ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጋና መብራት ኃይል ፓርላማው 1.8 ሚሊዮን ዶላር ውዝፍ ዕዳ ባለመክፈሉ የኃይል አቅርቦቱን አቋረጠ
የጋና መብራት ኃይል የአገሪቱ ፓርላማ 23 ሚሊዮን የጋና ሲዲ (1.8 ሚሊዮን ዶላር) ውዝፍ ዕዳ ባለመክፈሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱን አቋረጠ።
መብራት ሲቋረጥም የፕሬዚዳንቱ ብሄራዊ ንግግርን በተመለከተ ክርክር እየተደረገ በነበረበት ወቅት ነው።
የፓርላማ አባላቱ ብርሃን በሌለው ክፍል ውስጥ በአካን ቋንቋ “ዱምሶር፣ ዱምሶር” እያሉ ሲጮሁ የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተጋራ ሲሆን ይህም “መብራት ጠፋ” እንደማለት ነው።
የመጠባበቂያ ኃይል (ጄኔሬተር) ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በመነሳቱም መብራት በዚያች ክፍል ብቻ እንዲመለስ መደረጉን የኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ነገር ግን ሌሎች የፓርላማው የህንጻ ክፍሎች የኃይል አቅርቦቱ ከመመለሱ በፊት አብዛኛውን ቀን ያለ መብራት እንዲቆዩ ተገደዋል።
መብራት ድንገት በተቋረጠበት ወቅትም አሳንሰር (ሊፍት) ውስጥ የነበሩ የፓርላማ አባላት እና ሰራተኞች መውጫ አጥተው መቆዬታቸውን የጋና ቲቪ3 ቻናል ዘግቧል።
የጋና የመብራት ኃይል የኮሙኒዪኬሽን ዳይሬክተር ዊልያም ቦአቴንግ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት “ፓርላማው ክፍያውን እንዲፈጽም የተላከለትን ማስጠንቀቂያ ባለመክበር” እምቢተኝነቱን በማሳየቱ የኃይል አቅርቦት መቋረጡን ነው።
ፓርላማው ካለበት ዕዳ 13 ሚሊዮን የጋና ሲዲ በመክፈል እና ቀሪውንም ዕዳውንም በሳምንት ውስጥ ለመክፈል ቃል መግባቱንም ተከትሎም በዚያኑ ቀን መብራት እንደተቀጠለለት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
“መብራት መቋረጥ ለሁሉም ነው። ያለበትን ክፍያ የማይፈጽም ማንኛውም አካል የኃይል አቅርቦቱ ይቋረጣል” ሲሉም ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ከፍተኛ የገንዘብ ችግር አጋጥሞታል የተባለው የጋና የመብራት ኃይል ዕዳቸውን ያልከፈሉ ደንበኞችን መብራት በማቋረጥም ይታወቃል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አገሪቱ በአስር ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ የምጣኔ ኃብት ቀውስ እየታገለች ከመሆኑ ጋር ተያይዞም የአገሪቱ የኃይል እጥረት ተባብሷል።
የአገሪቱ የግል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢዎች በመንግሥታዊው የመብራት ኃይል ያልተከፈላቸው 1.6 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንዳላቸውም የድርጅቶቹ ተወካይ የሆነው ኤሊክፕሊም ክዋባላ አፔቶግባር ገልጸዋል። ድርጅቶቹ ባልተከፈላቸው ውዝፍ ዕዳ ምክንያት ስራቸውን እንደሚያቆሙም ከጥቂት ወራት በፊት አስጠንቅቀው ነበር።