ትራምፕ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመገደብ እና ለነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ቅድሚያ ለመስጠት ወሰኑ

የትራምፕ አስተዳደር በሚቀጥለው ዓመት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ወደ 7 ሺህ 500 ለመገደብ ቢወስንም ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ ለነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ሐሙስ ዕለት ይፋ በተደረገ ማስታወቂያ መሠረት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከተቀመጠው 125 ሺህ ገደብ በእጅጉ የቀነሰ ከመሆኑም በላይ በዝቅተኛው ክብረወሰን ሆኖ የሚመዘገብ ነው።

ለቅነሳው ምንም ምክንያት ባይሰጥም "በሰብአዊ ጉዳዮች ምክንያት ወይም ለአገር ጥቅም የሚውል ነው" ብሏል።

በጥር ወር ትራምፕ የአሜሪካ የስደተኞች የመግቢያ ፕሮግራም ወይም ኡስራፕን ለማገድ የሚያስችለውን የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ፈርመዋል። ይህም የአሜሪካ ባለስልጣናት ለብሔራዊ ደህንነት እና ለሕዝብ ደህንነት ቅድሚያ እንዲሰጡ የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ዝቅተኛው የስደተኞች የመግቢያ ገደብ የተጣለው በ2020 የመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር ሲሆን ለ2021 የበጀት ዓመት 15 ሺህ መመደቡ ይታወሳል።

በፌዴራል ሬጅስተር ድረ-ገጽ ላይ በተለጠፈው ማስታወቂያ መሠረት ከ7 ሺህ 500ዎቹ ውስጥ "በዋነኛነት" ለአፍሪካነር ደቡብ አፍሪካውያን እና "በየትውልድ አገራቸው ሕገ-ወጥ ወይም ኢ-ፍትሃዊ መድልኦ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች" እንደሚመደብ ገልጿል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በየካቲት ወር ለደቡብ አፍሪካ የሚሰጠውን ወሳኝ እርዳታ አግደዋል። የአፍሪካነር ማኅበረሰብ አባላት (በአብዛኛዎቹ የቀደሙት የደች እና የፈረንሳይ ሰፋሪዎች ነጮች ናቸው) በአሜሪካ ውስጥ እንደ ስደተኛ እንዲሰፍሩ እንዲፈቀድላቸውም ቃል ገብተዋል።

በዋሽንግተን የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢብራሂም ራስል ትራምፕ "የዘር የበላይነትን በማነሳሳት" እና "የነጭ ተጎጂነትን ለማስጮህ" ሞክረዋል በማለታቸው ተባረዋል።

በግንቦት ወር ደግሞ በኦቫል ኦፊስ ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጋር በነበራቸው ቆይታ በአገራቸው ውስጥ ነጭ ገበሬዎች እየተገደሉ እና "እየተሰደዱ" እንደሆነ ትራምፕ ተናግረዋል።

ዋይት ሐውስም የተገደሉ ነጭ ገበሬዎች የቀብር ቦታዎችን የሚያሳይ ነው ያለውን ቪዲዮም አጫውቷል። ቪዲዮዎቹ በ2020 በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተተከሉ መስቀሎችን የሚያሳይ ሲሆን ከዚያ ቀደም ለሞቱ ገበሬዎች ማስታወሻነት የተተከሉ ነበሩ።

በውጥረት የተሞላበት ስብሰባ የተከናወነው አሜሪካ ለ60 አፍሪካነርስ ጥገኝነት ከሰጠች ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።

የደቡብ አፍሪካ መንግስት አፍሪካነርስ እና ሌሎች ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ጥቃት እየደረሰባቸው ነው መባሉን አጥብቆ አስተባብሏል።

ትራምፕ ዋይት ሐውስ በደረሱበት የመጀመሪያ ቀን አሜሪካ "ብዙ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች እና በተለይም ስደተኞችን ወደ ማኅበረሰቦቿ የመሳብ አቅም ማጣት" እና "ደህንነታቸውን የሚጠብቅ" መሆኑን ለማንፀባረቅ ዩስራፕን እንደምታግድ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን የመቀበል ፖሊሲው ከስደተኞች ተሟጋች ቡድኖች ኢ-ፍትሃዊ ነው በሚል ትችትን አስከትሏል።

አንዳንዶች አሜሪካ በትውልድ አገራቸው ውስጥ ሊጎዱ ለሚችሉ እና ስጋት ላላባቸው የሌላ አገር ዜጎች ወይም አፍጋኒስታንን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካን ጦር ያገዙ የቀድሞ አጋሮችን እንኳን ረስታለች ሲሉ ተከራክረዋል።

"ይህ ውሳኔ የስደተኞችን ቁጥር ብቻ ዝቅ አያደርገውም። ይልቁንም አቋማችንን ጭምር ዝቅ ያደርገዋል" ሲሉ የግሎባል ሪፊዩጂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና ፕሬዝዳንት ክሪሽ ኦማራ ቪኛራጃህ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።

"ከአፍጋኒስታን እስከ ቬንዙዌላ እስከ ሱዳን እና ከዚያም በላይ ባሉ አገሮች ውስጥ በችግር ባጋጣመበት በዚህ ወቅት፣ የመግቢያ መስፈርቶችን በአንድ ቡድን ላይ ማተኮር የፕሮግራሙን ዓላማ እና ተዓማኒነት ያዳክማል" ሲሉ አክለዋል።

ሪፊዩጂስ ኢንተርናሽናልም እርምጃውን "የስደተኞችን ጥበቃ እና የአሜሪካን እሴቶች መሳለቂያ ያደርጋል" ሲሉ ተቃውሟል።

"እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አንዳንድ አፍሪካነርስ ሊያጋጥማቸው የሚችለው ችግር ምንም ይሁን ምን፣ ለስደተኛነት የሚያበቃ ምንም አይነት አሳማኝ ጥያቄ የላቸውም። ስልታዊ ፍርድን እየሸሹ አይደለም" ሲል ሪፊዩጂየስ ኢንተርናሽናል በመግለጫቸው ተናግሯል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ስለአዲሱ ውሳኔ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

ፕሬዝዳንት ራማፎሳ በኦቫል ኦፊስ ስብሰባ ወቅት የትራምፕ ባለስልጣናት ስለጉዳዩ ደቡብ አፍሪካውያንን እንደሚያዳምጡ ተስፋ እንዳላቸው ብቻ ተናግረዋል። በኋላም "ስለሁሉም ነገር [በትራምፕ] ጭንቅላት ውስጥ ጥርጣሬ እና እምነት ማጣት አለ" ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ራማፎሳ መንግሥት በአንዳንድ ሁኔታዎች ያለ ካሳ በግል ባለቤትነት የሚተዳደሩ ያላቸውን መሬቶች መያዝ የሚያስችለው አወዛጋቢ ሕግ ፈርመዋል።

አገሪቱ በዘር ላይ የተመሰረተ የወንጀል መረጃን ባታወጣም፣ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የታተሙ አሃዞች እንደሚያሳዩት በደቡብ አፍሪካ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ 2024 ድረስ ሰባት ሺህ ሰዎች ተገድለዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 12ቱ በእርሻ ጥቃቶች የተገደሉ ሲሆን ከ12ቱ ውስጥ አንዱ ብቻ በግርብርና የተሰማራ ነበር። ሌሎች አምስት የእርሻ ነዋሪዎች ሲሆኑ ጥቁር ሊሆኑ የሚችሉ አራቱ ደግሞ ሠራተኞች ነበሩ።