በሶማሊያ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት 9 የአንድ ቤተሰብ አባላት ተገደሉ

በሶማሊያ በማዕከላዊ ሒራን አውራጃ ረቡዕ ዕለት በተፈጸመ የሽብር ጥቃት ዘጠኝ የአንድ ቤተሰብ አባላት ተገደሉ።

የአውራጃው ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ለሮይተርስ እንዳረጋገጡት ከእነዚህ የአንድ ቤተሰብ የጥቃት ሰለባዎች በጠቸማሪ ሌሎች 26 ሰዎችም በጥቃቱ ተገድለዋል።

የአልቃኢዳ ክንፍ ነኝ የሚለው አልሸባብ ለጥቃቱ እኔ ኃላፊነት እወስዳለሁ ብሏል።

የመሐስ ከተማ አካባቢው ኮሚሽነር ጥቃቱ እርሱን እና ሌሎች የፓርላማ አባላትን ለመግደል ያለመ ነበር ብለዋል።

ሁለተኛው ጥቃት ዒላማ ያደረገው ደግሞ አንድ ገበያ ማዕከልን ነበር ብለዋል የመሐስ ከተማ ከንቲባ ሙሚን ሙሐመድ ሐላኔ ለቢቢሲ።

እነዚህ ጥቃቶች ፍንዳታቸው ከፍተኛ ስለነበረ ከጥቃቶቹ ስፍራ ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችን ሳይቀር አንቀጥቅጠዋል፤ በተጨማሪም የፍንዳታው ፍንጣሪዎችም በርካታ ሰዎችን ማቁሰላቸውን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

አዳን ሐሰን የተባለ የዐይን እማኝ “ይህ እጅግ የከፋ ጥቃት ነበር” ሲል ለፈረንሳይ ዜና አገለግሎት ኤኤፍፒ ተናግሯል።

አልሸባብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእጁ የነበሩ ግዛቶችን በመንግሥት ኃይሎች እየተነጠቀ መምጣቱ አስቆጥቶታል።

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ከነሐሴ ወር ወዲህ የለየለት ጦርነት በአልሸባብ ላይ ከከፈቱ ወዲህ አልሸባብ ገዢ መሬቶችን ቢያጣም በሽብር ጥቃቱ ግን ገፍቶበታል።

በባለሥልጣናት ይዘወተራል በሚባለው በሞቃዲሾ የሚገኝ ሆቴል ላይ በተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት 20 ሰዎች የተገደሉት ከጥቂት ወራት በፊት ነበር።

ከዚህ ጥቃት ሁለት ወራት በኋላ ደግሞ ሰው በሚበዛበት የሞቃዲሾ ጎዳና አልሸባብ በፈጸማቸው መንትያ ጥቃቶች 100 ሰዎችን ገድሏል።

ፕሬዝዳንት መሐሙድ በአልሸባብ ላይ መጠነ ሰፊ ዘመቻን ከፍተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት እና የአሜሪካ እገዛዎች አልሸባብን ጨርሶ ከሶማሊያ ምድር እና ከቀጠናው ለማጥፋት ለሚውለው ጥረት እየዋሉ ናቸው።

ከዚህ ሌላ በኤርትራ ምድር ለረዥም ጊዜ ወታደራዊ ሥልጠና የወሰዱ እና ወደ ሶማሊያ በቅርቡ የተመለሱ የአንደኛ ዙር ሠልጣኝ ወታደሮች በአልሸባብ ላይ በተከፈተው ጦርነት እንደሚሳተፉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።