ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፕሬዝዳንት ባይደን መኖሪያ ቤት ተጨማሪ ምስጢራዊ የመንግሥት ሰነዶች ተገኙ
የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ዴልዌር በሚገኘው የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መኖሪያ ቤት ላይ ባደረገው 13 ሰዓታትን የፈጀ ፍተሻ ስድስት ተጨማሪ ምስጢራዊ ሰነዶችን ማግኘቱን የፕሬዝዳንቱ ጠበቃ ተናግረዋል።
ሌሎች ሰነዶች ደግሞ ጆ ባይደን የባራክ ኦባማ ምክትል እና ከዚም ቀደም ብሎ የምክር ቤት አባል እያሉ ይኖሩበት በነበረው እና ዊልሚንግተን በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ባለፈው አርብ ተገኝቶ ነበር።
የፕሬዝዳንቱ ጠበቃ ቦብ ባዋ በግል በእጅ የተጻፉ ማስታወሻዎች እና መሰል ነገሮች በፖሊስ እንደተወሰዱ ጠቁመዋል።
ፍተሻው በሚካሄድበት ወቅት ፕሬዝዳንት ባይደንም ይሁኑ ባለቤታቸው አልተገኙም ነበረ።
ፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤያቸው በፍትህ መሥሪያ ቤት እንዲፈተሽ ፍቃድ መስጣታቸውንም ጠበቃቸው ተናግረዋል።
በዚህ ወር መግቢያ ላይ ባይደን በዋሽንግተን ባቋቋሙትና ፔን ባይደን በተሰኘው የምሁራን ሃሳብ ማፍለቂያ ማዕከል ውስጥ የመጀመሪያው ምስጢራዊ ሰነድ መገኘቱን ጠበቃቸው ገልጸው ነበር።
ሁለተኛው ሰነድ በፈረንጆቹ ታኅሣሥ 20/2022 ዊልሚንግተን በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የተገኘ ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ ከ10 ቀናት በፊት በተመሳሳይ ቤት መጋዘን ውስጥ ተጨማሪ ምስጢራዊ ሰነድ ተገኝቷል።
ፕሬዝዳንቱ ሰነዶቹን ለምን እንደያዟቸው ባይታወቅም ሰነዶቹ ከተገኙ በኋላ ግን ወዲያውኑ ለብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ለፍትህ መሥሪያ ቤት ማስተላለፋቸውን ባይደን ገልጸዋል።
በአሜሪካ የፕሬዝደንቶችን ሰነድ በሚመለከት በወጣው አዋጅ መሠረት በአስተዳደር ላይ የቆየ መንግሥት የሥልጣን ጊዜው ሲቋጭ ሰነዶች በምስጢር ወደ ሚቀመጡበት ብሔራዊ ቤተ መዛግበት እንዲተላለፉ ይጠበቃል።
እነዚህ በፕሬዝዳንት ባይደን መኖሪያ እና የሥራ ቦታዎች የተገኙት ጥንቃቄ የሚፈልጉ ሰነዶች እንዴት ተይዘው እንደነበር የሚመረምር ልዩ አካልም ተቋቁሟል።
ረጅም ሰዓታት ከፈጀው ፍለጋ በኋላ በፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤት ምስጢራዊ ሰነዶች መገኘታቸው እንደ አውሮፓውያኑ በ2024 ለሁተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት “እወዳደራለሁ” ወይም “አልወዳደርም” የሚለውን ለመግለጽ እየተዘጋጁ ላሉት ባይደን ራስምታት ሆኖባቸዋል ተብሏል።
ባይደን እና ባለቤታቸው ጂል ቅዳሜ እና እሁድን በባሕር ዳርቻዋ ዴልዌር ውስጥ የሚያሳልፉ ሲሆን፣ በዚያው ከተማ ሌላ መኖሪያ ቤት አላቸው።
ይህኛው መኖሪያ ቤያቸው ላይ ፍተሻ ተደርጎ ምንም አይነት ምስጢራዊ ሰነድ አለመገኘቱን ጠበቃቸውን ጠቅሶ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
በአገሪቱ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ከተካሄደ ከሁለት ወራት በኋላ በባይደን ቤት ምስጢራዊ ሰነዶች መገኘታቸው በፕሬዝዳንቱ ላይ የግልጽነት ጥያቄን አስነስቷል።
የባይደን ቡድን ፕሬዝዳንቱ ምርመራው ላይ ከፍትህ መሥሪያ ቤቱ ጋር መሉ በሙሉ መተባበራቸውን ገልጿል።
ባይደን ጉዳዩን ‘ቀለል’ አድርገው የተመለከቱት ሲሆን፣ ሰነዶቹን ይፋ ስላላወጧቸው መገኘታቸው “አይጸጽተኝም” ብለዋል።
በፕሬዝዳንት ባይደን መኖሪያ ቤት ምስጢራዊ ሰነዶች የመገኘቱ ዜና በሚሰማበት ወቅት፣ ዶንልድ ትራምፕ ላይም ተመሳሳይ ክስተት ማጋጠሙ አይዘነጋም።
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፍሎሪዳ በሚገኘው ኩባንያቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ምስጢራዊ ሰነዶች ተገኝቶባቸዋል የተባል ሲሆን፣ ለቀረበላቸው ጥያቄም በጎ ምልሽ አልሰጡም ተብሏል።
ትራምፕ እና ጠበቃቸው ሰነዶቹን ለመስጠት አሻፈረኝ ቢሉም፣ ኤፍቢአይ ባለፈው ነሐሴ ፍሎሪዳ የሚኘውን መኖሪያ ቤታቸውን በርብሯል።
ትራምፕ በቀጣይ ምርጫ እንዳይሳተፉ ለማደናቀፍ የተሸረበ ሴራ ነው በማለት ኤፍቢአይ በተመሳሳይ ጉዳይ ለፕሬዝዳንት ባይደን ውለታ እየሰራ ነው ማለታቸውም ተዘግቧል።