እስራኤል በሊባኖስ ግዛት ውስጥ ‘ውስን’ የእግረኛ ጦር ዘመቻ መጀመሯን አስታወቀች

የእስራኤል ታንኮች በሊባኖስ ድንበር ላይ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ታንኮች በሊባኖስ ድንበር ላይ

በሄዝቦላህ ላይ ያነጣጠረ ‘ውስን፣ የተገደበ እና ግልጽ ዒላማ ያለው’ የእግረኛ ዘመቻ በደቡባዊ ሊባኖስ መጀመሩን የእስራኤል ጦር ገለጸ።

በድንበር አቅራቢያ የሚገኙት ዒላማዎች “ለእስራኤል ዜጎች ትልቅ ስጋት ናቸው” ሲል የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በኤክስ ገጹ ላይ በለጠፈው መግለጫ ገልጿል።

"የእስራኤል አየር ኃይል እና የእስራኤል መከላከያ የመድፍ ምድብ በአካባቢው በሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ድብደባ በመፈጸም የምድር ጦሩን እየደገፉ ነው" ሲል መግለጫው አክሏል።

እስራኤል የእግረኛ ጦር ዘመቻውን ከመጀመሯ በፊት ስለጉዳዩ ለወዳጇ አሜሪካን ማሳወቋ ተሰምቷል።

በዚህም ሊባኖስ ውስጥ ውስን የምድር ጦር ዘመቻ ለመጀመር እንዳሰበች ለዋይት ሐውስ አሳውቃለች ሲሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።

እስራኤል ሄዝቦላህን ለማጥቃት “የአየር፣ የባሕር እና ምድር ኃይሎችን” ለመጠቀም መዘጋጀቷን የአገሪቱ መከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላንት በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ ለሚገኙ ወታደሮች ቀደም ሲል መናገራቸው ይታወሳል።

የሄዝቦላህ ምክትል መሪ በበኩላቸው በሊባኖስ ውስጥ ለሚደረገው ማንኛውም የእስራኤል ጥቃት ቡድኑ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ግጭቱን እንዳይባባስ በዓለም አቀፍ ደራጃ ጥሪዎች ቀርበዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ እስራኤል ምንም ዓይነት የምድር ዘመቻ እንዳትከፍት ጠይቀዋል።

የሊባኖስ የፀጥታ ምንጭን ጠቅሶ የሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የአገሪቱ ጦር በደቡብ አቅጣጫ ድንበር ላይ የሰፈሩ ወታደሮችን ቢያንስ 5 ኪሜ ወደ ኋላ ስቧል።

ጋላንት በድንበር ላይ ለሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች እንደተናገሩት፤ ተፈናቃዮችን ወደ ሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል እንዲመለሱ ለማድረግ የአገሪቱ ሠራዊት ሁሉንም “በእጁ ያለን መንገድ” ይጠቀማል ሲሉ ተናግረዋል ።

የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህን አርብ ዕለት ቤይሩት ውስጥ “ማስወገዳችን በጣም አስፈላጊ እርምጃ ቢሆንም፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር አብቅቷል ማለት አይደለም” ሲሉ በአንድ አጭር ቪዲዮ ላይ ጋላንት ሲናገሩ ተደምጠዋል።

አክለውም “መሠራት ያለበት በሙሉ ይከናወናል” በተጨማሪም “ከአየር፣ ከባሕር እና ከምድር ጦራችንን በሙሉ እንጠቀማለን” ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውንና እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የሊባኖስ ባለስሥልጣናት ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውንና እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የሊባኖስ ባለስሥልጣናት ተናግረዋል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሰኞ ምሽት ላይ በሊባኖስ ርዕሰ መዲና ቤይሩት በርካታ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።

ሰኞ አመሻሽ ላይ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት (አይዲኤፍ) ነዋሪዎች በደቡባዊ ቤይሩት ከሚገኙ ሦስት አካባቢዎች “በፍጥነት” ለቀው እንዲወጡ ካዘዘ በኋላ ነው ጥቃቶቹ የተፈጸሙት።

የእስራኤል ጦር የአረብኛ ቃል አቀባይ አቪሻይ አድራይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “ከአሸባሪው ሄዝቦላህ ንብረቶች እና መገልገያዎች አጠገብ ይገኛሉ? እንግዲያውስ የመከላከያ ሠራዊታችን በዒላማዎቹ ላይ እርምጃ ይወስዳል” ብለዋል።

የኒው ዮርክ ታይምስ ቀደም ብሎ እንደዘገበው ከሆነ የእስራኤል የኮማንዶ አባላት ለሰፊ የምድር ዘመቻ ለመዘጋጀት በሚል ወደ ሊባኖስ ግዛት ለአጭር ገብተው ነበር።

ከድንበሩ ከ10 ኪሜ ርቃ በምትገኘው እና የክርስትና እምነት ተከታዮች በብዛት የሚኖርባት የጅዲዴት ማርጃዩን ከተማ ከንቲባ ሰኞ ዕለት ለሮይተርስ እንደተናገሩት ከሆነ ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች በተቻለ ፍጥነት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ከእስራኤል ጦር በስልክ ተነግሯቸዋል።

የሄዝቦላህ ምክትል ኃላፊ ሼክ ናይም ቃሲም በበኩላቸው ለእስራኤል የምድር ጥቃት ዝግጁ ነን ብለዋል። ቡድኑ እስካሁን በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት “አነስተኛ” ሲሉ ገልጸው፤ ጦርነቱ ረዥም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችልም ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ጠይቀዋል። የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል “ተጨማሪ ወታደራዊ ጣልቃገብነት ሁኔታውን በእጅጉ ስለሚያባብሰው ከወዲሁ መወገድ አለበት” ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ ምንም ዓይነት የምድር ዘመቻ ስታደርግ ማየት አይፈልጉም ሲሉ ቃል አቀባያቸው ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “አሁን የተኩስ አቁም ሊኖር ይገባል” ሲሉ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

ባይደን ስለእስራኤል ድንበር ተሻጋሪ ዘመቻ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ከምታውቁት በላይ አውቃለሁ። እነሱ ቢያቆሙት ይመቸኛል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ምላሽ ሰጥተዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት“የተሻለው አማራጭ ፈጣን የተኩስ ማቆም ማድረግ ነው” ብለዋል።

እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት በሊባኖስ የሐማስ መሪ የሆኑት ፋተህ ሸሪፍ አቡ ኤል-አሚን መገደላቸውን እስራኤል እና ሐማስ አረጋግጠዋል።

ሸሪፍ “በሊባኖስ ውስጥ የሐማስን የሽብር ተግባር ከሄዝቦላህ አባላት ጋር የማስተባበር ኃላፊነት ነበረበት” ሲል የእስራኤል ጦር ገልጿል።

ሰኞ ማለዳ በማዕከላዊ ቤይሩት ኮላ በሚባል ሰፈር በተፈጸመ የእስራኤል ጥቃት ሦስት የፍልስጤም ነፃ አውጪ የሕዝባዊ ግንባር (ፒኤፍኤልፒ) አባላት መግደላቸውን የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የተገደሉት የወታደራዊ ደህንነት ኃላፊው መሐመድ አብደል-አል፣ ወታደራዊ አዛዡ ኢማድ ኦዴህ እና ወታደሩ አብደል ራህማን አብደል-አል ናቸው ብሏል።

በኮላ ከደረሰው ጥቃት በኋላ “ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ስለመኖሩ በትክክል አናውቅም” ሲሉ በሊባኖስ የድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ጂናኔ ሳድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ዛሬ ደኅንነቱ የተጠበቀ የሚባለው ቦታ ከአንድ ሰዓት በኋላ ወይም ነገ ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል” ብለዋል።

እሑድ ዕለት ደግሞ የእስራኤል አውሮፕላኖች በየመን ሁቲዎች ቁጥጥር ስር በምትገኘው ሆዴዳህ ወደብ ላይ ጥቃት በመፈጸም ከፍተኛ ፍንዳታ አድርሰዋል።

ሐማስ ወደ እስራኤል ደንበር ገብቶ ያልተጠበቀ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ አልፎ አልፎ የነበረው የእስራኤል እና የሄዝቦላህ ድንበር ተሻጋሪ ጦርነት ተባብሷል። ሄዝቦላህ ካለፈው ዓመት መስከረም 27 ጀምሮ ለሐማስ አጋርነቱን ለማሳየት በሚል ጥቃት እየፈጸመ እገኛል።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ግን ሁኔታው በእጅጉ ተባብሷል።

ፔጀር እና ዎኪ ቶኪ በሚባሉ የግንኙነት መሳሪያዎች ላይ ያጋጠሙ ፍንዳታዎች፣ ተከታታይ የሆነው የሄዝቦላ የጦር አዛዦች ግድያ፣ ሠላማዊ ሰዎችን የገደሉ አሰቃቂ የአየር ድብደባ ዎች እንዲሁም ቤይሩት ውስጥ የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህን የገደለው አርብ ዕለቱ ጥቃቶች ቡድኑ ላይ በርካታ ጉዳት አድርሶበታል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።