ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“ፖለቲካ አያውቁም፤ አላማ የላቸውም ተብለን የተናቅነው ለድርድር ተቀመጥን” ጃል መሮ
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል በሚካሄደው የሰላም ንግግር ላይ ለመሳተፍ በታንዛንያ የሚገኘው የጦሩ ዋና አዛዥ ኩምሳ ድሪባ “ፖለቲካ አያውቅም” የተባለው ሠራዊታቸው ኃያላን ባሉበት ለድርድር መቀመጡን ተናገረ።
መንግሥት 'ሸኔ' የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ የሆነው ኩምሳ ድሪባ ይህንን የተናገረው ቅዳሜ ኅዳር 08/ 2016 ዓ.ም. በዙም አማካኝነት ከደጋፊዎቹ ጋር ባደረገው ወይይት ላይ ነው።
“ፖለቲካ አያውቁም፤ ልጆች ናቸው፤ አላማ የላቸውም። እርስ በርስ አይስማሙም ተብለን ስንናቅ የነበረው [የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት] ዛሬ ኃያላን ባሉበት እየተደራደርን እንገኛለን” በማለትም ተናግሯል።
ለዓመታት የዘለቀውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት እየተደረገ ያለው ሁለተኛ ዙር ንግግር በታንዛንያ የቀጠለ ሲሆን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ዋና አዛዥ ጃል መሮ ከአገር ሲወጣም ሆነ ሲሳተፍ የመጀመሪያው ነው።
ከአስር ቀናት በላይ የተካሄደው ውይይት መቼ እንደሚጠናቀቅም ሆነ ስለተደረሰበት ደረጃ እስካሁን ቢቢሲ በቂ መረጃ አላገኘም።።
ለመጀመሪያ ጊዜ በዳሬሰላም የሰላም ድርድሩ ላይ ተሳታፊ የሆነው ድሪባ ኩምሳ በመካሄድ ላይ ስላለው የሰላም ድርድር ማብራሪያ ባይሰጥም በዙም ባደረገው አጭር ቆይታ “ሻይ ሰዓት ላይ ነው እየተናገርኩ ያለሁት” ሲል አስታውቋል።
“አሁን እየተካሄደ ስላለው ድርድር ይህ ነው፣ ያ ነው ማለት አልፈልግም። ነገር ግን ትልቅ ፈተና እንዳለብን ማወቅ አለባችሁ” ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።
“በሥራችን ገምግሙን እንጂ በወሬ ብቻ አትመሥረቱ። እኛ ሥራ ላይ ነን” ሲልም ተደምጧል።
“የኦሮሞ ሕዝብ መወዳደር ያለበት በወሬ ሳይሆን በተግባር ነው። አንገታችሁን ደፍታችሁ በርትታችሁ ሥሩ። ታይታ ጥቅም የለውም” ብሏል።
የኦሮሞ ነጻነት እንቅስቃሴን በገንዝብ እየደገፉ ላሉ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ባደረገው ንግግር “በገንዘብ ለምታደርጉት ድጋፍ እናመሰግናችኋለን። እኔ በበኩሌ ገንዘቡም ይቅር እያልኩ ነው። ሁሉም ሰው ባለው ሙያ እና ችሎታ እንዲደራጅ እፈልጋለሁ” ሲልም አስረድቷል።
“በሁሉም ነገር ባንስማማም እንዳልተስማማን አምነን በሰላም መኖር ራሱ እንደ አንድ ትግል ነው የማየው” ሲልም ተደምጧል።
አክሎም “እኛ መገንባት የምንፈልገው ሥርዓትን ነው። ለሚመጣው ትውልድ ምን ዓይነት ሥርዓት እና አገር እናስረክባለን የሚለው ነው የሚያሳስበን” አክሎም “እኛ እናልፋለን ነገር ግን ለመጪው ትውልድ ምን ዓይነት አሻራ ጥለን ነው የምናልፈው የሚለው ነው የሚያሳስበኝ” ብሏል የጦር አዛዡ።
የጦር አዛዡ ስለ ገንዘብ ጉዳይ ለምን እንዳነሳ ግልጽ ባይሆንም አንዳንድ መጭበርበሮች እንዳሉ ግን ጠቁሟል።
“ኦሮሞ ሌላ ፓርቲ መመሥረት” እንደሚችል የተናገረው ድሪባ ኩምሳ “የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብቻ አይደለም። የራሳችሁ ፓርቲ መሥርቱ። ለዚህ ሰፊ ሕዝብ ብዙ ፓርቲዎች ቢኖሩት እኔ ተቃውሞ የለኝም። ነገር ግን በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ስም ግን መነገድ ይቁም” ሲልም ለደጋፊዎቹ ተናግሯል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በዋና አዛዡ ኩምሳ ድሪባ እና በምክትሉ ገመቹ አቦዬ በሚመራ ልዑካን የታንዛንያው የሰላም ውይይት ተሳታፊ መሆኑንም ኅዳር 3/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በሽብርተኛ ቡድንነት በመንግሥት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሲሆን፣ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።
በመጀመሪያው ዙር ውይይት የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ ታንዛንያ ይገኛሉ።
ሁለቱ ልዑካን በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተዛምቶ ለበርካቶች እልቂት ለሆነው ጦርነት እልባት ለማግኘት የፌደራሉን መንግሥት ወክለው በፕሪቶሪያ ከህወሓት ጋር የተደራደሩት ልዑካን አባል መሆናቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እና ባለሥልጣናትን ጨምሮ ሰባት ልዑካን በውይይቱ ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
ከፌደራሉ መንግሥት ልዑካን በተጨማሪ የኦሮሚያ ክልል ሁለት ተወካዮች በውይይቱ ላይ መገኘታቸውን ቢቢሲ ሰምቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥትን እና የትግራይ ኃይሎችን በማሸማገል ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በታንዛንያ እንደሚገኙም ተነግሯል።
በመጀመሪያው ዙር ንግግር ኬንያ እና ኖርዌይ የአሸማጋይነት ስፍራ የነበራቸው ሲሆን የአሜሪካ ዲፕሎማቶችም ድጋፍ እየሰጡ እንደነበር ቢቢሲ ለውይይቱ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሰምቶ ነበር። በአሁኑ ውይይት አሜሪካ፣ ኬንያ፥ ኖርዌይ እና ኢጋድ የማሸማገሉን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በአምስት ከፍተኛ የጦር አዛዞዦች እና በሁለት የዲፕሎማሲ ተወካዮች በአጠቃላይ በሰባት ልዑካን ተወክሏል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች እየተባባሱ ይገኘሉ።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አካላት ለግጭቱ ሰላማዊ እልባት ለመስጠት እየተወያዩ ባለበት ወቅትም ጦርነት በተለያዩ ወረዳዎች ተጠናክሮ መቀጠሉን ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል።
በምዕራብ ሸዋ በሚገኙን ዲሬ ኢንጪኒ በተባለው አካባቢ እና በሆሮ ጉድሩ ጀማ ገናቲ በተባለ ስፍራ በባለፉት ሁለት ቀናት ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መደረጉንም ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሰላም ድርድር እየተካሄደ ባለበት ወቅት ግጭቱ ለምን እንደተባባሰ ግልጽ ባይሆንም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከስድስት ወር በፊት በታንዛኒያ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ዛንዚባር እየተደረገ በነበረው የመጀመሪያ ዙር ድርድርም ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ውይይቱ ከተጀመረ ከአንድ ሳምንት በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በኩል ንግግሩ እየተካሄደ ስለመሆኑ ቢያረጋግጥም ዝርዝሩ አልተገለጸም።
የጋራ መተማመን እና መግባባት ለመፍጠር በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በመንግሥት መካከል ውይይት እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ድርድር በሁለቱ ወገኖች መካከል መግባባት ተፈጥሮ እንደነበርም መገለጹ ይታወሳል።