የተባበሩት መንግሥታትበሁከት በምትናጠው ሄይቲ አነስተኛ የጦር መሳሪያ ሽያጭን አገደ

በተደራጁ ወሮበሎች ጥቃት በከፍተኛ ሁከት እና ግጭት በምትናጠው ሄይቲ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አነስተኛ የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ ክልከላን በሙሉ ድምፅ ወሰነ።

ውሳኔው የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገራት መንግሥታዊ ላልሆኑ አካላት ቀላል የጦር መሳያዎችን እና ጥይቶችን መሸጥ እንዲከለክሉ ይጠይቃል።

ነገር ግን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ላይ ሙሉ እገዳ በአገሪቷ ላይ እንዲጣል የቀረበው ሃሳብ በቻይና ውድቅ ተደርጓል።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመዲናዋ ፖርት ኦ ፕሪንስ ብቻ 89 ሰዎች ተገድለዋል።

የረድዔት ድርጅቶች በአሁኑ ጊዜ በሄይቲ ያሉ አካባቢዎችን ለመድረስ አደገኛ ነው ይላሉ።

ቅዳሜ ሐምሌ 09/ 2014 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው ከሐምሌ 1 አስከ 5 ባለው ጊዜ ውስጥ በወሮበሎች ቡድን ጥቃት 234 ሰዎች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል ብሏል።

"አብዛኞቹ ሟቾች ወይም ተጎጂዎች በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ ተሳታፊ ባይሆኑም የጥቃቱ ኢላማ ሆነዋል” በማለት የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ጄረሚ ሎሬንስ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለጽህፈት ቤታቸውም የወሲባዊ ጥቃት ሪፖርቶች እንደደረሳቸውም አክለዋል።

በሜክሲኮና በአሜሪካ አማካኝነት የቀረበው የተባበሩት መንግሥታት የጦር መሳሪያ ሽያጭን የሚከለክለው የውሳኔ ሃሳብ ባለፈው አርብ ተቀባይነት አግኝቷል።

ውሳኔው በሄይቲ የወሮበሎች ቡድን መሪዎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦች ላይ የጉዞና የንብረት እገዳ ማዕቀብ እንደሚጣል ያሳያል።

እንዲሁም በሄይቲ ተቀማጭነቱን ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት ልዩ የፖለቲካ ተልዕኮ ተቋምን የሚቆይበትን ጊዜ ለአንድ ዓመት ያራዝመዋል።

ከዓመት በፊት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆቬኔል ሞይስ በቅጥረኞች ከተገደሉ በኋላ በሄይቲ የወሮበሎች ጥቃት በሰፊው ተንሰራፍቷል።

ከቅርብ ቀናት ወዲህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የቤንዚን አቅርቦቱ ወደነበረበት እንዲመለስ አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ አለበት ሲሉ ጎማዎችን እያቃጠሉ እንዲሁም መንገዶችን እየዘጉ ነው።

የሄይቲ ዋና የነዳጅ ማከማቻ ባለፈው ሳምንት የነበረውን ከባድ የወሮበሎች ጥቃት ተከትሎ ሥራውን ለማቆም ተገዷል።

የቫርሬክስ የነዳጅ ማከማቻ በሁለት ተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል ፍልሚያ በሚደረጉባት በሲቴ ሶሌይል ከተማ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ሥራውን ማቆሙ በአገሪቱ የነዳጅ እጥረት አስከትሏል።

በሄይቲ ያለው ድህነት እንዲሁም ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በርካታ ዜጎች ወደ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ እና አሜሪካ እየተሰደዱ ነው።