እስራኤል የአሶሺየትድ ፕሬስን የጋዛ የቀጥታ ዘገባ በማቋረጥ ወስዳቸው የነበሩ ካሜራዎችን መለሰች

የእስራኤል መንግሥት አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል በጋዛ በቀጥታ የሚያስተላልፈውን ዘገባ በማቋረጥ ወስዷቸው የነበሩ የዜና ወኪሉን ካሜራዎች እና የስርጭት መሳሪያዎች መለሰ።

እስራኤል የዜና ወኪሉን የቀጥታ ዘገባ ትናንትና ማክሰኞ ግንቦት 13/ 2016 ዓ.ም በማገድ በነጻ ጋዜጠኝነት ባደረገችው ገደብ ከፍተኛ ትችት አስተናግዳለች።

የእስራኤል መንግሥት በደቡባዊ እስራኤል የሚገኘውን የዜና ወኪሉን ካሜራዎች እና የስርጭት መሳሪያዎች የወሰደው ለአልጀዚራ ቪዲዮዎችን በመስጠት አገሪቱ ያወጣችውን የሚዲያ ህግ ጥሷል የሚል ክስ ከሰነዘረ በኋላ ነው።

የእስራኤል ባለስልጣናት አዲሱን የብሮድካስት ህግ በመጠቀም ሚያዝያ 27/ 2016 ዓ.ም በእስራኤል የሚገኘውን የአልጀዚራ ቢሮ በመውረር፣ መሳሪያዎቹን ወርሰዋል፣ ስርጭቱን እና ድረ ገጾቹን አግደዋል።

እስራኤል የኤፒን የስርጭት ዕቃዎች ከወሰደች በኋላ የባይደን አስተዳደር፣ በጋዜጠኝነት ላይ የሚሰሩ የመብት ተሟጋቾች እና የእስራኤል ተቃዋሚ መሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ውሳኔ በማውገዝ እንዲቀለበስ ግፊት አድርገዋል።

አለም አቀፍ ጫናዎች መበርታታቸውን ተከትሎ የእስራኤል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሺሎሞ ካርሂ ውሳኔው እንዲቀለበስ አድርገዋል።

ዋይት ሃውስ ስጋቱን የገለጸ ሲሆን የውጭ ፕሬስ ማህበር “የእስራኤል መንግሥት ሚዲያዎችን ለማፈን የሚወስዳቸው እርምጃዎች አስደንግጦኛል” ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ድርጊቱን “አስደንጋጭ” ሲል አውግዟል።

የዜና ወኪሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ላውረን ኢስቶን "የእስራኤል መንግስት የወሰደውን እርምጃ በጽኑ እንቃወማለን” ብለዋል።

የእስራኤል ሚኒስትር በበኩላቸው የኤፒ የስርጭት ማስተላለፊያዎችን አገራቸው የወሰደችው ላገደችው አልጀዚራ ምስሎችን በመስጠት አዲሱን የሚዲያ ህግ በመጣሱ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ በኤክስ ላይ ባሰፈሩት መግለጫ በዜና ወኪሉ የተጋሩት ምስሎች “ሰራዊቱ በሰሜናዊ ጋዛ ያለውን አሰፋፈር በማሳየት ጦሩን አደጋ ውስጥ ሊጥሉ እንደሚችሉ የደህንነት ባለስልጣናት እና መንግሥት በመወሰኑ ነው” ብለዋል።

ምስሎቹን ከገመገሙ በኋላም መሳሪያዎቹ ለዜና ወኪሉ የተመለሰ ሲሆን “ይህም በመከላከያ ሚኒስቴሩ የተለየ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ነው” ብለዋል።

የእስራኤል መንግሥት አልጀዚራን “የሃማስን ፕሮፖጋንዳ ያዛምታል” እንዲሁም “የአገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት እየጎዳ ነው” በሚል መዝጋቱ ይታወሳል።

አልጀዚራ ውንጀላውን ውድቅ በማድረግ እገዳው የሰብዓዊ መብቶችን የሚጻረር ወንጀል ነው ሲል አውግዞታል።

በጋዜጠኝነት ላይ የሚሰሩ ተቆርቋሪ ድርጅቶችም የእስራኤልን እርምጃ አውግዘውታል።

አልጀዚራ እስራኤል በኃይል ተቆጣጥራው በምትገኘው ዌስት ባንክ እና ጋዛ ሰርጥ ስራውን ቀጥሏል። ይሄኛው ዙር ጦርነት ከተጀመረ በኋላ እስራኤል ማንኛውም የውጭ ጋዜጠኞች እንዳይገቡ ከልክላለች።