ከ10 ደቡብ አፍሪካዊያን ሕፃናት ስምንቱ ማንበብ እንደሚከብዳቸው ጥናት ገለጠ

ከ10 ደቡብ አፍሪካዊያን ሕፃናት ስምንቱ ዕድሜያቸው 10 እስኪሞላው ድረስ ማንበብ እንደሚከብዳቸው አንድ ጥናት ገልጧል።

ፕሮግረስ ኢንተርናሽናል ሪዲንግ ሊትራሲ የተሰኘው ጥናት ደቡብ አፍሪካን ከ57 አገራት የመጨረሻዋ አድርጓታል።

ተቋሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሠራው ጥናት የ400 ሺህ ሕፃናትን የማንበብ አቅም ፈትኗል።

በፈረንጆቹ 2016 ማንበብ የማይችሉ ደቡብ አፍሪካዊያን ሕፃናት 78 በመቶ ነበሩ። አሁን ይህ ቁጥር ወደ 81 በመቶ ከፍ ብሏል።

የአገሪቱ ትምህርት ሚኒስትር ቁጥሩ ያሻቀበው በኮቪድ-19 ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ነው ብለዋል።

ውጤቱ “በሚያሳፍር ሁኔታ ዝቅ ያለ ነው” ያሉት አንጂ ሞትሼጋ የአገራቸው የትምህርት ሥርዓት በድኅነት፣ ኢ-ፍትሐዊነት እና መሠረት ልማት መጓደል ምክንያት እየተጎዳ እንዳለ ገልጠዋል።

በአብዛኛዎቹ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች “ተማሪዎች ማንበብ እንዲችሉ ትምህርት የሚሰጣቸው በቃል ሲሆን ይህ ደግሞ የማንበብ አቅማቸውን አያጎለብተውም” ብለዋል ሚኒስትሯ።

ጥናቱ እንደሚጠቁመው 81 በመቶ ደቡብ አፍሪካዊያን ሕፃናት በሃገሪቱ 11 ኦፊሴላዊ ቋንቋዎች የተፃፉ ፅሑፎችን አንበበው መረዳት አይችሉም።

ከአፍሪካ አገራት ከ9 እስከ 10 ያሉ ሕፃናትን ባሳተፈ በጥናት የተካተቱት ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅና ሞሮኮ ብቻ ናቸው።

በየአምስት ዓመቱ ትምህርት ሲዘጋ የሚደረገውን ጥናት ተከትሎ አገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የትምህርት ደረጃ ይፋ ይሆናል።

ሲንጋፖር 587 ነጥብ በማምጣት በጥናት ከተሳተፉ አገራት ቁንጮ ሆና ስትገኝ 288 ነጥብ ያላት ደቡብ አፍሪካ መጨረሻ ሆናለች።

ግብፅ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ከፍ ብላ በ378 ነጥብ ከመጨረሻ ሁለተኛ ወጥታለች። ውጤቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ500 የሚያዝ ነው።

ጥናቱ አክሎ እንደጠቆመው በጠቅላላው ሴት ሕፃናት ከወንድ እኩዮቻቸው በተሻለ በፍጥነት የማንበብ ክህሎት ያዳብራሉ።

ነገር ግን በቅርቡ የተሠራው ጥናት እንደሚያሳየው የሴቶች ቁጥር ከወንዶች ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአፓርታይድ ዘመን በነጭና ጥቁር ተማሪዎች መካከል በነበረው ኢ-ፍትሐዊነት ምክንያት ሕፃናት ተማሪዎች የማንበብ አቅማቸው ደካማ ሆኗል።

መንግሥት ከፍተኛ በጀት ከሚበጅትላቸው መስኮች መካከል አንድ ትምህርት ሲሆን ጥናቱ ይህን ይፋ ማድረጉ አገሪቱን አስከፍቷል።

በትምህርት ቤቶች ያለው መሠረት ልማት ያልበለፀገ መሆኑና የማንበቢያ መሣሪያዎች አለመሟላታቸው ለውጤቱ አስተዋፅኦ አድርጓል።