ የሰዎችን የማሰብ ችሎታ የሚጠይቁ ተግባራትን ሊያከናውኑ የሚችሉ ሥርዓቶችን ፈጥረዋል።
የኤአይ ፕሮግራሞች ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃን ማካሄድ፣ የነገሮችን አካሄድ መለየት እና በመረጃው ምን እንደሚደረግ ዝርዝር መመሪያዎችን መከተል ይችላሉ።
ይህ አንድ የበይነ መረብ ሸማች ባደረጋቸው የቀደሙ ግዢዎች ላይ በመመሥረት ምን ዓይነት ምርት ሊገዛ እንደሚችል ለመገመት መሞከር ሊሆን ይችላል።
ቴክኖሎጂው እንደ አፕል ሲሪ እና አማዞን አሌክሳ ካሉ በድምፅ ቁጥጥር ስር ካሉ ቨርቹዋል ረዳቶች ጀርባ ያለ ሲሆን፣ አሽከርካሪ አልባ መኪኖችን ለማዘጋጀት ጥቅም ላይ ይውላል።
ኤአይ እንዲሁም እንደ ፌስቡክ፣ ቲክ ቶክ እና ኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ያሉ ማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ለተጠቃሚዎች ምን ዓይነት ልጥፎችን ሊያሳዩ እንደሚገባ እንዲወስኑ ይረዳል።
እንደ ስፖቲፋይ ያሉ የሙዚቃ ማሠራጫ አገልግሎቶች ሙዚቃን ለመጠቆም ኤአይን ይጠቀማሉ።
ሳይንቲስቶች ኤአይአይን ካንሰርን ለመለየት፣ ምርመራዎችን በአፋጣኝ ለማከናወን እና አዳዲስ መድኃኒቶችን ለመለየት እየተጠቀሙበት ነው።
በምሥሎች ውስጥ ያሉ ነገሮችን ወይም ሰዎችን እንዲለዩ የሚያስችል የኤአይ ዓይነት ደግሞ የኮምፒዩተር ዕይታ የራጅ ውጤቶችን ለመገምገም በራዲዮግራፈሮች ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።
አመንጪ (ጄነሬቲቭ) ኤአይ ምንድን ነው? እንዴትስ ይሠራል?
አመንጪ ኤአይ (Generative AI) በሰው የተሠራ ሊመስል የሚችል አዲስ ይዘት ለመፍጠር ጥቅም ላይ ይውላል።
ይህን የሚያደርገው በይነ መረብ ላይ ካሉ ጽሑፍ እና ምሥሎች እጅግ በጣም ብዙ ነባር መረጃዎችን በመማር ነው።
'ቻትጂፒቲ' እና የቻይናው ተቀናቃኝ 'ዲፕሲክ' ጽሑፍን፣ ምሥሎችን፣ ኮድን እና ሌሎችንም ነገሮች ለማፍለቅ የሚያገለግሉ ታዋቂ የአይአይ መሳሪያዎች ናቸው።
የጉግል ጄሚናይ ወይም ሜታ ኤአይ በተመሳሳይ መልኩ ከተጠቃሚዎች ጋር የጽሑፍ ውይይቶችን ማድረግ ይችላሉ።
እንደ ሚድጆርኒ (Midjourney) ወይም ቪዮ3 (Veo 3) ያሉ አንዳንድ መተግበሪያዎች ከቀላል የጽሑፍ ጥያቄዎች ምሥሎችን ወይም ቪዲዮዎችን መፍጠር የሚችሉ ናቸው።
ጀኔሬቲቭ ኤአይ ከፍተኛ ጥራት ያለው ሙዚቃ ለመሥራትም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።
የታዋቂ ሙዚቀኞችን ዘይቤ ወይም ድምጽ የሚመስሉ ዘፈኖች በብዛት ተሠርተዋል፤ አንዳንድ ጊዜ አድናቂዎች በእውነተኛነታቸው ግራ ይጋባሉ።
ኤአይ ለምን አከራካሪ ሆነ?
አንዳንድ ባለሙያዎች የኤአይን አቅም ቢገነዘቡም ፈጣን ዕድገቱ እና የሚኖረው አንድምታ ያሳስባቸዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ኤአይ ወደ 40 በመቶ የሚጠጉ ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እና የፋይናንስ ኢ-ፍትሐዊነትን ሊያባብስ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በኤአይ ልማት "ጥራሳቸውን የነቀሉ" እንደሆኑ የሚነገርላቸው የኮምፒዩተር ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሂንተን፣ ኃይለኛ የኤአይአይ ሲስተሞች የሰው ልጆችን ከምደረ ገጽ ሊያጠፉ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፤ ይህ ፍርሃት በሌላው "የኤአይ አባት" በያን ሊኩን ውድቅ ተደርጓል።
ተቺዎች በተጨማሪም የቴክኖሎጂው አድሏዊ መረጃን የማባዛት ወይም በአንዳንድ ማኅበራዊ ቡድኖች ላይ አድልዎ የማድረግ አቅምን አጉልተው ያነሳሉ።
ይህ የሆነበት ምክንያት አብዛኛው ኤአይን ለማሠልጠን ጥቅም ላይ የሚውለው መረጃ ከሕዝባዊ ነገሮች የተገኘ በመሆኑ ነው።
የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎችን ወይም አስተያየቶችን ጨምሮ፣ ይህም እንደ ፆተኝነት ወይም ዘረኝነት ያሉ አድሏዊ ድርጊቶችን ሊያንፀባርቅ ይችላል።
እንዲሁም የኤአይ ፕሮግራሞች የበለጠ እያደጉ ቢሄዱም አሁንም ለስህተት የተጋለጡ ናቸው።
የጄኔሬቲቭ ኤአይ ሥርዓቶች የሚታወቁት ውሸቶችን እንደ እውነት በማቅረብ እና በማስረገጥ ችሎታቸው ነው።
አፕል የዜና መተግበሪያ ማሳወቂያዎችን በተሳሳተ መንገድ ካጠቃለለ በኋላ አዲሱን የኤአይ ገጽ በጥር ወር አቁርጧል።
የአፕል ኤአይ የዩናይትድ ሄልዝኬር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሪያን ቶምፕሰንን በመግደል የተከሰሰው ሉዊጂ ማንጊዮን፣ ራሱን ገድሏል ብሎ አንባቢዎችን ካሳሳተ በኋላ ቢቢሲ ቅሬታ አቅርቧል።
ጎግልም በኤአይ የፍለጋ ዕይታዎቹ ባቀረባቸው የተሳሳቱ መልሶች ሳቢያ ትችት ገጥሞታል።
ይህ በትምህርት ቤቶች እና በሥራ ቦታዎች የኤአይ አጠቃቀምን በተመለከተ ስጋትን ጨምሯል፣ ይህም ጽሑፎችን ለማጠቃለል፣ ኢሜይሎችን ወይም መጣጥፎችን ለመፃፍ እና የበለጠ ጥቅም ላይ ይውላል።
ተማሪዎች የኤአይ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የቤት ሥራዎቻችውን "ስለሚኮርጁ" ወይም ሠራተኞች ወደ ሥራ "በድብቅ ስለሚያስገቡት" ስጋቶች አሉ።
ፀሐፊዎች፣ ሙዚቀኞች እና አርቲስቶችም የኤአይ አበልጻጊዎች ያለፈቃዳቸው እና ካሳ ሳይከፈላቸው ሥርዓታቸውን ለማሠልጠን ተጠቅመውበታል ሲሉ በቴክኖሎጂው ላይ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ከያኒያን የስዊዲኑ የፖፕ ባንድ 'አባ' ሙዚቀኛ ቢዩን ኤልቪየስ ጨምሮ፣ ደራሲያን ኢያን ራንኪን እና ጆአን ሃሪስ እና ተዋናይ ጁሊያን ሙር በጥቅምት 2024 ኤአይን በኑሯቸው ላይ "ዐቢይ፣ ኢፍትሐዊ ስጋት" በማለት መግለጫ አውጥተዋል።
ኤአይ በአካባቢ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
የኤአይ ሥርዓቶች ምን ያህል ኃይል እንደሚጠቀሙ ግልጽ አይደለም፤ ነገር ግን አንዳንድ ተመራማሪዎች በአጠቃላይ ኢንዱስትሪው ብዙም ሳይቆይ ከኔዘርላንድስ ፍጆታ ጋር የሚሰተካከል ኃይል ሊጠቀም እንደሚችል ይገምታሉ።
የኤአይ ፕሮግራሞችን ለማስኬድ የሚያስፈልጉትን ኃይለኛ የኮምፒዩተር ቺፖችን መፍጠር ብዙ ኃይል እና ውሃ ይጠይቃል።
የጄኔሬቲቭ ኤአይ አገልግሎቶች ፍላጎት ማደግ ማለት በሌላ መንገድ የዳታ ማዕከሎች ቁጥር መጨመር ነው።
በሺዎች የሚቆጠሩ የኮምፒዩተር ሰርቨሮችን በውስጣቸው የያዙት ግዙፍ መጋዘኖች፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል ይጠቀማሉ እና እንዲቀዘቅዙ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ይፈልጋሉ።
አንዳንድ ትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አስፈላጊውን ውሃ ለመቀነስ ወይም እንደገና ጥቅም ላይ ለማዋል ኢንቨስት አድርገዋል፤ ወይም እንደ አየር ማቀዝቀዣ ያሉ አማራጭ ዘዴዎችን መርጠዋል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ባለሙያዎች እና አክቲቪስቶች ኤአይ የውሃ አቅርቦት ችግርን ያባብሳል ብለው ይፈራሉ።
ለቢቢሲ በየካቲት ወር እንደደረሰው መረጃ ከሆነ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አገሪቱን በኤአይ "የዓለም ቁንጮ" ለማድረግ የያዘው ዕቅድ ቀድሞውንም የነበረውን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ሊያባብሰው ይችላል።
በመስከረም 2024 ጉግል ከድርቅ ጋር እየታገለች ባለቸው ቺሊ ለመገንባት ያቀደውን የመረጃ ማዕከል እንደገና እንደሚያጤን ተናግሯል።
ኤአይን የሚቆጣጠሩ ሕጎች አሉ?
አንዳንድ መንግሥታት ኤአይ እንዴት መሥራት እንዳለበት የሚቆጣጠሩ ሕጎችን አውጥተዋል።
የአውሮፓ ኅብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሕግ ከፍተኛ ስጋት ባለባቸው እንደ ትምህርት፣ ጤና አጠባበቅ፣ ሕግ ማስከበር ወይም ምርጫ ላይ የሚኖረው አተገባባር ላይ ቁጥጥር ያደርጋል።
በአንዳንድ ሁኔታዎች ኤአይ መጠቀምን ሙሉ በሙሉ ይከለክላል።
በቻይና ውስጥ ያሉ ጀነሬቲቭ ኤአይ አበልጻጊዎች የዜጎችን መረጃ ለመጠበቅ እና የመረጃ ግልጽነትን እና ትክክለኛነትን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን በአገሪቱ ጥብቅ የሳንሱር ሕግጋት የተያዙ ናቸው።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር መንግሥት "ኤአይን ከመቆጣጠሩ በፊት እንደሞክረው እና እንደሚረዳው" ተናግረዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ሁለቱም አደጋዎችን ለመለየት እና የላቁ የኤአይ ሞዴሎችን ለመገምገም ያለመ የኤአይ ደኅንነት ተቋማት አሏቸው።
በ2024 ሁለቱ አገራት "ጠንካራ" የኤአይ መፈተሻ ዘዴዎችን በማዘጋጀት ላይ ለመተባበር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ነገር ግን በየካቲት 2025፣ አንዳቸውም ቴክኖሎጂውን ክፍት፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂነት ያለው አቀራረብ ለማድረግ የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የኤአይ ስምምነት አልፈረሙም።
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ አገራት በዲፕፌክ እርቃን ምሥሎችን እና የልጆች ወሲባዊ ጥቃትን የሚፈጥሩ የኤአይ ሥርዓቶችን መጠቀምን ለመከላከል ጠንካራ እርምጃ እየወሰዱ ነው።