ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማንቸስተር ሲቲ ከቶተንሃም፣ ኢፕስዊች ከማንቸስተር ዩናይትድ...የሳምንቱ ጨዋታዎች ግምት
አዲሱ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም የመጀመሪያ ጨዋታውን እሑድ ከኢፕስዊች ጋር ያከናውናል። አሰልጣኙ ምን አይንት አሰላለፍ ይዞ ይቀርባል የሚለው በጉጉት ይጠበቃል።
“አሰልጣኙ የራሱን አሰላለፍ ይዞ ይመጣል የሚል ሐሳብ በብዙዎች ዘንድ አለ” ሲል የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን ተናግሯል።
“በሦስት የመሐል ተከላካዮችን ከመስመር ተከላካዮች ጋር ያሰልፋል? ወይስ ክንፍ ተጫዋቾችን ያጫውታል?” የሚለው እሑድ ምላሽ ያገኛል ብሏል።
ሱተን ይህንን ጨምሮ የ12ተኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ ጨዋታዎችን ግምት እንደሚከተለው አስቀምጧል።
ቅዳሜ
ሌስተር ከ ቼልሲ
ኤንዞ ማሬስካ በክረምቱ ሌስተርን ከለቀቁ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቀድሞ ቡድናቸው በማቅናት በቀላሉ ሦስት ነጥብ ያሳካሉ።
ሌስተሮች ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ከተመለሱ በኋላ ባላቸው አቋም ደስተኞች ናቸው።
እንደሌሎቹ አዳጊ ቡድኖች ሁሉ ቡድኑ በርካታ ጎል ከማስተናገዱም በላይ ቼልሲ በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል።
ኮል ፓልመር ከጉዳቱ አገግሞ ከተሰለፍ ለቼልሲ ቀላል ጨዋታ ይሆናል።
ግምት፡ 1 – 3
በርንመዝ ከ ብራይተን
ሁለቱ ቡድኖች ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በፊት ማንቸስተር ሲቲን በተካታታይ ማሸነፍ ችለዋል።
በጣም ጠንካራ እና ለመገመት ከባድ ጨዋታ ይሆናል።
በተለያየ አቀራረብ ቢሆንም ሁለቱም ማራኪ እና ማጣቃት ላይ የተመሠረተ አጨዋወትን ይመርጣሉ።
በጨዋታው ጎሎች ቢቆጠሩም ጨዋታው አቻ ይጠናቀቃል።
ግምት፡ 1 – 1
አርሰናል ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
አርሰናል ነጥብ እየጣለ መቀጠል የለበትም። ዴክላን ራይስ በጉዳት ላይሰለፍ ቢችልም ጨዋታ ቀያሪው ማርቲን ኦዴጋርድ መመለሱ ትልቅ ዜና ነው።
ደጋፊዎቹም የተጫዋቹ መመለስ ቡድኑን ውጤት ያሻሽላል የሚል ተስፋ አላቸው።
የአንዳንድ ተጫዋቾች በጉዳት ሲርቁ ምን ያህል እንደሚያጎድሉ ኦዴጋርድ በተጎዳበት ወቅት ታይቷል።
የኑኖ ኤስፕሪቶ ሳንቶ ቡድን ጠንካራ ሲሆን ሊቨርፑልንም በሜዳው ማሸነፍ ችሏል። በዚህ ጨዋታ ግን ድሉ የአርሰናል ነው።
ግምት፡ 2 – 0
አስቶን ቪላ ከ ክሪስታል ፓላስ
አስቶን ቪላ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ቢሸነፍም ክሪስታል ፓላስ ደግሞ ከዚህ በባሰ ችግር ውስጥ ይገኛል።
ኡናይ ኤምሬ በድናቸውን በማቀናጀት ጥሩ ስለሆኑ ውጤት ያገኛሉ።
ፓላስ ዘንድሮ በብዙ መልኩ ጥሩ ባለመሆኑ መሻሻሎችን ማሳየት ይኖርባታል።
ቪላ በሜዳው ስለሆነ ሦስት ነጥብ ያሳካል
ግምት፡ 2 – 1
ኤቨርተን ከ ብሬንትፎርድ
ዘንድሮ ብሬንትፎርድ በሜዳው ጥሩ ቢሆንም ከሜዳው ውጭ ውጤታማ አይደለም።
ኤቨርተን ደግሞ በሜዳው አንድ ጨዋታ ብቻ ነው ያሸነፈው።
የሾን ዳይሽ ቡድን ዘንድሮ ለመገመት አስቸጋሪ ከሆኑ ቡድኖች አንዱ ነው።
ብሬትንፎርድ ጎል ማስቆጠር የሚችሉ እንደ ዮአን ዊሳ እና ብሪያን ምቡሞ ያሉ ተጫዋቾችን ቢይዝም ጨዋታው አቻ ይጠናቀቃል።
ግምት፡ 2 – 2
ፉልሃም ከ ዎልቭስ
ዎልቭስ የመጀመሪያ ድሉን ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በፊት ሳውዝሃምፐተንን አሸንፎ አሳክቷል። አጥቂው ማቲያስ ኩንሃም ጎል ማስቆጠር ጀምሯል።
ፉልሃም በሜዳው ከመጫወቱም በላይ በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል።
ኤሚል ስሚዝ ሮው በጥሩ አቋም ላይ ከመሆኑም በላይ ራውል የሚኔዝም በቀድሞ ቡድኑ ላይ ጎል ሊያስቆጥር ይችላል።
ግምት፡ 2 – 1
ማንቸስተር ሲቲ ከ ቶተንሃም
ፔፕ ጋርዲዮላ የውል ማረዘሚያውን በመፈረሙ የሌሎች ቡድን ደጋፊዎችን ማበሳጨቱ የሚጠበቅ ነው። ብስጭቱ ከሊቨርፑል እና ከቀያዩ የማንቸስተር መንድር እንደሚበረታ ግልጽ ነው።
ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ቢሸነፍም ማንቸስተር ሲቲ አሁንም በአምስት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የአሰልጣኙ አዲስ ውል ቡድን እንደሚያነቃቃው ይጠበቃል።
ቶተንሃም ዘንድሮ ችግር ውስጥ እንዳለ ቢገለጽም ከሦስተኛ ደረጃ በሦስት ነጥብ ብቻ ርቀዋል።
ቶተንሃም ኢትሃድ ላይ ምንም ነጥብ አያሳካም። ቶተንሃም አጨዋወቱን ስለማይቀይር ጎል ቢያስቆጥርም ድሉ የሲቲ ይሃናል።
ግምት፡ 3 – 1
እሑድ
ሳውዝ ሃምፐተን ከ ሊቨርፑል
በአምስት ነጥብ ልዩነት ሊጉን የሚመራው ሊቨርፑል በአሰልጣኝ አርን ስሎት አጀማመር ደስተኛ ነው።
ይህ በሊጉ መጨረሻ ላይ ያለውን ቡድን በቀላሉ የሚያሸንፍበት ጨዋታ ነው።
ጨዋታውን ሊቨርፑል ቢያሰንፍ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አይሆንለትም።
ሳውዝሃምፐተን ምን ያህል ቡድኖችን ተቋቁሞ መጫወት እንደሚችል ከሲቲ ጋር አሳይቷል። ይህንን በዚህ ጨዋታም ይደግማል።
ግምት፡ 0 – 2
ኢፕስዊች ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ቶተንሃምን ማሸነፉ ለኢፕስዊች በራስ መተማመን ይሰጣል። በተለይም አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ከቡድኑ ጋር በቂ ጊዜ ካለማግኘቱ ጋር ተጨምሮ ማንቸስተር አዲስ አጨዋወት ይዞ ከቀረበ ኢፕስዊች ተፎካካሪ ይሆናል።
ዩናይትድ የኋላ መስመሩን ማጠናከር ሲገባው ኢፕስዊችም የተካላካይ መስመሩን ግዴለሽነት መቀነስ አለበት።
ብዙዎች አሞሪም በድል ይጀምራሉ ቢሉም ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።
አስቡት እስቲ አዲሱ አሰልጣኝ የፈጠረውን ብሩህ መንፈስ ኢፕስዊች አሸንፎ ውሃ ቢከልሰበት?
ግምት፡ 1 – 1
ሰኞ
ኒውካስል ከ ዌስት ሃም
የዌስትሃሙ አሰልጣኝ ዩሊየን ሎፕቲጉ ከመባረር ጫፍ ላይ ከሚገኙ አሰልጣኞች መካከል ናቸው።
ባለፈው ዓመት ዌስት ሃም 3 ለ 1 ከመምራት 4 ለ 3 ተሸንፎ ወቅቱ አሰልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ የኮንትራት ውል እንዳይራዘምላቸው ሆነ።
አዲሱ አሰልጣኝም ግን ያን ኣህል አመርቂ የሚባል ነገር አላሳዩም።
አልክሳንደር አይዛክ ወደ ጥሩ አቋሙ ከመመለሱ ጋር ተደምሮ በዚህ ጨዋታም ዌስት ሃም ውጤት የሚያገኙ አይመስልም።
ግምት፡ 2 – 1