አሜሪካ በሶማሊያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ‘30 የአልሻባብ ታጣቂዎችን’ ገደልኩ አለች

የሶማሊያ መንግሥት ሠራዊት በአልሻባብ ላይ እያካሄደ ላለው ዘመቻ ድጋፍ የአሜሪካ አየር ኃይል በፈጸመው ጥቃት 30 የሚደርሱ የታጣቂው ቡድን አባላት መገደላቸውን የአሜሪካ ሠራዊት አስታወቀ።

የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው ከሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በስተሰሜን ምሥራቅ 260 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ጋልካድ ከተባለች ከተማ አቅራቢያ ነው።

ባለፉት ጥቂት ቀናት የሶማሊያ መንግሥት ሠራዊት እና የአልሻባብ ታጣቂዎች ከተማዋን ለመቆጣጠር ሲዋጉ ቆይተዋል።

አሜሪካ አርብ ዕለት የፈጸመችው የአየር ጥቃት እየተካሄደ በነበረው ውጊያ ወቅት የሶማሊያ መንግሥት ሠራዊት አባላት ከ100 በላይ በሚሆኑ ታጣቂዎች ጥቃት በተከፈተባቸው ጊዜ መሆኑን በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ ገልጿል።

ከጥቃቱ ቀደም ብሎ እስላማዊ ታጣቂዎቹ ጋልካድ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ወታደራዊ ሰፈር ላይ ጥቃት ፈጽመው ሰባት የመንግሥት ወታደሮችን ገድለዋል። የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እናዳለው ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ በርካታ የአልሻባብ ታጣቂዎች ተገድለዋል።

አልሻባብ በሾማሊያ ውስጥ ጽንፈኛ እስላማዊ መንግሥት ለማቋቋም አላማ ይዞ ከ15 ዓመት በፊት ጀምሮ በእርስ በርስ ጦርነት የተዳከመውን የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግሥት ለመጣል ሲዋጋ ቆይቷል።

ቡድኑ ከዋና ከተማዋ የሞቃዲሾ አካባቢዎች በኃይል ተገፍቶ የወጣ ቢሆንም ወታደራዊ እና የሰላማዊ ሰዎች አካባቢዎችን ኢላማ በማድረግ ከባድ ጉዳትን እያደረሱ ያሉ ጥቃቶችን እየፈጸመ ይገኛል።

የሶማሊያ መንግሥት እና የጎሳ ሚሊሻዎች ባለፉት ወራት በታጣቂ ቡድኑ ላይ በጥምረት እያካሄዱት ባለው ዘመቻ ምክንያት ቡድኑን ከበርካታ ቦታዎች እያስለቀቁት ይገኛሉ።

ባለፈው ሰኞ የሶማሊያ መንግሥት እንዳስታወቀው ሠራዊቱ እና የአካባቢ ሚሊሻዎች ሃራርድሄር የተባለች የወደብ ከተማን ለመቆጣጠር ችለዋል። ከተማዋ ከ2010 የአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጀምሮ የአልሻባብ የተለያዩ አቅርቦቶች ቆልፍ ቦታ ሆና መቆየቷ ተነግሯል።

በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ በጋልካድ አቅራቢያ ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው ሦስት የአልሻባብ ተሽከርካሪዎች በጥቃቱ ወድመዋል።

ዕዙ ጨምሮም በአየር ጥቃቱ “በሰላማዊ ሰዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳትም ሆነ ሞት አለመከሰቱን” አመልክቷል። ነገር ግን ስለተፈጸመው የአየር ጥቃት ዝርዝር ሁኔታ ከገለልተኛ ወገን የተሰጠ ማረጋገጫ የለም።

“ትልቁን እና አደገኛውን የአልቃኢዳ አጋር የሆነውን አልሻባብን ለመደምሰስ ለሚዋጉ ኃይሎች በአፍሪካ የአሜሪካ ዕዝ የሚያስፈልጋቸውን የሥልጠና፣ የምክር እና የቁሳቁስ ድጋፍ መስጠቱን ይቀጥላል” ብሏል የአሜሪካ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ።