ቻይናዊው የቼዝ ሻምፒዮን ባልተገባ ባህሪይው አሸናፊነቱ ተነጠቀ

ዢያንግኪ በተሰኘው የቻይና ቼዝ ውድድር ሻምፒዮን የሆነው ግለሰብ ያልተገባ ባህርይ አሳይቷል በሚል አሸናፊነቱ ተነጠቀ።

ያን ቼንግሎንግ በአንድ ሆቴል ውስጥ ጠጥቶ በገላ መታጠቢያ ገንዳ ተጸዳድቷል ተብሏል።

የ48 ዓመቱ ግለብ የአሸናፊነት ስፍራውንም ተነጥቆ ለአንድ ዓመት እንዳይጫወት ታግዷል።

በተጨማሪም ዶቃ መሳይ የመገናኛ መሳሪያዎችን በሰውነት አካሉ ውስጥ በመደበቅ አጭበርብሯል የሚሉ ውንጀላዎች ቢቀርብበትም የቻይና ዢያንግኪ ማህበር እነዚህን ክሶች ማረጋገጥ አይቻልም ብሏል።

ከምዕተ ዓመታት በላይ እድሜ ያለው ዢያንግኪየተሰኘው የቼዝ ውድድር በመላው እስያ ታዋቂ ነው።

እንደ ማህበሩ ከሆነ ያን ባለፈው ሳምንት በቻይና ደሴት ሃይናን በተካሄደው ብሔራዊ ውድድር የዢያንግኪ ንጉስ የሚል ማዕረግ ማግኘቱን ተከትሎም በሆቴሉ ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር እየጠጣ ነበር።

በመቀጠልም በክፍሉ በሚገኘው የመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ በመጸዳዳትም “በሆቴል ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል እንዲሁም የህዝብን ጸጥታ እና መልካም ስነ ምግባርን ጥሷል” ሲልም ማህበሩ ገልጿል።

ግለሰቡ ገመድ አልባ ዶቃ መሳይ የመገናኛ መሳሪያዎችን በሰውነት አካሉ ውስጥ ደብቆ ከኮምፒውተሩ ጋር በማገናኘት አጭበርብሯል የሚሉ ውንጀላዎችም ላይ ማህበሩ ምላሽ ሰጥቷል።

“ስለ ሁኔታው ካለን ግንዛቤ በመነሳት በአሁኑ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጨ እንዳለው በሰውነቱ አካሉ ውስጥ ዶቃ መሳይ የመገናኛ መሳሪያዎችን ደብቆ አጭበርብሯል መባሉን ማረጋገጥ አይቻልም” ብሏል።

ሆኖም ላልተገባ ባህርይው የአሸናፊነት ማዕረጉን ተነጥቆ ለአንድ ዓመት እንዳይጫወትም እግድ ተጥሎበታል።

ማህበሩ ያን ያጣውን የሽልማት ገንዘብ መጠን ይፋ ባያደርግም የዢያንግኪ ውድድሮች በአብዛኛውን ጊዜ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር እንደሚያሸንፉ የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያሳያል።