ከእስራኤል ወደ ሩዋንዳ ተልከው የነበሩ ስደተኞች እንዴት ወደ አውሮፓ ሊገቡ ቻሉ?

ዩናይትድ ኪንግደም በቅርቡ በርካታ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ እየተሰናዳች ነው።

በአንጻሩ ቢቢሲ በደረሰው መረጃ ከዚህ ቀደም ወደ ሩዋንዳ ተሰደው የነበሩ አሁን ተመልሰው ወደ አውሮፓ እየገቡ ነው። 

በተለይም ከእስራኤል በተመሳሳይ መንገድ ወደ ሩዋንዳ ያቀኑት አሁን መኖርያቸው አውሮፓ ሆኗል። 

እንዴት ይህ ሊሆን ቻለ? 

የሦስት ኤርትራዊያንን ታሪክ እነሆ፦ 

ባሐበሎም መንገሽ የ36 ዓመት ኤርትራዊ ነው።

ከአንድ አገር ተነቅሎ ወደ ሩዋንዳ መወሰድ ምን ማለት እንደሆነ አሳምሮ ያውቃል። 

ይሁንና በሩዋንዳ የነበረው የስደት ቆይታ እንደፈራው ረዥም አልሆነም። 

ጦርነትን ሽሽት ከኤርትራ የወጣው በፈረንጆቹ 2007 ዓ/ም ነበር። መጀመርያ ወደ እስራኤል አቀና፤ በዚያም ጥገኝነት ጠየቀ። 

ከሰባት ዓመታት በኋላ በእሰራኤል የመኖርያ ፍቃዱ ተሰረዘ።

ሁለት አማራጭም ተሰጠው፤ ወይ ወደ እናት አገሩ ኤርትራ መመለስ ወይ ደግሞ 3ሺህ 500 ዶላር የኪስ ገንዘብ ተሰጥቶት በአውሮፕላን ወደ ሩዋንዳ መብረር። 

“ይህ የሁለት ክፉ ምርጫዎች ሜኑ ይመስላል” ሲል ነበር በወቅቱ ስለተሰማው ስሜት ለቢቢሲ የተናገረው።

ባሐበሎም አሁን ያለው ስዊዘርላንድ ነው። ላለፉት ሰባት ዓመታትም የኖረው በስዊዘርላንድ ነው። 

“ማንም ጤነኛ ሰው ወዶና ፈቅዶ ወደ እስር ቤት አይገባም መቼስ” የሚለው ባሐበሎም በእስራኤል ቀደም ሲል የቀረበለትን ምርጫ ይኮንናል። 

“መታሰር ባሕል እየሆነ ወደመጣባት ኤርትራ መመለስ መቼስ ምርጫ ሊሆን አይችልም”

ስለዚህ ሩዋንዳን መረጠ። 

ይሁንና ሩዋንዳ እጇን ዘርግታ እንዳልተቀበለችው ለመረዳት ባሐበሎም ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም።

ገና ዋና ከተማዋ ኪጋሊ በገባ በስንተኛው ቀን ወደ ጎረቤት ሩዋንዳ እንደሚወሰድ ተነገረው። 

ማን ይህን ውሳኔ እንደወሰነ ባሐበሎምም ሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌሎች ስደተኞች አያውቁም። 

 የሚጠረጥሩት ግን የሩዋንዳ ባለሥልጣናት እጅ እንዳለበት ነው። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ ሩዋንዳ ለስደተኞች አስተማማኝ ቦታ መሆኗ ጥያቄ ውስጥ እየገባ ነው።

በተለይም ይህ ጉዳይ ይበልጥ እያነጋገረ ያለው ዩኬ ከሩዋንዳ ጋር ስደተኞችን እንድትቀበል ስምምነት ላይ ከደረሱ ወዲህ ነው። 

ምዕራባውያን ሃገራትበተለይም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሩዋንዳ ከሰብአዊ መብት ጥበቃ ጋር በተያያዘ ያለባትን ክፍተት እያነሱ ይወቅሳሉ።

እርግጥ ነው ዩኬ ከሩዋንዳ ጋር ያደረገችው ስምምነት እስራኤል ከሩዋንዳ ጋር ካደረገችው ስምምነት ጋር መሠረታዊ ልዩነቶች አሉት። 

ለምሳሌ የእስራኤሉ ስምምነት ጉዞው በስደተኞች “በጎ ፈቃድ የሚደረግ ነው” ይላል።

የዩኬው ስምምነት ግን በግዴታ የሚፈጸም ይለዋል። 

የእስራኤል መንግሥት ከአራት ሺህ ኤርትራዊያንና ሱዳናዊያን በላይ በዚህ መንገድ ወደ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ልኳል። ይህም በፈረንጆቹ ከ2013 እስከ 2018 የሆነ ነው። 

በሐበሎም ወደ ኪጋሊ የተወሰደው በ2014 ዓ/ም ነበር። 

“ወደ ሩዋንዳ መወሰዳችን ግን ወደ አውሮፓ ከማለምና ከማማተር አላገደንም” ይላል። 

ቢቢሲ ከእስራኤል ወደ ሩዋንዳ የተመለሱ በርካታ ጥገኝነት ጠያቂዎችን አነጋግሯል። 

ወደ ሩዋንዳ ከ2014 እስከ 2016 መወሰዳቸውን የተናገሩት እነዚህ ስደተኞች ታዲያ አሁን እንደሚታሰበው በሩዋንዳ የሉም። ብዙዎቹ በዚህ ሰዓት በአውሮፓ ነው የሚገኙት።

ከነዚህ መሀል አንዳንዶቹ አሁን በዩኬ የሚኖሩ አሉ።

በሩዋንዳ ምን ገጠማቸው?

ብዙዎች እንደሚያስታውሱት መጀመርያ ኪጋሊ አየር ማረፊያ ጆን የሚባል ሰው ነበር የተቀበላቸው።

 ይህ ሰው ሰነዳቸውን ይቀበላቸዋል። ከዚያ ወደተመደበላቸው ማረፊያ ይወስዳቸዋል።

ከዚያ ግን ብዙም እንዲንቀሳቀሱ አይፈቀድላቸውም። 

በዚህ ሁኔታ ጥቂት ከቆዩ በኋላ መንቀሳቀስ ካሻቸው እያንዳንዳቸው 500 ዶላር እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ።

ይህን ተፈጻሚ ሲያደርጉ ወደ ኡጋንዳ ድንበር ይወሰዳሉ። 

ከድንበር ማዶ ደግሞ አንድ መኪና ይጠብቃቸዋል። መኪናው ከድንበር አንስቶ ወደ ካምፓላ ያደርሳቸዋል። 

ሆኖም ሰነዳቸው በሰው እጅ ስለሚያዝ አማራጭ አይኖራቸውም። ሌላ የስደት አዙሪት ውስጥ ገብተው ራሳቸውን ያገኙታል። 

ከዚህ በኋላ አዲስ የስደት መንገድ ይታሰባል። በመጨረሻ በሜዲትራኒያን አድርገው ወደ አውሮፓ የመግባቱን ጉዞ ይጀምሩታል። 

በሐበሎም እንደሚለው አንድ ስደተኛ ሩዋንዳ የሚያቆየው አንዳችም ምክንያት አይኖርም። 

“ይህን ክፈል ብለው ሲሉህ መቼስ ምን አማራጭ ይኖርሃል? አድርግ ያሉህን ከማድረግ ውጭ” ይላል በወቅቱ ለዚህ ውሳኔ ያበቃውን ሲያስረዳ። 

ከሩዋንዳ ወደ ኡጋንዳ ለምን ይወሰዳሉ? 

መብራሕቶም ተስፋሚካኤል የተባለ ሌላ ኤርትራዊ ይህን ጆን በሚል ስም የሚታወቀውን ሰው ተጋፈጠው።

“በግል ጆንን ላነጋግረው ሞክሬ ነበር” ይላል በ2014 ከእስራኤል ወደ ኪጋሊ ተወስዶ የነበረው መብራሕቶም።

በዚያ ሆሎት በሚባል መጠለያ 9 ወራትን አሳልፏል። “ጆን ከዚህ መልቀቅ አለባችሁ ሲለን ለምን ብዬ ጠየቅኩት።” 

“ከእስራኤል ስንለቅ ሩዋንዳ ቋሚ የስደተኛ መብት ታገኛላችሁ ተብለን ነው፤ ለምንድነው ከዚህ መውጣት አለባችሁ የምትለን?’ ስል ተጋፈጥኩት።” 

“ምናልባት እዚህ ለሦስት ቀናት እንድትቆዩ ነው የተፈለገው፤ ከዚያ ግን የግድ መልቀቅ ይኖርባችኋል” አለኝ። 

ሌላው ኤርትራዊ ተስፋይ ጎሹ በየካቲት 2015 ሩዋንዳ ተላከ።

እሱም ተመሳሳይ ሕይወት ውስጥ ነው ያለፈው። ለምን ወደ ሩዋንዳ እንደሚላኩ ሲጠየቅ፣ “ምናልባት የሩዋንዳ ባለሥልጣናትና ሰው አስተላላፊ ደላላዎች እጅና ጓንት ሆነው እየሠሩ ይመስለኛል” ይላል። 

“እንደ አፍሪካዊነቴ በሩዋንዳ የተሻለ ክብካቤ የማገኝ መስሎኝ ነበር” የሚለው ተስፋይ በኋላ ላይ ባለሥልጣናት ሲመሳጠሩበት ተስፋ እንደቆረጠ ያስረዳል። 

“በቃ እኛን አይፈልጉንም”

"ብዙውን ጊዜ ሰዎች ድንበር እንድትሻገር ሲያደርጉህ በምሥጢር ነው፤ እኒህ ሰዎች ግን በግላጭ ነው ይህን ሁሉ የሚያደርጉት፤ ለምሳሌ ድንበር ስንደርስ ሰነዳችን እንድናሳይ ያደርጉናል”

ይህም የሚያሳየው ባለሥልጣናት መሆናቸውን ነው ብሎ ይገምታል። 

ቢቢሲ የሩዋንዳ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ የጠየቀ ሲሆን ቃል አቀባይ የሆኑት ሰው “የምትሉት ስለመፈጸሙ አናውቀውም፣ ሆኖም ግን ምርመራ እናደርጋለን ብለዋል። 

“...የሩዋንዳ መንግሥት የሕዝቡን እንዲሁም ወደ አገሩ የሚገቡ ሰዎችን ደኅንነት መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፤ ይህ ታዲያ ስደተኞችንም ይጨምራል

የማይጨበጠው ተስፋ

ባሐበሎም በመጨረሻ በጀልባ ተሳፍሮ ግሪክ ገባ። ከዚያም በየብስ ወደ ስዊዘርላንድ ተሳፈረ። አሁን በዙሪክ ኑሮን ጀምሯል።

የተመሠከረለት የባንቧ ሠራተኛ ለመሆን የሚያስችለውን የመጨረሻ ፈተናውን ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ነው።

ወደ ሩዋንዳ ከተላኩ ሌሎች ስደተኞች አንጻር ራሱን እንደ ዕድለኛ ይመለከታል። 

“በትንሹ 10 ሰዎች በሊቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል። የተወሰኑት በእስልምና አክራሪው ዳኢሽ ቡድን ተቀልተዋል። የተወሰኑት ባሕር ውስጥ ሰምጠዋል። ” 

ዶ/ር ዯታም ጊድሮም ይህን የእስራሌ የስደተኞች ጉዳይ ስምምነትን በቅርብ የሚያውቁ ሰው ናቸው። 

እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ይህ ስምምነት ባዶ ተስፋ ነበር። 

ባዶ ተስፋ ብቻም ሳይሆን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንዳመዘነ ያስረዳሉ።

“ስደተኞችን ለሕገ ወጥ ሰው አስተላላፊዎች አሳልፎ የሰጠ” ይሉታል በደምሳሳው። 

አምነስቲ ኢንተርናሽናልም አገራት ስደተኛ ጠያቂዎችን ወደ ሦስተኛ አገር የመላካቸውን ጉዳይ አጥብቆ ይኮንናል። 

የዩኬ ከሩዋንዳ ጋር ያደረገችው ስምምነት የ5 ዓመት የሙከራ ሂደት ሲሆን ስደተኛ ጠያቂዎችን ለአጭር ጊዜና በቋሚነት የማስፈር መርሐግብር ነው። 

የሩዋንዳ መንግሥት፣ ከዩኬ ጋር ያደረኩት ስምምነት ከእስራኤል ጋር ከነበረው ስምምነት ጋር የሚነጻጸር አይደለም ይላል። 

 “የእስራኤሉ ስምምነት እንዳልሠራ ሲረጋገጥ እንዲቆም ተደርጓል” ሲልም ያክላል። 

በዚህ የዩኬ መርሐግብር ስደተኞችን ለማገዝ የሚያስችሉ በርካታ ዘዴዎች ተቀምጠዋል የሚለው የሩዋንዳ መንግሥት ይህም በዩኬ መንግሥት ገንዘብ የሚፈጸም ነው። 

“ይህ አዲስ ስምምነት ከሁለቱ አገራት በሚውጣጣ ጥምር ኮሚቴ ክትትል የሚደረግለት ሲሆን ይህ አደገኛ ጉዞን ወደ ዩኬ የሚያደርጉ ሰዎችን በሩዋንዳ አዲስ ሕይወትን እንዲጀምሩ የሚያስችል ነው” ይላሉ የሩዋንዳ መንግሥት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ።