ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (ኤአይ) ሲጠቀሙ ራስዎን መጠየቅ ያለብዎ አራት ጥያቄዎች
የሂሳብ ትምህርት የቤት ሥራን ይሠራልዎታል። ለሥራ ቅጥር ቃለ መጠይቅ ጥያቄዎችም ምላሽ ይሰጣል። የሥነ ልቦና አማካሪ ቴራፒስትም ጭምር ሊሆንልዎ ይችላል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የስልክ ስክሪን ወይም የኮፒውተር ኪቦርድ ላይ አንድ ቁልፍን በመጫን ብቻ ሁሉንም ማከናወን የሚችል ይመስላል።
ተፎካካሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ለመድረስ ፉክክር ላይ ባሉበት በዚህ ጊዜ፤ ቴክኖሎጂው በከፍተኛ ፍጥነት እየለወጠ ነው።
ቻትጂፒቲ (ChatGPT) በቴክኖሎጂ መተግበሪያዎች ታሪክ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ካሉት መገልገያዎች አንዱ ነው።
መተግበሪያው በተለቀቀ ከአምስት ቀናት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን እና በሁለት ወር ውስጥ ደግሞ 100 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ማፍራት እንደቻለ በ30 ሀገራት መንግሥታት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና 'ኦርጋናይዜሽን ፎረ ኢኮኖሚም ኮኦፕሬሽን ኤንድ ዲቨሎፕመንት (OECD) አባላት የተሰበሰበው ዓለም አቀፍ የኤአይ ደኅንነት ሪፖርት ያመለክታል።
በ2023 ረዳት የኤአይ መተግባሪያ የሆነውን ኮ-ፓይለትን ያስጀመረው ማይክሮሶፍት፤ በ2025 ሁለተኛ ሩብ ዓመት ከኤአይ ንግድ የሚያገኘው ገቢ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል ብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል። ያሉትን የመረጃ ማዕከላትንም በመላው ዓለም 60 ቀጣናዎች እንዳስፋፋ አስታውቋል።
ሰዎች ጎግል ላይ መረጃዎችን በሚፈልጉበት ጊዜ፤ በኤአይ የተዘጋጀ ጥቅል መረጃ የሚያቀርበው 'አልፋ ኦቨርቪው'፤ ከ200 ሀገራት እና ግዛቶች የተወጣጡ 1.5 ቢሊዮን ተጠቃሚዎች በየወሩ እንደሚገለገሉበት የጎግል የአልፋቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰንዳ ፒቻይ ተናግረዋል።
ይህ ቴክኖሎጂ እዚሁ አብሮን መቆየቱ አይቀሬ መሆኑን ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ታድያ ተጠቃሚዎች እንዴት አድርገው ኤአይን በከፍተኛ ደረጃ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ጠይቀናቸዋል።
ካናዳዊቷ የኮምፒውተር ተመራማሪ ሳሻ ሉቺኦኒ፤ 'ሀጊንግ ፌስ' የተባለው በኦፕን ሶርስ ኤአይ ሞዴል የሚሠራ እና "ማሽን ለርኒንግን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ" የሚሠራ ተቋም አመራር ናት።
"ኤአይን የምመለከተው የሰውን ልጅ መልካምነትም ሆነ ክፋት የሚያጎለብት ነገር ነው ብዬ አስባለሁ" ስትል ለቢቢሲ 100 ሴቶች ተናግራለች።
ኤአይን ከመጠቀምዎ በፊት እነዚህን አራት ጥያቄዎች ራስዎን ሊጠይቁ እንደሚገባ ተመራማሪዋ ትመክራለች።
1. የምፈልገውን ለማግኘት ትክክለኛው የኤአይ መገልገያ ይህ ነው?
የኤአይ ሥርዓቶች በጣም የተለያዩ ነገሮችን የመሥራት አቅም እንዳላቸው ሉቺኦኒ ታስረዳለች።
"አንዳንድ ጊዜ ስለምናውቃቸው እና ብዙ ነገሮችን ማከናወን ስለሚችሉ ፊታችንን ይበልጥ ታዋቂ ወደ ሆኑት የኤአይ መገልገያዎች እናዞራለን። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ሳይንሳዊ ጥያቄዎችን እንደመመለስ ያለ አንድ የተለየ ተግባርን ለማከናወን ታስበው የተሠሩ [የኤአይ መገልገያዎች] አሉ፤ በእውነቱ እነዚህ የተሻለ ሥራ ያከናውናሉ።"
የተለያዩ መስፈርቶችን ለማሳካት ተብለው የተሠሩ ትልቅም ሆኑ ትንሽ በርካታ መተግበሪያዎች በየጊዜው ሥራ ላይ እየዋሉ ነው።
አንዳንዱ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች የሂሳብ ጥያቄ የተጻፈበትን ወረቀት ፎቶ አንስተው ሲያቀርቡለት ምላሽ ይሰጣል።
ሌላ አንድ የተለየ ነገር መልስ ለመስጠት የተዘጋጀ መተግበሪያ ከሆነ ያዘጋጁትን ምግብ ተመልክቶ ምን ቢያደርጉ በተሻለ መንገድ ምግቡን ማዘጋጀት እንደሚችሉ ሊያስረዳዎት ይችላል።
ሌላው ደግሞ የተለያዩ ቅዱሳን መጻህፍትን በማጣቀስ ለእርሶ የሚሆን የግል ጸሎት ያቀርብሎታል።
የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ፤ የ2025 'የአይ አይ ኢንዴክስ ሪፖርት' እንደሚያመለክተው አሜሪካ ውስጥ ያሉ ተቋማት ባለፈው ዓመት 40 ተጠቃሽ የአይአይ ሞዴሎችን አዘጋጅተዋል። በዚህ ተመሳሳይ ጊዜው ውስጥ የቻይና ተቋማት 15፤ የአውሮፓ ተቋማት ደግሞ ሦስት የአይአይ ሞዴሎችን ሠርተዋል።
ስለዚህ ለእርሶ የሚሆነውን ትክክለኛ የኤአይ መገልገያ ለማግኘት የትኛው ምርት ገበያው ላይ እንዳለ ይወቁ፤ ከአማራጮቹ መካከልም ለፍላጎትዎ የቀረበውን ይምረጡ።
2. ከኤአይ የሚገኙ መልሶች ምን ያህል ይታመናሉ?
ሊቺኦኒ እንደምትናገረው ኤአይ ምላሽ ሊሰጥዎ ይችላል፤ ነገር ግን መልሱ ሁሌም ትክክል ወይም እውነት ነው ማለት አይደለም።
"የኤአይ ሞዴሎች አንዳንድ ነገሮች ምክንያታዊ ስለሚመስሉ ብቻ የሌሉ ነገሮችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ ነገር ከኤአይ የተገኘን ነገር በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ውስጥ ጥቅም ላይ ሲውል ብዙ ችግር ሊያስከትል ይችላል" ትላለች።
ይህንን ለማስቀረት፤ ከኤአይ ሥርዓቱ የተገኘውን ውጤት ሁሌም ማረጋገጥ እንደሚገባ ትመክራለች።
"እንደገና በዝርዝር ያንብቡት እና የተገኘው ምላሽ ምን እንደሚል እንዲሁም ስሜት ይሰጥ እንደሆነ በጥንቃቄ ያስቡ። የኤአይ ሥርዓቱ በሰጠው ምላሽ በራስ መተማመን ኖሮት እንኳ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል።"
3. ምን ዓይነት መረጃ ለኤአይ እያጋራሁ ነው?
ተጠቃሚዎች ከኤአይ ስለሚያገኙት መረጃ በጥልቀት የሚያስቡትን ያህል ወደ ኤአይ ሞዴሉ ስለሚያስገቡትም መረጃ መጨነቅ እንዳለባቸው ሊቺኦኒ ታሳስባለች።
የኤአይ ሥርዓቶች የሚሠሩት ግዙፍ መጠን ያለውን ዳታ በመሰብሰብ እና ሞዴሉን ለማሠልጠን ጥቅም ላይ በማዋል ነው። ይህ ማለት እርስዎ ያስገቡት መረጃ፣ ፎቶ ወይም ጽሑፍ በሥርዓቱ ውስጥ ሊከማች፣ ሊተነተን እንዲሁም ሞዴሉ ወደፊት የሚሰጣቸውን ምላሾች ቅርጽ ለማስያዝ ሊያገለግል ይችላል ማለት ነው።
እያንዳንዱ መገልገያ የራሱ የሆነ የፕራይቬሲ ፖሊሲ (የግል መረጃ ጠበቃ) ስላለው ከመጠቀምዎ በፊት እነዚህን ዝርዝር ጉዳዮች መመልከት ይኖርብዎታል።
"የግል ወይም ምሥጢራዊነት ያለው ወይም ትንሽም ቢሆን አሳፋሪ መረጃ ከሆነ ወደ ኤአይ ሞዴል ውስጥ አያስገቡት፤ ምክንያቱም መረጃው ኢንተርኔት ላይ ሊወጣ ይችላል" ስትል ሉቺኦኒ ታክላለች።
ከዚህ ቀደም የሜታ ኤአይ መተግበሪያን ሲጠቀሙ የነበሩ የተወሰኑ ሰዎች ወደ ሞዴሉ ያስገቡት ጽሁፍ 'ዲስከቨር' በሚለው የመገልገያው ገጽ ላይ ለሁሉም ሰው እንዲታይ ሆኖ ሲለጠፍ እንደነበር አስታውሳለች።
ቢቢሲ ባደረገው ክትትል፤ ተጠቃሚዎች የትምህርት ቤት ወይም የዩኒቨርሲቲ ፈተና ጥያቄዎችን ፎቶ በማንሳት ወደ ኤአይ ያስገቡባቸው፣ ወሲባዊ ምሥሎችን እንዲሰጣቸው የጠየቁበት እንዲሁም የፆታዊ ማንነታቸውን በተመለከተ ከኤአይ ምክር የጠየቁባቸውን ምሳሌዎችን አግኝቷል።
በአውሮፓውያኑ 2023 ጣሊያን፤ የቻትጂፒቲን (ChatGPT) የተራቀቀ ቻትቦት በማገድ የመጀመሪያዋ ምዕራባዊ ሀገር ሆለች። ሀገሪቱ ይህንን እገዳ የጣለችው በግላዊ መረጃ ጥበቃ (privace) ላይ ባለ ስጋት እንዲሁም ከዳታ ጥበቃ ሕግ ተገዢነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ነው።
ደቡብ ኮሪያ፣ አውስትራሊያ እና አሜሪካም የቻይና ቻትቦት የሆነው 'ዲፕሲክ' የተጠቃሚዎችን መረጃን የሚያከማችበትን እና የሚጠቀምበትን መንገድ በተመለከተ ስጋታቸውን አንስተዋል።
4. በእርግጥ ኤአይን መጠቀም ያስፈልገኛል?
ሉቺኦኒ፤ ኤአይ መገልገያ እንጂ የአእምሮዎ ምትክ አይደለም ትላለች።
አንድን ነገር ወደ ኤአይ ከመውሰድዎ በፊት ራስዎ ሊያከናውኑት የሚችሉት ተግባር እንደሆነ ወይም እንደ ካልኩሌተር ያሉ ሌሎች ተገቢ መገልገያዎች በመጠቀም መፍትሄ የሚገኝለት ነገር እንደሆነ ማሰብ ይጠበቅቦታል።
ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ እና ግላዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች ሲኖሩ በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን እርዳታ መጠየቅ የተሻለ እንደሆነም ትመክራለች።
"ኤአይ፤ ምን ነገር ትክክል ነው፣ የትኛው ስህተት ነው፣ በአንድ ሁኔታ ውስጥ ምን ጉዳይ ሥነ ምግባርን የጠበቀ ነው የሚሉትን የሰው ልጅ ዕሴቶች መሠረት በማድረግ ውሳኔ መስጠት አይችልም። እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮችን እንዲወስንልን መፍቀድ የለብንም" ትላለች።
በተጨማሪም ኤአይ ምላሽ ለመስጠት የሚጠቀመው ኃይል እና ሀብት የተለመዱት የመፈለጊያ ኢንጅኖች ጥቅም ላይ ከሚያውሉት የሚበልጥ ነው።
ለኤአይ የሚጠቀሙባቸውን የኮምፒተር ሰርቨሮች የሚቀመጡባቸው የመረጃ ማዕከላትን ለማቀዝቀዝ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ያስፈልጋል። ይህም በዓለም ዙሪያ የሚፈጠሩ የውሃ አቅርቦት ችግሮችን ሊያባብስ ይችላል።
ሉቺኦኒ፤ "በእርግጠኝነት የኤአይ መገልገያዎች ለተወሰኑ ጊዜ አብረውን ይሆናሉ፤ በተለይም ኢንተርኔት እና ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የበለጠ ስለምንገኝ እና የበለጠ ንቁ ስለሆንን ነው" ስትል ታስረዳለች።
"ነገር ግን ይህ በሕይወታችን ውስጥ ላለ ነገር ሁሉ ኤአይን መጠቀም አለብን ማለት አይደለም፤ ይህ ሲጀመርም የሰው ልጅ ያስባሉንን እንደ የፈጠራ ክህሎት፣ የሰው ለሰው ግንኙነቶች እና ማኅበረሰባዊነት የመሳሰሉ ነገሮችን እንድናጣ ያደርገናል" በማለት አሳስባለች።