ታዋቂዋ የኢንስታግራም ሞዴል በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሴቶችን በባርነት ስትበዘብዝ እንደነበር ተደረሰባት

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያፈራችው ካት ቶሬዝ
የምስሉ መግለጫ, ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያፈራችው ካት ቶሬዝ

በአውሮፓውያኑ መስከረም 2022 ሁለት ብራዚላዊያን አሜሪካ ውስጥ ሲጠፉ ኤፍቢአይ እና ቤተሰቦቻቸው ፍለጋ ተያያዙ።

ኤፍቢአይም ሆነ ቤተሰብ ያላቸው መረጃ ሁለቱ ሴቶች የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት በመስጠት ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ብዙ ተከታይ ያፈራችው ካት ቶሬዝ ቤት ማረፋቸውን ነው።

ቶሬዝ ከሁለቱ ሴቶች በአንዷ ምክንያት በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በባርነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብላ የስምንት ዓመት እሥር ተፈርዶባታል።

ቢቢሲ እንደተረዳው በማኅበራዊ ሚድያ የምትታወቀው ቶሬዝ በሁለተኛዋ ሴት ምክንያት ሌላ ክስ ተከፍቶባታል።

ለመሆኑ እንደ ሌዎናርዶ ዲካፕሪዮ ካሉ የሆሊውድ ፈርጦች ጋር ትጨፍር የነበረች፤ በለተያዩ ዓለም አቀፍ መፅሔቶች ላይ ፎቶዋ የወጣ የቀድሞ ሞዴል፤ እንዴት የኢንስታግራም ተከታዮቿን ልትበዘብዝ ቻለች?

“እኔ ሳያት የሆነ ዓይነት ተስፋ ይሰማኝ ነበር” ትላለች በአውሮፓውያኑ 2017 የቶሬዝን ኢንስታግራም ገፅ ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኘችው አና።

ምንም እንኳ አና በኤፍቢአይ የፍለጋ መነፅር ውስጥ ከገቡት ሁለቱ ሴቶች መካከል ባትሆንም የሞዴሏ በደል ከደረሰባቸው አንዷ ናት። ሁለቱ ሴቶች እንዲገኙም ምክንያት ሆናለች።

አና፤ ቶሬዝ ከብራዚል አቧራማ መንገዶች ተነስታ ሞዴሎች የሚረማመዱበት ቀይ ምንጣፍ ላይ ስትንፈላሰስ አይታለች። ከሆሊውድ ታዋቂ ሰዎች ጋር ‘ፓርቲ’ ስትወጣ ተመልክታለች። በቶሬዝ ስኬት ተማርካለች።

“በልጅነቷ ብዙ ነገር አምልጣ፣ ስቃይን አልፋ እዚህ የደረሰች ትመስላለች” ስትል አና ለቢቢሲ አይ የምርመራ ቡድን እና ለቢቢሲ ኒውስ ብራዚል ተናገራለች።

ከደቡባዊ ብራዚል የመጣችው አና በልጅነቷ ብዙ ስቃይ አሳልፋለች። ከዚያም በላይ በቀደመ የፍቅር ጓደኛዋ ብዙ በደል እና እንግልት ደርሶባታል።

ካት ቶሬዝ በቅርቡ አ ቮዝ አሊያም በእንግሊዝኛው ‘ዘ ቮይስ’ የተሰኘ የሕይወት ታሪኳን የሚዳስስ መፅሐፍ አሳትማለች። በዚህ መፅሐፏ ላይ በተሰጣት መንፈሳዊ ኃይል ምክንያት የወደፊቱን መተንበይ እንደምትችል ትናገራለች። ይህን ተከትሎ በርካታ የብራዚል ሚድያዎች ቃለ-መጠይቅ ሲያደርጉላት ነበር።

“አንድ መፅሔት ላይ ፎቶዋ ተለጥፎ ነበር። በጣም ታዋቂ ከሆኑ እንደ ሌዎናርዶ ዲካፕሪዮ ካሉ ሰዎች ጋርም ታይታለች። ሁሉም የማየው ነገር አሳማኝ መስሎ ታየኝ” ትላለች አና።

አና በተለይ ቶሬዝ ከመንፈሳዊ ዓለም ጋር ያላት ቁርኝነት ነው የበለጠ እንድትሳብ ያደረጋት።

አና የማታውቀው አንድ ነገር ቢኖር ቶሬዝ በማኅበራዊ ሚድያ የምታንፀባርቀው ሕይወት ግማሹ እንጂ ሙሉ በሙሉ እውነት አለመሆኑን ነው።

ቶሬዝ ኒው ዮርክ ውስጥ ቤት ተከራይታ ስትኖር ደባሏ የነበረው ሉዜር ትዌርስኪ እንደሚለው የሆሊውድ ጓደኞቿ አያሁስካ የተባለ አደንዛዥ ዕፅ ካቀመሷት በኋላ ነው የድሮ ባሕርይዋ የተቀየረው።

ከደቡባዊ ብራዚል የመጣችው አና

የፎቶው ባለመብት, Jack Garland/BBC

የምስሉ መግለጫ, ከደቡባዊ ብራዚል የመጣችው አና በልጅነቷ ብዙ ስቃይ አሳልፋለች

“መድኃኒቱን ከወሰደች በኋላ ነው ጠባይዋ መቀያየር የጀመረው” ይላል።

እሱ እንደሚያምነው ለሚኖሩበት አፓርትማ ትከፍል የነበረው የናጠጠ ሀብታም እና በገንዘብ ምክንያት ጡንቻ ካዳበሩ ሰዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት በመመሥረት እና በመተኛት ነው።

የቶሬዝ የሰውነት ማጎልመሽ ድረ-ገፅ በክፍያ የሚሠራ ሲሆን “ሁሌም የሚመኙት ፍቅር፣ ገንዘብ እና በራስ መተማመን እኛ ጋ አለ” ሲል ቃል ይገባል።

ድረ-ገፁ ከያዛቸው ቪድዮዎች መካከል ስለፍቅር ግንኘኑት፣ ሰውነት ማጎልመስ፣ የተሳካ ቢዝነስ መመሥረት እና መንፈሳዊነት የሚሉ ሐሳቦች ይገኙበታል። ‘ሂፕኖሲስ’ የተሰኘው መንገድ፣ አርምሞ [ሜዲቴሽን] እንዲሁም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተካተውበታል።

150 ዶላር ጨምረው የሚከፍሉ ደንበኞች ደግሞ ከቶሬዝ ጋር በቪድዮ ተገናኝተው ምክር የሚቀበሉ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት ችግር ካለባቸው እንደምትፈታላቸው ቃል ትገባለች።

በብራዚል ዋና ከተማ የምትኖረው አማንዳ የቶሬዝ የቀድሞ ደንበኛ ስትሆን፣ በእሷ ምክር ምክንያት በራስ መተማመኗ እንደጨመረ ትናገራለች።

“የነበሩንኝ ጥርጣሬዎች፣ ጥያቄዎች እና ውሳኔዎች ብቻ ሁሉንም ነገሮች ቀድሜ የምናገረው ለእሷ ነው። ውሳኔ የምንወስነው በጋራ ነው” ትላለች።

ነገር ግን የቶሬዝ ምክር ጥላ ያጠላበት ነበር። አና፣ አማንዳ እና ሌሎች የሞዴሏ ተከታዮች ከእሷ ምክር መቀበል ከጀመሩ በኋላ ከቤተሰቦቻቸው እና ከጓደኞቻቸው እየተነጠሉ እንዲሁም እሷ አድርጉ የምትላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።

ካት ቶሬዝ

የፎቶው ባለመብት, Kat Torres

የምስሉ መግለጫ, ካት ቶሬዝ

በአውሮፓውያኑ 2019 ቶሬዝ፤ አና ወደ ኒው ዮርክ መጥታ የግል ተላላኪዋ ሆና እንድታገለግላት ስትጠይቃት አላመነታችም።

ቦስተን ዩኒቨርሲቲ ኒውትሪሽን ታጠና የነበረችው አና ትምህርቷን በበይነ-መረብ አማካይነት ለመከታተል ወስና የቶሬዝ እንስሳት ጠባቂ ሆነች። ምግብ ማብሰል፣ ልብስ ማጠብ እንዲሁም ፅዳት መሥራት ተያያዘች። ለዚህ አገልግሎቷ በወር 2 ሺህ ዶላር ይከፈላታል።

ቢቢሲ አይ እና ቢቢሲ ብራዚል በጋር በሠሩት የምርመራ ዘገባ የሰውነት ማጎልመሻ እና መንፈሳዊ ሕይወት አሰልጣኟ ካት ቶሬዝን ወደ ዝና መመንጠቅ እና የዓለም አቀፍ ደንበኞቿ መበራከትን ይዳስሳል።

አና ወደ ቶሬዝ አፓርትማ ስትመጣ ኢንስታግራም ላይ የምታየው እውነታ እና መሬት ላይ ያለው እውነታ የተለያየ መሆኑን ተረዳች።

“በጣም አስደንጋጭ ነበር። ምክንያቱም ቤቷ ዝርክርክ ያለ ነው። በጣም ቆሻሻ እና ሽታው በጣም የሚቀረና ነው” ትላለች።

አና እንደምትለው ቶሬዝ ገላዋን መታጠብን የመሳሰሉ ዕለታዊ ተግባራትን እንኳ ብቻዋን መፈፀም አትችልም። ምክንያቱም ብቻዋን መሆን በጣም ትፈራለች። በዚህ ምክንያት ሁሌም ቶሬዝን የመንከባከብ ኃላፊነት አለባት። በቂ እንቅልፍ አታገኝም። ለጥቂት ሰዓታት የምትተኛው ደመቶች ባቆሸሹት ሶፋ ላይ ነው።

“እንደ ባሪያ ትጠቀመኝ እንደነበር የገባኝ አሁን ነው። በዚህ ትረካ ነበር” ትላለች አና። አና ለሰጠችው አገልግሎት ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳልተከፈላት ትናገራለች።

ቶሬስ (ከግራ)፣ ዲዜሪ እና ሌቲሺያ (ከቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, Kat Torres

የምስሉ መግለጫ, ቶሬስ (ከግራ)፣ ዲዜሪ እና ሌቲሺያ (ከቀኝ)

በቦስተን ዩኒቨርሲቲ የተሰጣትን ‘ዶርም’ ጥላ የወጣችው አና በወቅቱ የምትሄድበት ጠፍቷት እንደነበር ታስውሳለች። አና እንደምታወሳው ቶሬዝደን መጋፈጥ ስትጀምር ፀባይዋ እየተቀያየረ፤ ቁጡ እየሆነች መጣችባት።

ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላ አና አዲስ የፍቅር ግንኙነት መሥርታ ከቶሬዝ ቤት አምልጣ ጠፋች። ይሄኔ ነው መስከረም 2022 ሁለት ብራዚላውያን አድራሻቸውን መጥፋቱን የሰማችው።

በዚህ ወቅት ቶሬዝ ዛክ የሚባል የ21 ዓመት ወጣት የፍቅር ጓደኛ ይዛ፤ ቴክሳስ ግዛት ኦስቲን ከተማ አምስት መኝታ ያለው ሰፊ ቤት ተከራይታ መኖር ጀምራለች።

በአና የለመደችው ቶሬዝ ታማኝ የሚባሉ ተከታዮቿን አስመጥታ ለእሷ እንዲሠሩ አደረገች። ለዚህ ተግባራቸው ምላሽ ሕልማቸውን እንደምታሳካ ቃል ትገባላቸዋለች።

ሌቲሺያ ማያ እና ዴዚሬ ፍሬይታስ የተባሉ ጀርመን ይኖሩ የነበሩ ብራዚላውያን ናቸው አድራሻቸው ጠፍቶ በኤፍቢአይ እየተፈለጉ የነበሩት። ሶል የተባለች ሌላ ሴትም በቶሬዝ ተመልምላ ነበር።

ቢቢሲ ባገኘው መሠረት ቶሬዝ ቢያንስ አራት ሴቶችን አሳምና ወደ ቤቷ መጥተው እንዲያገለግሏት አድርጋለች። አንዳንዶቹ ሴቶች ካሜራ ላይ ለመቅረብ ፈቃደኛ አልሆኑም።

አና እና ሶል እንዲሁም ሌሎች የቶሬዝ ሰለባ የሆኑ ሴቶች በጋራ ሆነው የደረሰባቸውን ለፖሊስ ካሳወቁ በኋላ ነው ጉዳዩን ኤፍቢአይ ይዞት ቶሬዝን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ የከፈተው።

ቢቢሲ እንዳረጋገጠው ቶሬዝ ብራዚል ውስጥ የሚገኝ ፍርድ ቤት ሴቶቹን ለባርነት በማጋለጥ እና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጥፋተኛ ናት በሚል የ8 ዓመት እሥር የፈረደባት።