ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢንተር ሚላን ከ13 ዓመታት በኋላ ለቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ደረሰ
ማክሰኞ ምሽት የሚላን ከተማ ደርቢን በላውታሮ ማርቲኔዝ ጎል ታግዞ የረታው ኢንተር ሚላን ከ13 ዓመታት በኋላ ለቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ደርሷል።
በመጀመሪያው ዙር ፍልሚያ በሳንሴሮ ስታድየም ኤሲ ሚላንን 2 ለምንም ያሸነፈው ኢንተር ሚላን በሁለተኛው ዙር ፍልሚያ አንድ ጎል በማከል በድምር 3-0 ወደ ፍፃሜ ተሻግሯል።
ኢንተር ሚላን በተወዳጁ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ሰኔ 3 ከሪያል ማድሪድ አሊያም ከሲቲ ለዋንጫ ይጫወታል።
ምንም እንኳን ኤሲ ሚላን በማክሸኞ ምሽቱ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ተፅዕኖ ለማሳደር ቢሞክሩም የኢንተርን አጥር መጣስ ተስኗቸዋል።
ቲዮ ኧርናንዴዝ ከርቀት በግራ እግሩ ወደ ጎል የነረታት ኳስ በኢንተሩ በረኛ አንድሬ ኦናና የከሸፈችው የብራሂም ዲያዝ ሙከራ ተጠቃሽ ነበሩ።
በመጀመሪያው ዙር ግጥሚያ ኢንተር ሚላን በመጀመሪያዎቹ 11 ደቂቃዎች 2 ጎል በማስቆጠር የበላይነቱን ተቀዳጅቶ ነበር።
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ግጥሚያ በጉዳት ምክንያት ያልተሰለፈው ራፋኤል ሊያው ትላንት ምሽት ጎል ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ መና ሆኖበታል።
ብዙም ማራኪ ባልነበረው ሁለተኛው 45 ደቂቃ ጨዋታ ኢንተር ሚላን ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ሲሞክር ተስተውሏል።
አርጀንቲናዊው ላውታሮ ማርቲኔዝ ጨዋታው 16 ደቂቃዎች ሲቀሩት በግራ እግሩ ወደ ጎል የሰደዳት ኳስ መረብ ስትነከ የሳን ሲሮ ስታደየም በጩኸት ደምቋል።
ኢንተር ሚላን ከ13 ዓመታት በኋላ ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ማለፉን ተከትሎ ደጋፊዎች ላንቃቸው እስኪላቀቅ ሲፈነጥዙ አምሽተዋል።
ሁለት ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳት የቻሉት ኢንተር ሚላኖች ታሪካዊ ተቀናቃኛቸውን ጥለው ወደ ፍፃሜ የሚወሰደውን ቲኬት ቆርጠዋል።
ኢንተር ሚላን እና ኤሲ ሚላን ሳን ሲሮ ስታድየምን በጋራ ነው የሚጠቀሙበት።
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ግጥሚያ ኤሲ ሚላን ባለሜዳ ሆኖ በመቅረቡ የሚላን ደጋፊዎች ልቆ ታይቷል።
በትላንትናው ፍልሚያ ደግሞ ኢንተር ባለሜዳ በመሆኑ ሳን ሲሮ ሰማያዊና ጥቁር መስመር ባለው ማሊያ ደምቆ አምሽቷል።
ምንም እንኳ ኢንተር ወደ ፍፃሜው የሚያመራው ብዙ ግምት ሳይሰጠው ቢሆንም በዘንድሮው ቻምፒየንስ ሊግ ባለፉት 8 ጨዋታዎች አንድም ጎል አልተቆጠረበትም።
ዛሬ ምሽት የግማሽ ፍፃሜ ሁለተኛ ዙር ጨዋታቸውን ከሚያደርጉት ማንቸስተር ሲቲና ሪያል ማድሪድ መካከል አንዱ ሰኔ 3 ከኢንተር የፍፃሜ ጨዋታ ያደርጋል።
ባለፈው ሳምንት ማንቸስተር ሲቲ ወደ ስፔን ተጉዞ ከቻምፒዮንስ ሊግ ኃያላኑ ማድሪድ ጋር የነበረውን ግጥሚያ 1 አቻ መውጣቱ ይታወሳል።
ፕሪሚዬር ሊግ፣ ቻምፒዮንስ ሊግና ኤፍ ኤ ዋንጫን ለማንሳት እየሞከሩ ያለው የፔው ጉዋርዲዮላ ቡድን ዛሬ ምሽት በሜዳው ማድሪድ አሸንፎ ለማለፍ ይጥራል።
የፍፃሜው ጨዋታ ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 በቱርክ፤ ኢስታንቡል ምሽት 4፡00 ይካሄዳል።