ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአውሮፓ ኅብረት በትግራይ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ጠየቀ
በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ መንግሥት በትግራይ ለአንድ ዓመት ያህል ተቋርጠው የቆዩት መሠረታዊ አገልግሎቶች መልሰው እንዲጀመሩ ማድረግ አለበት አሉ።
የአውሮፓ ኅብረት የቀውስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺክ በትዊተር ገጻቸው ላይ፣ በትግራይ ውስጥ “ለሕዝቡ መሠረታዊ አገልግሎቶች መመለስ አለባቸው” በማለት፣ ያለው አሳሳቢ ሁኔታ የእርዳታ ሠራተኞች አቅርቦታቸውን እንዲያፋጥኑ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የኅብረቱ ባለሥልጣን ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ወደ ትግራይ የሚገባው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መጨመር አወንታዊ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፣ ነገር ግን ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል “የበለጠ መደረግ አለበት” ማለታቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።
በትግራይ ክልል “የባንክ፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮሙኒኬሽን አገለግሎቶችን ተቋርጠው እንዲቆዩ የማድረግ ምክንያቱ አይታየኝም” ያሉት ሌናርቺክ፣ ክልሉ ላይ ያለው ከፊል ዕቀባ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን 5.2 ሚሊዮን ሰዎችን ለመድረስ የሚደረገውን ጥረት እያደናቀፈው ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች ትግራይን ለቀው ከወጡና የትግራይ ኃይሎች መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ የእርዳታ አቅርቦትና መሠረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል።
ባለፈው መጋቢት ወር መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺነት የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ እርዳታ ወደ ክልሉ በየብስ እየገባ ነው።
የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ጃኔዝ ሌናርቺክ፣ ወደ ትግራይ እየገባ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ወደሚፈለገው አካባቢ ለማድረስ በነዳጅ እና በገንዘብ አቅርቦት ላይ የተጣለውን ዕቀባ መንግሥት እንዲነሳ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ለዚህም መንግሥት የትግራይ ኃይሎች የነዳጅ አቅርቦቱን ለወታደራዊ አላማ ሊያውሉት ይችላሉ የሚለውን ስጋቱን የሚያስወግድ “የቁጥጥር ዘዴ” ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ማለታቸውን ኤፒ ዘግቧል።
የአውሮፓ ኅብረት የቀውስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺክ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ባደረጉት ጉብኝት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር አዲስ አበባ ላይ እንዲሁም ወደ መቀለ ተጉዘው ከህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር መነጋገራቸው ተዘግቧል።
ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺክ፣ ከአቶ ደመቀ ጋር ሲገናኙ ስለ ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት፣ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ስለሚካሄደው የሰላም ጥረት እና በጦርነቱ ከተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አንጻር መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎችን በሚመለከት መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
ጨምሮም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት እና ከአባል አገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ገንቢ በሆነ መልኩ ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብላ እንደምታምን መናገራቸው ተጠቁሟል።
የአውሮፓ ኅብረት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ መወያየቱ የተነገረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ከአውሮፓ ኅብረት ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ወደ ኅብረቱ መቀመጫ ማምራታቸው ተነግሯል።
የኅብረቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ጋር ከተገናኙ በኋላ ወደ መቀለ መሄዳቸው የተነገረ ሲሆን፣ የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሉት ጃኔዝ ሌናርቺክ ከደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
“ፕሬዝዳንት ደብረጽዮን፣ ጃኔዝ ሌናርቺክን ተቀብለው በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ገንቢ ውይይት አድርገዋል” ሲሉ አቶ ጌታቸው ያሰፈሩ ሲሆን፣ የኅብረቱ ባለሥልጣን መቀለ ውስጥ የሚገኘውን ዋነኛ የሕክምና ተቋም የሆነው አይደር ሆስፒታልን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት መካከል ንግግር እንዲደረግ እንዲሁም የሰብአዊ አርዳታ አቅርቦት ያለምንም ችግር ወደ ክልሉ እንዲገባ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል።
የኅብረቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጃኔዝ ሌናርቺክ ከትግራይ በተጨማሪ በድርቅ ክፉኛ የተጠቃውን የሶማሌ ክልልን እንደጎበኙም ተነግሯል።
የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት አንጻር ጠንካራ አቋም ያንጸባረቀ ከመሆኑ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ድጋፍ የተወሰነውን ማገዱ ይታወሳል።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ነበር።