ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ይዛ ወደ የመን ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ሰጥማ 38 ሰዎች ሞቱ

በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ይዛ ከጂቡቲ ወደ የመን በማቅናት ላይ የነበረች ጀልባ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ውስጥ ሰጥማ የ38 ሕይወት አለፈ።

አደጋው የደረሰው ትናንት ሰኞ መጋቢት 30/2016 ዓ.ም. ኢትዮጵያውያኑን አሳፍራ ከጅቡቲ ወደ የመን ስትጓዝ ነው ጀልባዋ የመስመጥ አደጋ ያጋጠማት።

በጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሰሜን ምሥራቅ ከሚገኘው የአገሪቱ ክፍል ተነስታ ጉዞዋን ወደ የመን አቅጣጫ አድርጋ የነበረችው ጅልባ 60 ኢትዮጵያውያንን አሳፍራ ነበር ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችን ዜግነትን በተመለከተ ያለው ነገር ባይኖርም፤ ከሟቾቹ መካከል ሕጻናት እንደሚገኙበት ገልጾ 22 ሰዎች በሕይወት ተገኝተዋል ብሏል።

የተባባሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በጀልባዋን ላይ ተሳፍረው የነበሩ ሰዎችን ቁጥር 64 የሚያደርሰው ሲሆን፣ ሕይወታቸው ሳያልፍ አይቀርም የተባሉ ተጨማሪ 6 ሰዎች የገቡበት አልታወቀም ብሏል።

በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አደጋው ወደ ደረሰበት ስፍራ በመጓዝ የአደጋውን መንስኤ በማጣራት ላይ እንደሚገኝም ጨምሮ ገልጿል።

ኤምባሲው በየዓመቱ ከ200 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች ከጅቡቲ ተነስተው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ለመድረስ በየብስ እና በባሕር አደገኛ ጉዞ ያደርጋሉ ያለ ሲሆን፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በጀልባ መስመጥ አደጋ ብቻ የ189 ኢትዮጵያውያን ሕይወት ማለፉን ጨምሮ ገልጿል።

የአይኦኤም ፕሮጀክት የሆነው እና የስደተኞችን መጥፋት የሚከታተለው ሚሲንግ ማይግራንትስ የአሁኑ አደጋ ከእአአ 2014 ጀምሮ ‘በምሥራቃዊ የጉዞ አቅጣጫ’ ሕይወታቸውን ያጡ ወይም የገቡበት የጠፉ ስደተኞችን ቁጥር 1ሺህ አድርሶታል ብሏል።

ምንም እንኳ ስደተኞች በዚህ የጉዞ አቅጣጫ አደገኛ ሁኔታ እየገጠማቸው ቢሆንም፣ የስደተኞች ቁጥር አሁንም እየጨመረ ነው።

በሕይወት የተገኙ ስደተኞች በአሁኑ ወቅት በጂቡቲ መንግሥት እና በአይኦኤም አስፈላጊው ክትትል እየተደገላቸው እንደሆነም ተገልጿል።

“በጅቡቲ በኩል ወደ የመን የሚደረግ ሕገ ወጥ ጉዞ ከሞት ውጪ ሌላ ትርፍ የለውም” ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ዜጎች በሕገ ወጥ ደላሎች “በመታለል ውድ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በዚህ አደገኛ የጉዞ መስመር” ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

ኤምባሲው ጨምሮም የፍትህ አካላት ከገጠራማ የአገሪቱ አካባቢዎች ዜጎቻችን በመመልመል ለስደት በሚዳርጓቸው ግለሰቦች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪውን አስተላልፏል።