ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“የዳሬሰላሙ ድርድር እንዳይሳካ ያደረገው መንግሥት ነው ብዬ አምናለሁ” - አቶ ታዬ ደንደአ
የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ በኦሮሞ ፖለቲካ እና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን እና አቋማቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በማጋራት ይታወቃሉ።
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) አባል የሆኑት አቶ ታዬ፣ አገሪቷን በሚያስተዳድረው የብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው ያገለግላሉ።
በአጠቃላዩ በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየተከሰቱ እና አሁንም ባሉ ችግሮች ዙሪያ እራሳቸው አባል የሆኑበትን መንግሥት ይወቅሳሉ።
ከአምስት ዓመት በፊት የተገባውን ቃል፣ ኦሮሚያ ውስጥ ባለው ጉዳይ፣ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል በነበረው ድርድር እና ቤተሰባቸው ላይ በደረሰው ጉዳት እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በኦሮሚያ ስላለው ሁኔታ
በ2010 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ በመጣው የፖለቲካ ለውጥ ኦሮሞ ወደ ከፍተኛው የፖለቲካ ሥልጣን መጣ። ያኔ ብልጽግና እና ዲሞክራሲ ይመጣል ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር ይላሉ አቶ ታዬ ደንደአ።
“ትልቅ ደስታ ነበር የተፈጠረው። ሰው ተስፋ ያደረገው ለ150 ዓመታት የነበረው ችግር ተዘግቶ ዲሞክራሲ ይመጣል፣ የሚል ነበር። የሕዝብ ጥያቄ የሆኑት የቋንቋ፣ የምጣኔ ሃብት እና ሌሎች ትልልቅ ጉዳዮች ተቆጥረው ይመለሳሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር” ይላሉ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታዬ ደንደአ።
ሕዝብ ሰላም እንደሚያገኝ፣ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ ሰው በጋራ ሠርቶ እድገት ይመጣል ተብሎ እንዲሁም ፖለቲካችን ይሰለጥናል የሚል የብዙ ሰዎች ተስፋ ነበር ይላሉ።
“ኦሮሞ እርስ በእርሱ ተነጋግሮ ችግሩን ይፈታል፣ ከብሔር ብሔረሰቦች ጋርም በሰላም ይኖራል የሚል ትልቅ ተስፋ ነበር። የፖለቲካ ምኅዳሩም መጀመሪያ አካባቢ ክፍት ነበር። የሰው ተስፋም ትልቅ ነበር። የሕዝብ ተነሳሽነትም ትልቅ ነበር” በማለት በለውጡ ወቅት የነበረውን ያስታውሳሉ።
ይህ ለውጥ እንዲመጣ፣ ሌሎች የሕዝብ ክፍሎች የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉ ሌሎች ደግሞ በሚችሉት ሁሉ አስተዋጽኦ ያደርጉ ነበር የሚሉት አቶ ታዬ፣ ከዚያ በኋላ እንዴት ወደፊት እንሄዳለን የሚል ዕቅድ ባለመኖሩ፣ አሁን ያለው ችግር መፈጠሩን ያነሳሉ።
“ለውጡ ከመጣ በኋላ ሰው ወደ ጥቅም እና ሥልጣን ማጋደል ጀመረ። እርስ በእርስ መጠላለፍ መጣ። ወደ ቀኝ እና ወደ ግራ መሳሳብ መጣ። ሌላው ቀርቶ በኦዲፒ ውስጥ ተመካክሮ በአንድ አጀንዳ ላይ አብሮ መሥራት ራሱ አልተቻለም ነበር” ይላሉ።
በፓርቲያቸው ውስጥ መመካከር ከቀረ በኋላ የኦሮሞ ፖለቲካ አንድ ከመሆን ወደ መበታተን አመራ። በኦሮሞ ፖለቲካ ሜዳ ውስጥ በተፈጠረው ግራ መጋባት፣ ሌሎች ወደ ጫካ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ የሕዝቡ ሰቆቃ በማምታታት ሥልጣናቸውን ማራዘም ለሚፈልጉት ትልቅ ዕድል ፈጠረላቸው ሲሉ ይከሳሉ።
ማዕከሉን ተቆጣጥሮ በሕዝብ ሰቆቃ ይነግዳል የሚሉትን አካል አቶ ታዬ በስም አልጠቀሱም።
ከለውጥ በኋላ የኦሮሞን ትግል በትክክል እና መጀመሪያ ቃል በተገባው መንገድ ሥራ ላይ አለመዋሉ ኦሮሞ በ150 ዓመት ውስጥ አይቶ በማያውቀው መከራ ውስጥ አድርጎታል የሚሉት አቶ ታዬ “በ150 ዓመት ውስጥ በትግል ከተሰዉት ይልቅ፣ ከአሸነፈ በኋላ መልሶ በኪሳራ ሰቆቃ ውስጥ ገባ።”
ላጋጠመው ችግር ተጠያቂ ማን ነው?
ለተፈጠረው ችግር ከዚህ ቀደም በተለያየ መንገድ በኦሮሞ ትግል ውስጥ የተሳተፉት ተጠያቂ እንደሚሆኑ የሚጠቅሱት አቶ ታዬ ራሳቸውም ቢሆን ለተጠያቂነት ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራሉ።
“መንግሥት ትልቅ ተጠያቂነት አለበት። የፖለቲካ ሜዳው ምቹ እንዲሆን፣ ሕዝብ ወደ ዲሞክራሲ እንዲሻገር ማድረግ የመንግሥት ግዴታ ነበር። መንግሥት ውስጥ የነበሩ ደግሞ ውይይትን አልመረጡም” ይላሉ።
አቶ ታዬ እንደሚሉት አሁን በኦሮሚያ እና በአገሪቷ የተከሰቱ ችግሮች ከዚህ በፊት በ2011 ዓ.ም. በድርጅት ጉባዔ ላይ እንደሚከሰቱ ተናግረው ሰሚ ማጣታቸውን ያስታውሳሉ።
“በ2011 ምሁራን ጋር ባደረግነው ውይይት አራት ትልልቅ ችግሮች እንደሚከሰቱ ተናግሬ ነበር። የመጀመሪያው የሰላም እና የደኅንነት እጦት ሊከሰት እንደሚችል፣ የምጣኔ ሃብት መናጋት፣ የአስተዳደር እና ዲፕሎማሲ ውድቀት እንደሚከሰቱ ተናግሬ ነበር” በማለት መንግሥት ቀድሞ መዘጋጀት እንዳለበት ተናግረው እንደነበር ያስታውሳሉ።
አሁን ላይ ሆነው ወደ ኋላ ሲመለከቱ እርሳቸው ከጠቀሱት ችግሮች ውስጥ ሦስቱ በተጨባጭ ተከስተው ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ያነሳሉ።
እነዚህ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ መሥራት ባለመቻሉ፣ አገሪቷን የሰብዓዊ እና የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲሁም ድቀት ማስከተሉን በማስታወስ፣ በትግራይ ጦርነት ብቻ የ28 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ መድረሱን ይናገራሉ።
ሙስና ቀይ መስመር መሆኑ ቀርቶ ቀይ ምንጣፍ ሆነ. . .
አቶ ታዬ ደንደአ በአሁኑ ወቅት በመንግሥታቸው ወስጥ ሙስና እና ብልሹ አሰራር በከፍተኛ ሁኔታ የተንሰራፋ መሆኑን በግልጽ ይናገራሉ።
“ድሮ መሬት ይዘረፋል ከሚባለው በላይ አሁን ሕጋዊ ሆኖ በቃላት መግለጽ በሚከብድ መልክ እየተንሰራፋ የአስተዳደር ቀውስ ተፈጥሯል” ይላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የኑሮ ውድነት ሰማይ ደርሶ የመንግሥት ሠራተኛ ቤት ኪራይ መክፈል አቅቶት ከዚህ ቀደም ዘመዶቹን ይረዳ የነበረው ሠራተኛ አሁን በቤተሰቦቹ አንደሚደጎም ይገልጻሉ።
በ2012 ዓ.ም. ፓርቲያቸው ወደ ብልጽግና በሚሸጋገርበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ባሉበት ቦታ ለውጡ ባለቤት አንዲኖረው፣ ለለውጥ ተብለው የተሰዉትን እውቅና አንዲሰጣቸው፣ ለወጣቶች የሥራ እድል እንዲፈጠር እንዲሁም ለሙስና ተጠያቂነት እንዲኖር ጠይቀው ሰሚ እንዳላገኙ አቶ ታዬ ይናገራሉ።
የሚገዳደሉት ወንድማማቾች ናቸው
ኦሮሚያ በአሁን ሰዓት ጦርነት ውስጥ መሆኗን የሚናገሩት አቶ ታዬ፣ በዚህ ጦርነት ውስጥ ሕዝብ ለከፋ ሰቆቃ መዳረጉን ገልጸዋል።
“ሕዝባችን ባለፉት አምስት ዓመታት ይሞት ነበር። ስንት እንደሞተም በቁጥር አይታወቅም። በጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በእስራኤል ስንት አንደሞተ፣ ከፍልስጤም ስንት አንደሞተ በቁጥር ይታወቃል። በኦሮምያ ያለው እልቂት ግን የሚታወቅ ነገር የለም።”
ስንት የደሃ ሰው ቤት ተቃጠለ፣ ስንት ሰላማዊ ዜጋ ሞተ፣ ምን ያህል ንብረት ተዘረፈ፣ ስንት ሰው አካሉ ጎደለ፣ የሚለውን የሚያውቀው ሰው የለም” በማለት በኦሮሚያ ከየትኛውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ፣ “ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መልኩ ነው አሁን እየሆነ ያለው በማለት ቁስሉ ከባድ” መሆኑን ይገልጻሉ።
“መሮ ለሰላም ቁርጠኝነት አሳይቶ የእኔ መንግሥት ግን ሰላሙን አደናቀፈ”
በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የመጀመሪያው የሰላም ድርድር ተጀምሯል የሚል ዜና የተሰማበት ቀን፣ በገብረ ጉራቻ ከተማ ሕዝብን ሲያወያዩ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ታዬ፣ ሕዝብ ከፍተኛ ተስፋ አድርጎ እንደነበር ያስታውሳሉ።
“ተቃጥለናል፣ ተቸግረናል፤ ለእግዚአብሔር ስትሉ ይህ ውይይት በውጤት እንዲጠናቀቅ አድርጉልን። በሰላም ካልተጠናቀቀ ድሮም አልቆልን ነበር አሁን ደግሞ የባሰ እናልቃለን ብለው ነግረውኝ ነበር” በማለት ሕዝቡ ድርድሩን በጉጉት ይጠብቅ አንደነበር ይገልጻሉ።
የመጀመሪያም ሆነ ሁለተኛው ድርድር ሲጀመር የወንድማማቾች መካከል የሚደረገው ጦርነት እንዲቆም በለውጡ ጊዜ የተገባ ቃል ሥራ ላይ እንዲውል፣ በውስጥ እና በውጪ ያሉ የኦሮሚያ ተወላጆች በሙሉ ልብ ይጠብቁ ነበር።
የኦሮሞ ፖለቲካ ችግር አሁን ያለበት ቦታ ከደረሰ እና ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸው በሰላም እንዲፈታ ከወሰኑ በኋላ “ይህ የሰላም ድርድር እንዲደናቀፍ ያደረገው እኔ ያለሁበት መንግሥት ነው” ይላሉ አቶ ታዬ ደንደአ።
“እኔ ያለሁበት መንግሥት ‘ችግር ውስጥ ነን፤ ተወያይተን መፍትሄ እናመጣለን’ ብዬ ስጠይቅ ቤቱ ለውይይት ክፍት አይደለም በማምታታት እና በማደናገር ማለፍ ነው የሚፈለገው። የእኔ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ጸባይ ነው ያለው” ይላሉ።
“በሁለተኛ ደረጃ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን የሚመራው መሮ፣ መንግሥት ከፈለገ ይግደለኝ ብሎ፣ መንግሥት በሚቆጣጠረው የአየር ክልል ውስጥ አልፎ፣ ወደ ታንዛኒያ በአውሮፕላን መሄዱ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ነው የሚያሳየው ብዬ አምናለሁ” ይላሉ አቶ ታዬ።
በታንዛኒያ ድርድሩ ተጀምሮ በሁለተኛው ቀን፣ ከመንግሥት ወገን ፕሮፓጋንዳ መንዛት እንደተጀመረ የሚገልጹት አቶ ታዬ “ሸኔን አጥፍተናል፣ አከርካሪውን ሰብረናል የሚል ፕሮፓጋንዳ ተጀመረ። ፕሮፓጋንዳ ብቻ ሳይሆን ጦር ከያለበት ተንቀሳቅሶ በአምስት ዓመት ውስጥ ያላለቀው ጦርነት በድርድሩ ጊዜ ለመጨረስ፣ እንቅስቃሴ ተደረገ” በማለት ከመንግሥት ወገን ለሰላም ፍላጎት አለመኖሩን ያስረዳሉ።
መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከሳምንታት በፊት ለረጅም ቀናት በታንዛኒያ ዳሬሰላም ሲያደርጉት የነበረው ሁለተኛ ዙር ድርድር ያለ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።
የሰላም ድርድር፡ የሰላም ሚኒስቴር ወይስ የፍትህ ሚኒስቴር?
አቶ ታዬ ከህወሓት ጋርም ሆነ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በሁለት ዙር የተደረገው የሰላም ድርድር የሰላም ሚኒስቴር እንዳልተሳተፈበት በመጥቀስ ይወቅሳሉ።
“የሰላም ድርድር ጉዳይ በሕግ የተሰጠው ለእኛ ነው። በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 ላይ የሰላም ጉዳይ እኛን እንደሚመለከት ነው የሚገልጸው። ነገር ገን የተሳተፈው የፍትህ ሚኒስቴር ነው። ሕጉ የሰላም ድርድር የፍትህ ሚኒስቴርን ይመለከታል አይልም። በኋላ አንድ ወገን ስምምነቱን ካልተቀበለ በሕግ የሚጠይቀው የፍትህ ሚኒስቴር ነው” ይላሉ አቶ ታዬ።
ነገር ግን ፍትህ ሚኒስቴር ራሱ የስምምነቱ አካል ሆኖ ነገ ተመልሶ አጥፊውን አካል እንዴት ይጠይቃል ሲሉ ጥያቄ በማንሳት የሚኒስትር መሥሪያ ቤታቸው ሚና መገፋቱን ይጠቅሳሉ።
የሰላም ሚኒስቴር ከተቋቋመ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ሰላም አልመጣም ተብለው የተጠየቁት አቶ ታዬ፣ የሰላም ሚኒስቴር በምክክር በሚገነባው ሰላም ላይ ይሠራል እንጂ ጦርነት ከተነሳ ተቋማቸው ተጠያቂ እንደማይሆን ይናገራሉ።
“እኛ ሕዝቦች እንዳይጋጩ ሃሳብ እናቀርባለን። ሕዝብ እናወያያለን። ከዚያ በተረፈ ችግር ሲፈጠር ወደ መገዳደል የሚሄድ አካል፣ ጦርነት ወይንም ግጭትን ለማስቆም ሥልጣን አልተሰጠንም” ሲሉ ይመልሳሉ አቶ ታዬ።
ራስዎን ከታሪክ ተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ ነው የመንግሥት ባለሥልጣን ሆነው መንግሥትን የሚተቹት? ተብለው የተጠየቁት አቶ ታዬ፣ “እኔ ለአስር ዓመት እስር ቤት ነበርኩ። ሽርፍራፊ ሳንቲም ለማግኝት ያደረግኩት ነገር የለም። ለኦሮሞ ሕዝብ ይጠቅማል ብዬ ያልኩትን አደርጋለሁ። ስለዚህ ከእኔ የሚጠበቀውን አደርጋለሁ። የምናገረው መስመር እንዲይዝ ነው እነጂ ራሴን ነጻ ለማድረግ አይደለም” በማለት ተጠያቂ ለመሆኑ ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ ተሰሚነት ስላጡ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሃሳባቸውን ለሕዝብ ለመግለጽ እንደወሰኑም ገልጸዋል።
“አገር ውስጥ፣ ሕዝብ ውስጥ የጠፋውን ነጻነት ለራሴ ብቻ የምኖረው ነጻነት ከየት መጥቶ ነው ራስህን ነጻ ለማድረግ ነው ተብዬ የምጠየቀው። ነገሩ ከገባኝ ቆይቷል።”
ጊዳሚ ያልተፈታ ጦርነት፣ ሱልልታ ከደረሱ በኋላ አይፈታም
በዳሬሰላም የነበረው የሰላም ድርድር ከፈረሰ በኋላ የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ “ሰላምን እምቢ ያለ አካል ተገዶ ወደ ሰላም እንዲመጣ እርምጃ እየተወሰደበት ነው ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር። ይህ መግለጫ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ያለው ችግር በጦርነት ለመፍታት እየተሄደበት መሆኑን የሚገልጽ ነው ይላሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታው።
አቶ ታዬ “ሰዎቹ [ታጣቂዎቹ] ጊዳሚ እያሉ መፍትሄ ያላመጣ ጦር አሁን ሱሉልታ ከደረሱ በኋላ ችግሩን አይፈታም” በማለት ሃሳባቸውን ይገልጻሉ።
“ከዚህ ቀደም ይህ ጦር በቄለም ወለጋ ውስጥ በአንድ ወይንም በሁለት ወረዳ ውስጥ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እየተዋጋን ነው። ስለዚህ ይህ ጦር ችግሩን አልፈታም ማለት ነው። አሁን ደግሞ ተስፋፍቶ ይህ ጦር የሌለበት ዞን የለም ማለት ትችላለህ። አሁን አንዲያውም እዚህ ቅርብ ሱልልታ ነው ያለው” በማለት ጦርነት መፍትሄ አንዳልሆነ እና እንዳላመጣ ምልከታቸውን ይገልጻሉ።
አቶ ታዬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ሁለት ጊዜ በአካል አግኝተው ኦሮሚያ ውስጥ ባለው ችግር ላይ እደተወያዩ ይናገራሉ።
“የመጀመሪያው የከረዩ አባገዳዎች በተገደሉበት ወቅት ነው ከእርሳቸው ጋር የተነጋገርኩት። ‘ኦሮሚያ በተመለከተ የሚደርስዎት ሪፖርት የውሸት ነው። የሚባለው ልማትም የውሸት ነው። ከሰላም ጋር ተያይዞ የሚነገረውም እንደዚያ አይደለም። ሕዝባችን እያለቀ ነው’” ብለው እንደነገሯቸው ይገልጻሉ።
አንድ የቤተሰብ አባል ከታጣቂዎች ጋር ከተቀላቀለ ቤተሰቡ የሸኔ ቤተሰብ በመባል እናት እና አባት፣ ልጅ እና ወንድም መታሰር እና ለሰቆቃ እንደሚዳረግ፣ በኦሮሚያ ውስጥ ሰቆቃ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚፈጸም ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአካል ባገኙበት ወቅት እንደነገሯቸው ገልጸዋል።
ከሕግ ውጪ ግድያ፣ በሕግ ቁጥጥር ስር ያለን ሰው ማሰቃየት፣ እና በከረዩ አባገዳዎች ላይ የተፈጸመውን አንደምሳሌ በማንሳት ማብራራታቸውን ይናገራሉ።
“ያስተካከሉት መስሎኝ ነበር። ግን ምንም አላደረጉም። ያኔ ሰዎቹን የገደሉት አልተጠየቁም። ያኔ በዚህ ጉዳይ ላይ የተጠረጠሩት፣ ያኔ በነበሩበት ሥልጣን ላይ ነው ያሉት። ለምን አንደተዉት አልገባኝም” ይላሉ።
በጨፌ ኦሮሚያ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ “ሃሳቤን አንዳልገልጽ ድምጼን አፈኑት” በማለት ለሁለተኛ ጊዜ ከዚያ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መገናኘታቸውንም ይናገራሉ።
በኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ‘ሃሳቤን አንዳልገልጽ ከለከሉኝ’ ብለው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከጻፉ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መገናኘታቸውን ይገልጻሉ።
“እየሄደ ያለው ነገር ትክክል አይደለም። ለምን እነደዚህ አደረክ ብለው ጠየቁኝ። እኔ ሕዝብን ነው የወከልኩት። የመናገር መብት መከልከል የለበትም። ሰው ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ መብቴን ስለሚያፍን ነው የተናገርኩት አልኳቸው።
“ዝርፍያ ተስፋፍቷል። የሰላም እጦት የሰዎችን ነፍስ እየቀጠፈ ነው። ይህ ካልተፈታ ሥልጣን አለን ብለን እዚህ መቀመጣችን ምን ፋይዳ አለው? ለምን ይህ ችግር አይፈታም? ብዬ ነግሬያቸው ነበር። ከዚያ ወዲህም ያደረጉትን ነገር አላየሁም። ያለው ሁኔታ እንደትናንትናው ነው” ይላሉ አቶ ታዬ።
“እናቴ ያለችኝ አይረሳኝም”
አቶ ታዬ ጨፌ ኦሮሚያን የተቀላቀሉት ሰሜን ሸዋ የኩዩ ወረዳ እና አካባቢ ሕዝብን በመወከል ነው። እርሳቸው የወከሉት ሕዝብ በሁለቱ ወገን በሚደረገው ጦርነት ውስጥ እየተሰቃየ መሆኑን ይናገራሉ።
በአሁኑ ጊዜ ከሰላም እጦት የተነሳ የወከላቸውን ሕዝብም ሆነ ቤተሰባቸወን ለማየት ወደ አካባቢያቸው መሄድ እንዳልቻሉ እና እናታቸውን ጨምሮ ዘመዶቻቸው በዚህ የሰላም እጦት ምክንያት ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ይናገራሉ።
“እናቴ ገጠር ትኖር ነበር። እዚያ የእርሻ መሬት አላት። ይህ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከቀዬዋ ተፈናቅላለች። በአባቴ እና በእናቴ ወገኖች መካከል ቤታቸው የተቃጠለባቸው ብዙ ናቸው። በአንድ በኩል ከመንግሥት ጋር ነው ያላችሁት፣ በማለት በሌላ በኩል ሸኔን ትደግፋላችሁ በማለት የተገደሉ የተሰቃዩ አሉ።”
የቅርብ ዘመዳቸው የሆነ ግለሰብም ማን እንደሆኑ በማይታወቁ ሰዎች ታግተው ከፍተኛ ብር በመክፈል መለቀቃቸውንም ይናገራሉ።
አቶ ታዬ ከዓመታት በፊት ወደ መብት ትግሉ ሲቀላቀሉ እናታቸው ያሉትን ያስታውሳሉ።
“እናንተ የምትሉት ጭቆና የታለ? እኛ በሰላም መሬታችንን አርሰን፣ በሰላም ገበያችን ሄደን አንገባለን አሉኝ። አሁን ቤት ከተቃጠለባቸው፣ ከብቶቻቸው ከታረዱባቸው እና ዘመዶቻቸው እና ወንድሞቻቸው ከተሰቃዩባቸው በኋላ ‘እናንተ ፍለጋ የወጣችሁት ነጻነት ለካ ይህ ነው’ አሉኝ እናቴ” ይላሉ አቶ ታዬ።
“በዚህ ጦርነት ወንድማማቾች ናቸው የሚገዳደሉት” የሚሉት አቶ ታዬ ሕዝብ መካከል ስቃይ እና ለአንግልት መዳረጉን በመጥቀስ የሰላም ድርድር ብቻ መፍትሔ እንደሆነ በአጽንኦት ይናገራሉ።
“ታጥቆ ለሚታገለውም፣ እኔ ያለሁበት መንግሥትም ያለኝ መልዕክት ሕዝባችን ከሚፈለገው በላይ ዋጋ ከፍሏል። ከዚህ በላይ ዋጋ መክፈል የለበትም። ለሕዝብ ስንል በውይይት ችግራችንን ብንፈታ መልካም ነው” ይላሉ።