ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሳዑዲው ልዑል የፈረንሳይ ጉብኝት ቁጣን ቀሰቀሰ
የሳዑዲ አረቢያ ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን በፈረንሳይ እያደረጉት ያለው ጉብኝት ቁጣን ቀሰቀሰ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ልዑሉ በተለይ ከጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ ጋር ተያይዞ የጠለሸው ስማቸውን ለማደስ ያደረጉት ጉብኝት ነው በሚል ትችት እየሰነዘሩ ነው።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሐሙስ ምሽት ለሞሐመድ ቢን ሰልማን የእራት ግብዣ አድርገውላቸዋል።
የሳዑዲው ልዑል ወደ ፓሪስ የተጓዙት የነዳጅ ዋጋ እየናረ ባለበት እና የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ስጋቶች በጠነከሩበት ወቅት ነው።
ልዑሉ ቢን ሳልማን በቱርክ በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ ጋዜጠኛው እንዲገደል ትዕዛዝ አልሰጠውም ሲሉ ይከራከራሉ።
የኻሾግጂ እጮኛ በመሐመድ ቢን ሳልማን ጉብኝት በጣም መበሳጨቷን ገልጻለች። ፕሬዝዳንት ማክሮን የእጮኛዋን ‘’ገዳይ በሙሉ ክብር” ተቀብለዋል ስትልም ከሳለች።
መሐመድ ቢን ሳልማን ከማክሮን ጋር ከመገናኘታቸው አንድ ቀን ቀደም ብለው ፓሪስ ከገቡ በኋላ በቅንጡ ማረፊያ ውስጥ ቆይተዋለ።
ሁለቱ መሪዎች ሐሙስ ዕለት ቤተ-መንግስት ከመገናኘታቸው ከሰዓታት በፊት ሶስት ቡድኖች ሞሐመድ ቢን ሳልማን ኻሾግጂን በማሰቃየት እና በመግደል ወንጀል ተባባሪ ናቸው ሲሉ ክስ መስርተውባቸዋል።
ከከሳሾቹ መካከል አንዱ የሆነው ዲሞክራሲ ለዓረብ ዓለም የተሰኘው ተቋም መሐመድ ቢን ሳልማን የአገር መሪ ስላልሆኑ ያለመከሰስ መብት የላቸውም ብሏል።
የሂዩማንራይትስ ዎች ባልደረባ ቤኔዲክ ጄኔሮድ በበኩላቸው ማክሮን በመብቶች ላይ ያላቸውን ጠንካራ እና ተጨባጭ ቁርጠኝነት ሳያረጋግጡ የልዑሉን ወንጀል ለማረረሳሳት ሞክረዋል ብለዋል።
ከስብሰባው በፊትም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ረዳት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ "በአጠቃላይ" በንግግራቸው ወቅት እንደሚነሳ ጠቅሰዋል። ነገር ግን አውሮፓ ያጋጠማትን ችግር ለመፍታት ሁሉንም የፈረንሳይ አጋር አገራትን ማነጋገር አስፈላጊ ነውም ብለዋል።
ሁለቱ ሰዎች ከኻሾግጂ ግድያ በኋላ በታሕሳስ ወር በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ከተማ ጨምሮ በተለያየ ግዜ ተገናኝተው ተነጋግረዋል።