አዲሱ የትዊተር ተቀናቃኝ በሰዓታት 10 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ማጋበሱን ዛከርበርግ ገለጠ

ሜታ የሠራው አዲሱ ትዊተር መሰል ማኅበራዊ ሚድያ ይፋ ከሆነ በሰዓታት 10 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ማጋበሱን ማርክ ዛከበርግ ገለጠ።

ዛከርበርግ “ወዳጅ” የትዊተር ተቀናቃኝ ያለው መድረክ ትሬድስ የተባለ ስም ተሰጥቶታል።

ኢላን መስክ በቅርቡ ትዊተርን ገዝቶ የግል ንብረቱ ማድረጉ ይታወሳል።

የዘርፉ ሰዎች እንደሚሉት ትዊተር ያመጣቸው ለውጦች ያልተዋጠላቸው ሰዎች ወደ ትሬድስ ሊጎርፉ ይችላሉ።

ከትዊተር ጋር በሚቀራረብ መልክ ትሬድስ ተጠቃሚዎች እስከ 500 ‘ካራክተር’ እንዲፅፉ ይፈቅዳል።

ዛከርበርግ አዲሱን መተግበሪያ በለተመከተ በሰጠው መግለጫ “ወዳጃዊ. . .መሆኑ ለስኬቱ ቁልፍ ነው” ብሏል።

ኢላን መስክ በአዲሱ መተግበሪያ ደስተኛ የሆነ አይመስልም።

“የኢንስታግራም ሃሰት ደስታ ከሚከበኝ፤ ትዊተር ላይ የማላውቀው ሰው ቢዘልፈኝ ይሻላል” ሲል ትሬስድን ሸንቆጥ አድርጓል።

ዛከርበርግ፤ ምንም እንኳ ጊዜ ሊወስድ ቢችልም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉበት መድረክ ሊኖር ይገባል ይላል።

“ትዊተር ይህን የማድረግ ዕድል ነበረው። ነገር ግን ይህ የሚሆን አይመስልም። እኛ ይህን እናደርጋለን የሚል ተስፋ አለኝ።”

አዲሱ መተግበሪያ ከተጠቃሚዎች የሚወስደው መረጃ ብዙ ትችት እያስተናገደ ነው።

ተጠቃሚዎች ይህን መተግበሪያ ሲያወርዱ የጤና፣ ፋይናንስ እና ከዚህ በፊት የጎገሏቸው መረጃዎችን አሳልፈው ሊሰጡ ይችላሉ።

ትሬድስ የተሰኘው መተግበሪያ ከ100 በላይ አገራት ላሉ ተጠቃሚዎች ይፋ ቢሆንም ከሕግ ጋር በተያያዘ በአውሮፓ ኅብረት አገራት ዕውቅና አልተሰጠውም።

‘የመጀመሪያው ዕትም’

የፌስቡክና ኢንስታግራም እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ አዲሱ መተግበሪያ ገና ጅማሬ ላይ ነው ይላል።

ትሬድስ ወደፊት የተለያዩ ይዘቶችን ይዞ ለመምጣት ቃል ገብቷል።

ምንም እንኳ ትሬድስ ራሱን የቻለ መተግበሪያ ቢሆንም ተጠቃሚዎች የኢንስታግራም አካውንታቸውን ተጠቅመው መግባት ይችላሉ።

የኢንስታግራም መግቢያ ስምና የይለፍ ቃል ትሬድስን ለመጠቀም ቢውሉም ወደ ውስጥ ሲገቡ ‘ፕሮፋይሎን’ እንደ ፍላጎትዎ መጠምለል ይችላል።

አልፎም ኢንስታግራም ላይ የሚከተሏቸውን ሰዎች ትሬድስም ላይ ለመከተል አማራጭ ይቀርብልዎታል።

በኢንስታግራም ‘ድብቅ’ አካውንት [ፕራይቬት] ያላቸው ሰዎች ወደ ትሬድስ ሲመጡ አካውንታቸውን ለሁሉም ይፋ ማድረግ ይፈቀድላቸዋል።

መረጃ አሳልፎ በመስጠት የሚወቀሰው ሜታ ባለፉት ዓመታት የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ አሳልፏል ተብሎ በርካታ ክስ ቀርቦበት ነበር።

ትሬድስ የተሰኘው መተግበሪያ ይፋ ይሆናል በተባለ ወቅት ኢላን መስክ “ፈጣሪ ይመስገን [እኒህን መተግበሪያዎች] የሚመራው ጤናማ ሰው ነው” ሲል ዛከርበርግን በነገር ወጋ አድርጓል።

የትዊተር ቅርፅ ያላቸው በርካታ መተግበሪያዎች ገበያ ላይ ቢኖሩም ውድድሩን ረትተው መውጣት አልቻሉም።

ከሌሎች ሲነፃፀር ትሬድስ የተሻለ ሥፍራ የሚሰጠው መቶ ሚሊዮኖች ካሉት ኢንስታግራም ጋር መቆራኘቱ ነው።

ተጠቃሚዎች ፅሑፍ፣ ፎቶ እና ከአምስት ደቂቃ ያልበለጠ ተንቀሳቃሽ ምስል መለጠፍ ይችላሉ።