ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኬንያ መንግሥት የነዳጅ ዋጋን ለማረጋጋት 140 ሚሊዮን ዶላር መደበ
በዓለም አቀፉ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ቢጨምርም በኬንያ ያለውን የነዳጅ ዋጋ ባለበት እንዲቀጥል የአገሪቱ መንግሥት አዲስ የነዳጅ ድጎማ አደረገ።
ይህም ኬንያውያን በሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ ካጋጠማቸው የዋጋ ጭማሪ በተጨማሪ ከሌላ የዋጋ ንረት ጋር ትግል ውስጥ እንዳይገቡ ያደርጋል ተብሏል። መንግሥት ከወረሃዊ የዋጋ ማሻሻያ በፊት በነዳጅ ላይ ያደርግ የነበረውን ድጎማ ሊያነሳ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቶ ነበር።
ይሁን እንጂ የአገሪቱ መንግሥት የውሳኔ ለውጥ በማድረግ አሁን ያለውን የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ለተጨማሪ 30 ቀናት ባለበት እንዲቀጥል የ141 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ አድርጓል።
በሰኔ ወር የአገሪቱ ባለስጣናት አሁን እየተደረገ ያለው የነዳጅ ድጎማ ''ዘላቂነት የሌለው ነው'' ሲሉ አስተያየት ሰጥተው ነበር።
ባለፈው ዓመት ኬንያ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መከሰቱን ተከትሎ ለነዳጅ ድጎማ ከ860 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች። የኢትዮጵያ ጎረቤት ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬንያ በቀጠናው ካሉ አገራት ነዳጅ በውድ የምታቀርብ አገር ነች። ድጎማው ባይኖር ኖሮ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ አንድ ሊትር ቤንዚን 1.80 ዶላር ይደርስ ነበር። አሁን ላይ ዋጋው 1.34 ዶላር ነው።
ከኬንያ በመከተል በአካባቢው በከፍተኛ ዋጋ ነዳጅ የሚገዛባቸው አገራት ሱዳን እና ኡጋንዳ ሲሆኑ፤ ነዳጅ የምታመርተው ሱዳን ለአንድ ሊትር 1.50 ዶላር ስታስከፍል፣ በቅርቡ የነዳጅ ዘይት ያገኘችው ኡጋንዳ ደግሞ አንድ ሊትር በ1.6 የአሜሪካ ዶላር ታቀርባለች።
በአፍሪካ ነዳጅ በከፍተኛ ዋጋ ከሚሸጡባቸው አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ ተጠቃሽ ናት። በመረጃው መሠረት በደቡብ አፍሪካ አንድ ሊትር ነዳጅ የሚሸጠው በ1.48 ዶላር ነው። በዓለም ላይ ዜጎቿን አነስተኛ የነዳጅ ዋጋ የምታስከፍለው ነዳጅ አምራች የሆነችው እና ምጣኔ ሀብቷ ክፉኛ የተጎሳቆለባት ቬንዙዌላ ነች።
እንደ ግሎባል ፔተሮል ፕራይስ ከሆነ በቬንዙዌላ በ1 የኢትዮጵያ ብር (0.02 የአሜሪካ ዶላር) አንድ ሊትር ነዳጅ መሸመት ይቻላል።