ስምምነቱን ሊያደናቅፉ የሚችሉትን ጉዳዮች እንዴት ማስወገድ ይቻላል?

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሁለተኛ ዓመቱን ሊደፍን ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች በዘላቂነት ግጭት ለማቆም ተስማምተዋል።

ከዚህ ስምምነት በኋላ ሁለቱም ወገኖች የፈረሙበት ዝርዝር ያዘለ ሰነድ ተሰራጭቷል።

ይህ ሰነድ በሁለቱም ወገኖች በኦፊሴላዊ መንገድ ተፈርሞ የወጣ መሆኑን ኦሲሺዬትድ ፕሬስ የተሰኘው የዜና ወኪል አረጋግጧል።

ይህ ዝርዝር ሰነድ ስለዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነት፣ ስለ ትጥቅ መፍታት እና ሌሎች ጉዳዮችን የሚዳስስ ነው።

ምንም እንኳ የሰላም ስምምነቱ ገና ጅማሬው ላይ ቢሆንም አንዳንድ አንገብጋቢ የሚባሉ ሐሳቦች አልተዳሰሱም የሚሉ ድምፆች ከአሁኑ መሰማት ጀምረዋል።

የኤርትራ ሠራዊት ጉዳይ እንዴት ይሆናል? ትጥቅ የሚፈታው እንዴት ነው? አወዛጋቢው የምዕራብ ትግራይ ጉዳይስ? ፍትሕ እንዲሰፍንስ እንዴት ማድረግ ይቻላል? የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።

የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ “ይህ መጀመሪያው እንጂ መጨረሻ አይደለም” በማለት ስለሂደቱ መጀመር በፊርማው ሥነ ሥርዓት ወቅት ተናግረዋል።

ብዙዎች በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ስምምነት ከሁሉም በላይ የሆነውን ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እና የሰብአዊ እርዳታ ያለገደብ እንዲቀርብ በር ከፍቷል።

ስምምነቱ፤ የህወሓት ኃይሎች “ከቀላል ጦር መሣሪያዎች” ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ ትጥቃቸውን ይፈታሉ ይላል።

የኢትዮጵያ ፌደራል የፀጥታ ኃይሎች “በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም የፌደራሉን ተቋማትና አየር ማረፊያዎችን እንዲሁም አውራ ጎዳናዎችን ጨምሮ ዋነኛ መሠረተ ልማቶችን” ሙሉ ለሙሉ እንደሚቆጣጠሩም ይጠቅሳል።

“ጦርነት ገሃነም ነው”

“እኔ ከጠበቅኩት በላይ ነው ሂደቱ የተፋጠነብኝ” ይላሉ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በተለያዩ አገራት በሠላም እና የግጭት አፈታት ዙሪያ ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ የሰሩት ዓለም አቀፉ የሕግ ባለሙያ አቶ ባይሳ ዋቅወያ።

“አንዳንድ ሰዎች ‘ቀኑ ተራዘመ፤ እየከሸፈ ነው’ ሲሉ እኔ ከልምድ አንጻር እንዲያውም ገና ንግግር ላይ ናቸው ድርድር ደረጃም አልደረሱም እያልኩ ነበር።”

አቶ ባይሳ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን አውዳሚ የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ተፋላሚ ወገኖች ሠላማዊ መፍትሔ እንዲያበጁ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲመክሩ እና ተሞክሯቸውን ሲያካፍሉ ነበር።

መኖሪያቸውን ኔዘርላንድስ ያደረጉት የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኙ አደም ካሴም (ዶ/ር) እንዲሁ በተመሳሳይ በተደረሰው ስምምነት የተሰማቸውን ደስታ ይገልጻሉ።

“በዚህ ፍጥነት ከስምምነት ይደረሳል የሚል እምነት አልነበረኝም፤ በጣም ደስ ብሎኛል።”

በተደጋጋሚ መልካም ዕድሎች እንዳመለጡ በማስታወስም “በጦርነቱ ለተጎሳቀለው በተለይ ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ይመስለኛል” ይላሉ ተንታኙ።

አክለውም ለዚህ የሰላም ሂደት መሳካት ከፍተኛ ድርሻ ለህወሓት ይሰጣ “በእኔ እምነት የህወሓት መሪዎች ትልቅ እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ሰላምን በመምረጥ የወሰዱት ቁርጠኝነት [concessions] ለሰላሙ ከፍተኛ አሰተዋጸኦ እንዲኖራቸው አድርጓል።”

የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ አቶ ባዑእሳም በተመሳሳይ የሰላም ስምምነቱ ለትግራይ ክልል ነዋሪዎች እፎይታ እንደሆነ ይገልጻሉ።

“በትግራይ ሰማይ ሥር ጥይት ሳይተኮስ ሲያድር፣ ሕጻናት፣ አዛውንቶች፣ እናቶች እና ወጣት ሴቶች በሠላም ነግቶላቸው ንጹህ አየር ሲተነፍሱ መስማት ደስ ይላል።”

“ጦርነት ገሃነም ነው” የሚሉት አቶ ባይሳ፣ የጦርነትን አስከፊነት በደንብ መረዳት የሚቻለው ከርቀት ከሚሰማው ይልቅ በተጨማጭ በቦታው ሲኮን እንደሆነ ይገልጣሉ።

የስምምነቱ እንቅፋቶች

የተፈረመበትን የስምምነት ሰነድ እንዳነበቡት ለቢቢሲ የሚናገሩት አቶ ባይሳ፣ ስምምነቱ የሚወደስ ሆኖ አፈፃፀሙ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ።

ጉምቱው የግጭት አፈታት ባለልምድ የአፈጻጸም ችግር የሚመጣው ከሎጂስቲክስ አቅርቦት እና ከፍላጎት አንፃር ነው ሲሉ ያክልሉ።

“ሕዝቡ ደም የተቃባ በመሆኑ በተገኘው መልካም ነገር ላይ በመሥራት እያከሙ መሄድ ያሻል” የሚሉት አቶ ባይሳ፣ ቀድሞ መሆን ያለበት ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ማድረግ እንደሚያስፈልግና መቀላጠፍ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሚና ቀላል እንዳልሆነም ያስረዳሉ።

የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኙ አደም ካሴም (ዶ/ር) እንዲሁ ስምምነቱን ማስፈፀም “ቀላል እንዳልሆነ እረዳለሁ” ይላሉ።

ነገር ግን ህወሓት የገባውን ቃል የሚያከብር ከሆን ትግራይ ውስጥ ካለው ተቀባይነት አንፃር ሕዝቡን ለማሳመን ብቃት አለው ብለው ያምናሉ።

በተጨማሪም “የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራዊያንን አሳምኖ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ፤ ድንበር ተሻግረው የሚወጡበት መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል።”

ስምምነቱ ላይ የኤርትራ መንግሥት ስም አለመጠቀሱ “የሚገርም አይደለም” የሚሉት አደም፣ በተዘዋዋሪ ኤርትራን የሚመለከቱ ጉዳዮች እንዳሉ ይጠቁማሉ።

የህወሓት ኃይሎች በስምምነቱ መሠረት ትጥቅ እንደሚፈቱ የሚጠብቁት ተንታኙ፣ በተለይ ከባድ መሣሪያቸውን እንደሚያስረክቡ ነገር ግን ሕግ አስከባሪዎች ታጥቀው እንደሚቆዩ ይገምታሉ።

የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ሳይወጡ ትጥቅ መፍታት የሚለው ሐሳብ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ግን ይናገራሉ።

የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች አየር ማረፊያዎችንና ትልልቅ የሚባሉ ሌሎች የፌዴራል ተቋማትን ብቻ ይጠብቃሉ ወይስ የፖሊስ ሥራ ላይ ይሰማራሉ የሚለው በሂደት የሚታይ ነገር ነው ይላሉ።

አደም አክለውም “ስምምነቱ ዝርዝር ነገሮች የያዘ ቢሆንም፤ ያልተጠቀሱ ነገሮች ይበዛሉ” የሚል እምነት አላቸው።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያውያን አለመግባባቶቻቸውን በጥይት ሳይሆን በሰላም የሚፈቱበትን ልምድ ማዳበር እንዳለባቸው የሚመክሩት የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው አቶ ባይሳ፤ ስምምነቱ ያልተዋጠላቸው ሰዎች እንቅፋት እንዳይሆኑ ስጋት አላቸው።

“ከጅማሮው ጦርነት ውስጥ መግባት አልነበረብንም፤ ጦርነቱ ውስጥ ከተገባ በኋላ ደግሞ በሰላም ማለቁን ካወቅን ለወደፊትም ለሚያጋጥሙንን አለመግባባቶች በውይይት መፍታት እየተለማመድን መሄድ አለብን።

“የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አክቲቪስቶች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ጋዜጠኞችም ጭምር እባካችሁ በሰላም ችግሮቻችን መፍታት ላይ እናተኩር. . . ” ሲሉ አቶ ባይሳ ይማፀናሉ።

በስምምነቱ ንዑስ አንቀጽ 10 ላይ እንደተቀመጠው ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በመመለስ ችግሮቻችንን ከጦርነት ይልቅ በሰላማዊ መንገድ መፍታት አስፈላጊ ነው ሲሉ ያስረግጣሉ።

“እርግጥ ነው ሕገ-መንግሥቱ ሲዘጋጅ ሕዝቦችን በሚገባ አላሳተፍም። ስለዚህ ሕገ-መንግሥቱ የሁሉንም ፍላጎቶች ያሟላል ወይ? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፤ አሁን ላሉብን ችግሮቻችን ግን ሕገ-መንግሥት አለን። ሁሉም የሚስማሙበት ሕገ-መንግሥት እስኪዘጋጅ ድረስ ያለብንን አለመግባባት በሕጉ መሠረት መፍታት አለብን።”

የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኙ አደም (ዶ/ር)፤ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ተግዳሮቶች ሊኖሩ ቢችሉም ወደ ጦርነት ተመልሶ ይገባል ብለው አያስቡም።

አስተዳደሩን በተመለከተ እንዲሁም የይዞታ ይገባኛል ውዝግቦች ፍትሕን በተለመከተ ለፖለቲካዊ ንግግር መተው መልካም መሆኑን ያምናሉ ተንታኙ።

“ዋናው ነገር የሚሆነው ይህንን ስምምነት የወሰኑት ተወካዮች ተመልሰው ሕዝባቸውን የማሳመን እና የማግባባት፤ የዚህ ጉዳይ ዓላማን ማሳወቅ፣ ‘ኮምፕሮማይዝ’ [ማቻቻል] የሚደረግም ካለ ለምን እንደዚያ እንደሆነ ግንዛቤ መፍጠር ሊቀድም ይገባል” ይላሉ።

የተለያዩ የመብት ተቆርቋሪ ተቋማት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተካሄደባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊዎች ከባድ የመብት ጥሰትና ወንጀሎችን መፈጻማቸውን የሚያመለክቱ ዘገባዎችን ማውጣታቸው የታወሳል።

“ይነስም ይብዛ ሁሉም ወገኖች ጥሰቶች ፈፅመዋል” የሚሉት የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኙ አደምም (ዶ/ር) በስምምነቱ ፍትሕ ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም ይላሉ።

አክለው በዋናነት በትግራይ እንዲሁም በአማራ እና በአፋር ክልሎች ሰፊ የመልሶ ግንባታ ሥራ እንደሚያስፈልግ አጠራጣሪ እንዳልሆነ ያለመልከታሉ።

ልክ እንደ ዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው አቶ ባይሳ ዋቅወያ ሁሉ፣ አደም ካሴም (ዶ/ር) ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመልሶ ግንባታው ካልተሳተፈ ሁኔታዎች ሊከብዱ ይችላሉ ብለው ያስባሉ።

“እንደ ሕዝብ፤ ኤርትራ፣ አማራ እና ትግራይ በጦርነት ከስረናል ከሚል መንፈስ፤ ከጥላቻ ንግግር ተቆጥበው፤ ይህ ሰላም እንዲሳካ ዕድል እንስጥ” በማለት ለተጀመረው የሰላም መንገድ ስኬት የሁሉም ሚና ወሳኝ ነው ይላሉ።