ትራምፕ እና ባይደን ቅድመ ምርጫውን በማሸነፍ ለዋናው ምርጫ ድጋሚ ሊፋጠጡ ነው

በአሜሪካ ምርጫ ማክሰኞ ዕለት ‘ሱፐር ቲዩስዴይ’ ትባላለች። የቅድመ ምርጫው የመጨረሻዋ ቀን ናት።

ትራምፕ በጭብጨባ እና ሆታ ለተሰባሰቡ ደጋፊዎቻቸው አሜሪካን “ወደ ቀደመ ክብሯ እንመልሳታለን” ሲሉ መልዕክታቸውን አሰምተዋል።

ማር-አ-ላጎ በሚሰኘው ፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ በሚገኘው የተንጠለለ ግቢያቸው ሆነው ንግግር ባሰሙበት ወቅት “የምንጠብቃት ቀን ቀርባለች” ብለዋል።

ተቀናቃኛቸው የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል ጆ ባይደንም በቅድመ ምርጫው የሚያስፈልጋቸውን በቂ ድምፅ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

ይህ ማለት በሚቀጥለው ምርጫ ልክ እንዳለፈው [2020] ምርጫ የሚፋጠጡት ባይደን እና ትራምፕ ናቸው ማለት ነው።

ሁለቱም ፖለቲከኞች የሚቀጥለው ምርጫ ለአገራቸው ኅልውና አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ።

ቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ እንዳለፈው ሁሉ ብዙ ግርግር እና ሁካታ ሊኖርበት እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

የተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች እንደሚያመለክቱት በርካታ አሜሪካውያን ድጋሚ ከባይደን እና ከትራምፕ መምረጥ አይፈልጉም። ነገር ግን ሌላ ምርጫ ያላቸው አይመስልም።

ሁለቱ የዕድሜ ባለፀጋ ፖለቲከኞች ከዋናው ምርጫ በፊት የፓርቲያቸውን ይሁንታ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ድምፅ በቅድም ምርጫው ማጋበስ ችለዋል።

ለወትሮው እጅግ ተጠባቂ የነበረው ‘ሱፐር ቲዩስደይ’ ዘንድሮ ደብዝዟል።

ትራምፕ፤ በአላባማ፣ አርካንሳ፣ ካሊፎርኒያ፣ ኮሎራዶ፣ ሜይን፣ ማሳቹሴትስ፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ ኦክላሆማ፣ ቴኔሲ፣ ቴክሳስ እና ቨርጂኒያ ግዛቶችን እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል።

ይህን ግምት ያወጣው የቢቢሲው የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ የተሰኘው ሚድያ ነው።

ባይደንም እንዲሁ ከላይ በተጠቀሱት ግዛቶች ጨምሮ በዩታህ እና ቬርሞንት ድል እንደሚቀናቸው እሙን ነው።

ሁለቱ ተቀናቃኞች አንዱ አንደኛውን የአሜሪካ ኅልውና ስጋት በማለት ይገልጿቸዋል።

ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው “ይህን ምርጫ ከተሸነፍን አገር አይኖረንም” ብለዋል።

ትራምፕ ንግግር ከማድረጋቸው በፊት መግለጫ የለቀቁት ፕሬዝዳንት ባይደን ደግሞ ተቀናቃኛቸውን ለአገራቸው ካላቸው እሳቤ ይልቅ “በቁጭት እና በማጭበርበር” የሚመሩ ናቸው ብለዋል።

“ወደፊት መገስገስ እንሻለን? ወይስ ዶናልድ ትራምፕ ወደኋላ እንዲመልሰን ነው ፍላጎታችን? ወደ ብጥብጥ፣ ክፍፍል እና ጭለማ ጊዜ መመለስ እንፈልጋለን?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ትራምፕ፤ በደቡባዊው የአገሪቱ አቅጣጫ የሚታየውን ስደት በማንሳት ደጋፊዎቻቸው ድምፅ እንዲሰጧቸው ተማፅነዋል።

በቅድመ ምርጫው ትራምፕን በመገዳደር እስከ መጨረሻው የዘለቁት ሪፐብሊካኗ ኒኪ ሄሊ በቬርሞንት ግዛት እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል።

ባይደን ደግሞ በአሜሪካን ሳሞዋ እምብዛም በማይታወቁት ፖለቲከኛ ጄሰን ፓልመር ተሸንፈዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን በተለይ በእስራኤል እና ጋዛ ጦርነት ምክንያት በአንዳንድ ግዛቶች ከሚገባቸው በታች ድምፅ ነው ያገኙት።