ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈረንሳይ ባጌት የተሰኘው ዳቦ በዩኔስኮ በቅርስነት ተመዘገበ
ለፈረሳንዮች ባጌት ከተሰኘው ዳቧቸው በበለጠ ፈረንሳይን ሊወክል የሚችል ነገር ቢኖር በጣም ጥቂት ነው።
ለነገሩ አገሪቱ በቀን 16 ሚሊዮን የሚገመት ባጌት ዳቦንም ታመርታለች።
ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የባጌት ምርት እያሽቆለቆለ መጥቷል።
ለዚህም ምክንያቱ ባህላዊ መጋገሪያዎች እንደ ትልልቅ የገበያ አዳራሾች ማንሰራራትና ያለ እርሾ ዳቦ መገጋር ተወዳጅ መሆን ጋር በተያያዘ በገጠማቸው ችግር ነው።
ሆኖም ለፈረንሳውያን አንድ የሚደሰቱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ዩኔስኮ ባጌትን “በማይዳሰስ የባህል ቅርስ” ዝርዝር ውስጥ አካቶታል።
ተቋሙ እንዳስታወቀው “የዳቦው ሙያና ጥበብ የተሞላበት አገጋር እና ባህሉን” ከሌሎች 600 የቅርስ ዝርዝሮች ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።
በዘንድሮው ከፈረንሳዩ ባጌት በተጨማሪ የቻይና ባህላዊ የሻይ አሰራር እና ታልቹም ተብሎ የሚታወቀው የኮሪያ ጭምብል ዳንስ በዩኔስኮው ዝርዝር ተካትተዋል።
የባጌት በዩኔስኮ የቅርስ ዝርዝር መካተት “የፈረንሳይን የአኗኗር ዘይቤ ያከብራል” ሲሉ የዩኔስኮ ዋና አዛዥ ኦድሪ አሶውሌይ ተናግረዋል።
ባጌት “የዕለት ተዕለት ባህል ነው፣ የፈረንሳይ የምግብ ማዕከል ነው።የመጋራትና እና የአብሮነት ተምሳሌት ነው” ብለዋል።
"እነዚህ ክህሎቶች እና ማህበራዊ ልምዶች ወደፊት ማስቀጠሉም መሰረታዊ ጉዳይ ነው” ሲሉ አክለዋል።
ባጌት መቼ እና የት እንደተጀመረ አይታወቅም።
ነገር ግን አንዳንዶች ዳቦው ለወታደሮች መሸከም ቀላል ስለሆነ ናፖሊዮን እንዳዘዘው ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ሰራተኞች ቢላ ሳያስፈልጋቸው መቁረስና መካፈል የሚችሉት ቀለል ያለ ዳቦ በማስፈለጉ በኋላ እንደመጣ ይናገራሉ። ከነዚህ የተለዩት ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1830ዎቹ የነበረ ኦስትሪያዊ ዳቦ ጋጋሪ ቅርጹን እንዳመጣው ያስረዳሉ።
ሆኖም ባጌት በሚል ስም በይፋ የተሰየመው ከ100 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 1920 ነው። በዚያን ጊዜ ባጌት ለመባልም ደረጃ የወጣለት ሲሆን ይህ 80 ሴንቲሜትር ርዝመትና 250 ግራም መመዘን ነበረበት። እስከ አውሮፓውያኑ 1986 ድረስም የተወሰነ ዋጋ ነበረው።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ባጌት አገሪቱን መቆጣጠር ቻለ። ሆኖም ከ1970 ጀምሮ በየዓመቱ 400 የሚጠጉ የዳቦ መጋገሪያዎች የሚዘጉ ሲሆን ቁጥሩም ከ55 ሺህ ወደ 35 ሺህ ዝቅ ማለቱን አጃንስ ፍራንስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ከአመት ወደ አመት የዳቦ መጋገሪያዎች ቁጥር ዝቅ ቢልም ባጌት የፈረንሳይ ማንነት መገለጫ እንደሆነ ይገኛል።