መኪናዋን በስህተት በመንገዱ ላይ ያዞረችውን ሴት የገደለው አሜሪካዊ 25 ዓመት እስር ተፈረደበት

በአሜሪካ መንገድ ተሳስታ በገጠር የመኪና ጥርጊያ መንገድ ላይ መኪናዋን ያስገባችውን የ20 ዓመት ወጣት ተኩሶ የገደለው ግለሰብ በ25 ዓመት እስር ተቀጣ።

ሟቿ ኬይሊን ጊሊስ እና ጓደኞቿ ከጥቂት ወራት በፊት በኒውዮርክ ግዛት የሚሄዱበትን ድግስ (ፓርቲ) አድራሻ እየፈለጉ በነበረበት ወቅት ነው ወደ ግለሰቡ የጥርጊያ መንገድ በስህተት የገቡት።

ኬቨን ሞናሃን የተባለው ይህ ግለሰብ ጊሊስን አንገቷ ላይ በጥይት ከመታት በኋላም ሕይወቷ አልፏል።

የ66 ዓመቱ ግለሰብ በሁለተኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው በጥር ወር ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ ከፍተኛው የተባለውን የ25 ዓመት እስራትም እንዲቀጣ ጠይቋል።

ዳኞቹም ግለሰቡን በግድያ ወንጀል እንዲሁም በግዴለሽነት የሰዎችን ሕይወት አደጋ ውስጥ በመክተት እና ማስረጃዎችን በማበላሸት ጥፋተኛ ሆኖ አግኝተውታል።

አርብ ዕለት ውሳኔው የተላለፈበት ሞናሃን በችሎቱ ላይ ለመናገር የተሰጠውን ዕድል ውድቅ አድርጓል።

ከፍርድ ቤቱም ሲወጣ አንድ ሰው “ፈሪ” በማለትም እንደዘለፈው የኤፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

“በመኪና መንገድዎ ላይ ስላዞሩ ሰዎች ላይ በጥይት መተኮስ እንዲሁም መግደል እንደማይቻል ሊገነዘቡ ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ” ሲሉም ዳኛው አዳም ሚሼሊኒ መናገራቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።

ጊሊስ እና ጓደኞቿ ከጥቂት ወራት በፊት ከአልባኒ በስተሰሜን ምሥራቅ 88 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኬብሮን በተሰኘች ትንሽ ከተማ ወደ ሞናሃን ረጅም እና ጠመዝማዛ የመኪና መንገድ የገቡት የድግስ አድራሻ ፍለጋ ነበሩ።

ይህች ገጠራማ ቦታም ደካማ የሞባይል አገልግሎት ያላት ናት ተብሏል።

ጊልስና ጓደኞቿን በዙሪያው ያገኘው ግለሰቡ “በወራሪዎች ተከብቤያለሁ” ብሎ እንዳሰበም ተናግሯል።

ሟቿ እና ጓደኞቿ የተሳሳተ ስፍራ ውስጥ እንደገቡ ሲያውቁ መኪናቸውን ሲያዞሩ ግለሰቡ ከቤቱ ወጥቶ ከበረንዳ ላይ ሁለት ጥይቶችን ተኩሷል።

ሁለተኛውም ጥይት መኪናውን ሲያሽከረክር ከነበረው የወንድ ጓደኛዋ አጠገብ የተቀመጠችውን ጊሊስን ያገኛት ሲሆን ሕይወቷም አልፏል።

የወንድ ጓደኛዋ ገዳዩን ሞናሃን “በፍጹም ይቅር ሊለው እንደማይችልም” ተናግሯል።

የሞናሃን ጎረቤት እንደተናገሩት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሞናሃን ተሳስተው በመንገዱ በሚያዞሩ ሰዎች በጣም እየተበሳጨ እንደነበር ተናግረዋል።

የጊሊስ ጓደኞች በመኪና መንገዱ ላይ የነበረውን የግል የሚለውን ምልክት እንዳላስተዋሉ በችሎቱ መስክረዋል።