ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሕንድ አንድ ሰው በዝንጀሮ ፈንጣጣ ሲሞት 20 ሰዎች ተለዩ
በሕንድ ኬሬላ በተባለች ግዛት ውስጥ አንድ ሰው በዝንጀሮ ፈንጣጣ መሞቱ ተዘገበ።
የ22 ዓመቱ ግለሰብ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ነበር ወደ ሕንዷ ኬሬላ ግዛት በቅርቡ የተጓዘው።
የግዛቲቱ የጤና ሚኒስትር ቬና ጆርጅ እንዳሉት፣ ግለሰቡ ውጭ አገር ሳለ በዝንጀሮ ፈንጣጣ መያዙ ታውቋል።
በዚህም ከአፍሪካ ውጭ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የሞተ አራተኛው ሰው ነው።
ከግለሰቡ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው 20 ሰዎችም ተለይተው እንዲቆዩ ተደርገዋል።
እነዚህም ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹና በቅርቡ አብረውት እግር ኳስ የተጫወቱ 9 ሰዎች ናቸው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚከሰተው ፈንጣጣ ከሚያስይዘው ቫይረስ ጋር ተቀራራቢ በሆነ የቫይረስ ዝርያ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ አጣዳፊ ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ እንደሆነ ከጥቂት ሳምንት በፊት ማወጁ ይታወሳል።
የግለሰቡን ሕልፈት ተከትሎ በሕንድ የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚቴ ተቋቁሞ የሟቹን የሕክምና ታሪክ እየመረመ እንደሆነ ተገልጿል።
ግለሰቡ ትኩሳት የነበረው ሲሆን፣ ሆስፒታል ሲወሰድ ሰውነቱ እብጠት ነበረው።
ነገር ግን ሽፍታ ስላልታየበት የዝንጀሮ ፈንጣጣ ሊሆን እንደሚችል አልተገመተም።
በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ሳለ በቫይረሱ መያዙ ቢነገረውም፣ ቤተሰቡ ለጤና ሚኒስትር ያሳወቀው ዘግይቶ ነው።
ሆስፒታል ሳለ ሕመም እንደጸናበትና የመተንፈሻ መርጃ (ቬንትሌተር) ታግዞ ይተነፍስ እንደነበርም ተገልጿል።
ከዚያም ሕመሙ የዝንጀሮ ፈንጣጣ እንደሆነ ታውቋል።
ግለሰቡ ሕክምና ሳያገኝ ለምን እንደዘገየ እየተጣራ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ወደ ኬሬላ ግዛት አብረውት የተጓዙ ሰዎችም ስለ ጉዳዩ እንዲያውቁ ተደርጓል።
ከግለሰቡ ጋር የቅርብ ንክኪ ስላልነበራቸው ግን እምብዛም አያሰጋም ተብሏል።
ሕንድ ውስጥ እስካሁን አራት ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ መያዛቸው ታውቋል። ሦስቱ በኬሬላ ግዛት ሲኖሩ አንዱ በዴልሂ ይገኛል።
መጀመሪያ የተገኘው ታማሚ በኬሬላ ሆስፒታል ታክሞ አገግሟል።